ከአዲስ አበባ ተነስተን ወደ ሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል አረፋፍደን ነበር ጉዞ የጀመርነው። የጎጃምን መስመር ይዘን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሜዳዎቿ በቤቶች የተሞሉባትን ሱሉልታን ዐይተን፣ ያለምንም እክል ነበር ጫንጮ ከተማን ያለፍናት። መንገድ የሚዘጋጋበት ሰዓት ስላልነበረም በተረጋጋ ጉዞ መልካ ጡሬ ከተማ ምግብ በልተን፣ ዋናውን መንገድ ትተን ወደቀኝ ታጥፈን እየተሠራ ያለውን መንገድ ተያያዝነው።
ከአዲስ አበባ ወደ አማራ ክልል ከሚያስገቡ መንገዶች መካከል በብዛት በማይታወቀው በዚህ ጠመዝማዛማ መንገድ መጓዝ አስቸጋሪ ነው። ለዘመናት አሳቢ አጥቶ በኮሮኮንች ሲሰቃይ የኖረው ተጓዥ፣ በቅርቡ የዓመታት ምኞቱ ተሳክቶለት አስፋልት ሊያገኝ ግንባታው ተጀምሮለታል። እንደ ደሴ መካነ ሰላም መንገድ ወዲያው ተሠርቶ ወዲያው፣ ‹ፒስታው ይሻል ነበር!› እንዳያስብል ታስቦበት የሚሠራ ይሁን አይሁን ባይታወቅም፣ መንገዱ በዘመቻ መልክ አለፍ አለፍ እየተባለ ይሠራል።
የያዝነው መንገድ ወደ መሬዎቹ ግዛት ወደ መርሃቤቴ የሚወስድ ነው። ገዳማትንና መስህቦችን እያለፍን የዓባይ ገባር የሆነውን ጀማ ወንዝን አልፈን፣ የአውራጃው ዋና ከተማ የሆነችው አዲስ ዓለም ከተማ ከመድረሳችን በፊት ያለው ሸለቆ ውስጥ ጥንታዊ ገዳምን ጎብኝተናል። ገዳሙን ለመሳለም ከዋናው መንገድ በምንታጠፍበት ወቅት፣ ፈረንጆቹ ኦአሲስ እንደሚሉት በረሃ መካከል ሆና የለመለመች ገነት የምትመስል እድሜ የጠገበች በፍራፍሬ የተሞላች ቦታ ትታያለች። ከአረብ አገር በልጇ አማካኝነት መጥታ የማያይ ዐይኗ በርቶላት እዛው በቀረች በልበሊት በተባለች ሴት ሥም የተሰየመች ገዳም ናት።
ለረጅም ሰዓታት ተጉዘን ያላየነውን ልምላሜ የተላበሰችው ይህች በልበሊት ኢየሱስ ገዳም፣ በዙሪያዋ የተራቆተ መሬት ከቧታል። ይህ ሁኔታ በመጀመሪያው ቀን ብቻ ያየነው ሳይሆን ለቀናት በተጓዝንባቸው የሸዋ፣ ወሎና ጎጃም ግዛቶች ላይ በስፋት የሚስተዋል ነው። በኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ተተከሉ የሚባሉ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞች ሊሸፍኑ ከሚገባቸው የሄክታር ብዛት አንፃር፣ እንዲህ የጥላ ዛፍ የሚናፈቅበት የሚታረስም ሆነ የማይታረስ ሰፊ ምድር መታየት አልነበረበትም።
ከዋናዋ ከተማ እየራቅን ኪሎ ሜትሮችን ባለፍን ቁጥር ዘመናዊነት እየቀነሰ ይበልጥ ወደ ገጠር ሕይወት እየገባን እንመለከታለን። በጠመዝማዛ መንገድ ኹለት መቶ ኪሎሜትር እንኳን ሳንርቅ ዘመኑ ጥንት ላለመሆኑ አመላካች ነገር ቢኖር አንዳንድ ወጣቶች የሚለብሷቸውና የሚጫሟቸው አልባሳትና ጫማዎች ናቸው።
እናቶች እንደቀደመው ዘመን ነጭ መልበሳቸውን ሙሉ በሙሉ ትተውታል ማለት ይቻላል። ቆሻሻ የሚችል ጠቆር ያለ ቀሚስ ለብሰው በብዛት ይታያሉ። የማጠቢያ ውሃና ሳሙና እጦት ጥንትም ሆነ አሁን ያለ ቢሆንም፣ ልዩነቱ እንስራ በጀሪካን መተካቱ ነው። አልፎ አልፎ ‹ሰዎች ለሰዎች› የተሰኘውን በጎ አድራጎት ድርጅት በመሠረቱት ካርል ሄንዝ (ነፍስ ኄር) ጥረት የተቆፈሩ የጉድጓድ ውሃዎች ምንጮችንና ጅረቶችን ተክተው እያገለገሉ ይገኛሉ። (እኚህ በግብረ ሰናይ ተግባራቸው የሚታወቁ የአገር ባለውለታ ሀውልታቸው በአዲስ ዓለም ከተማ አደባባይ ቆሞ ይታያል)
የውሃ ችግር አሁንም ኢትዮጵያ ውስጥ በሰፊው እንዳለ በየመንገድ የሚታየው ጄሪካን አመላካች ነው። በከዘራና ወፍራም በትር/ ዱላ አስደግፎ የተሸከመ ሰውና ጄሪካን የተጫኑ አህዮች ማየትም የተለመደ ነው። ውሃ ቦኖ ጋር ተሰብስበው ወረፋ የሚጠብቁ ሰዎች ማኅበራዊ ትስስራቸውን በአጋጣሚው ሲያጠነክሩም መመልከት ይቻላል።
አለባበስን በተመለከተ ወንዱ አልፎ አልፎ ጣል አድርጎ ከሚታየው ኩታ በስተቀር ከከተማው ነዋሪ ሲነፃፀር፣ ንፅህናውና እርጅናው ነው እንጂ አለባበሱ እምብዛም የሚለየው ነገር የለም። እናቶች ግን ቀሚሳቸው ላይ የሚደርቡት ጋቢ የሚያክለው ኩታ ልዩ ያደርጋቸዋል። ወገባቸው ላይ ተጠምጥሞ በወፍራሙ ከታሰረው በተጨማሪ፣ ሌላ ኹለተኛ መልኩን የቀየረ ኩታ እህልም ሆነ ሌላ እቃቸውን አዝለውበት ይታያል።
የሸክሙ ብዛት አስጎንብሷቸው በረሃ መካከል ላይ በቡድን ሆነው ሲጓዙ የሚታዩት እናቶች መስቀለኛ አስረውት ይንከላወሳሉ። ያዘሉበትና የታጠቁት ኩታ ከአየሩ ፀባይ ጋር ተደምሮ ሙቀቱን እንዴት እንደሚችሉት ያስገርማል። እጃቸው በአብዛኛው ባዶውን ስለማይሆን የሚይዙትን ጥላ ክርናቸው ላይ አንጠልጥለው ማየት የተለመደ ቢሆንም ከወበቁም ሆነ ከፒስታው አቧራ የሚከላከልላቸው አይደለም።
ወደ ገጠር በተገባ ቁጥር የሸክማቸውን ክብደት መገንዘብ ከመቻሉ በላይ አሁንም እንደጥንቱ አህያ ያላትን ውለታ ከቦታው ተራራማነት አኳያ ለመረዳት ቀላል ነው። በበሬ ማረሱ ከተማ ውስጥና በአቅራቢያ አሁንም ድረስ በስፋት ስለሚታይ ልብ ብለው ካላስተዋሉት ላይገርም ይችላል። የሚታረስበት ሞፈሩና ቀንበሩ ቢያንስ ለእንስሳቱም ሆነ ለአራሹ ምቹ ተደርጎ እስካሁን ለማሻሻል አለመሞከሩ የጥንቱን የምናስታውስበት ተግባራዊ ሙዚየም እንዲሆን አድርጎታል።
ነዳጅን የሚጠቀም ትራክተርና ኮምባይነር መጠቀም ይቅርና በባህላዊ መንገድ የተመረተን በተሽከርካሪ የፈለጉበት አጓጉዞ ለገበያ ማቅረብም የሕልም ያህል እንደፈለጉት ማየት የሚቻል አይደለም።
ኢትዮጵያ ካለችበት ድህነት አኳያ ለነዳጅ የምታወጣው ወጪ በአንፃራዊነት ከፍተኛ እንደሆነ ግልጽ ነው። ከዋናዎቿ ዐስር ወጪዎቿ ተርታ የሚሰለፈው ይህ ሀብቷ ግን ለጥቂቶች መበልጸጊያ፣ ለተወሰኑ መተዳደሪያ፣ ለአንዳንዶች ደግሞ መንደላቀቂያ መሆኑ ይታመናል። ከአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ሀብት ላይ እየተቀነሰ በሚገኘው ነዳጅ አብዛኛው ድሃ ኢትዮጵያዊ ተጠቃሚ መሆን አለመቻሉ ደግሞ እጅግ በጣም ሆድ አስብሶ አንጀት ይበላል።
በአቅም ማነስ ሳቢያ መጠቀም የማይችሉት ከማሳዘናቸውም በላይ፣ ካላቸው ላይ ቆንጥረው እንጠቀም ቢሉ እንኳን በተሽከርካሪ እጦትም ይሁን በዋጋው መጋነን፣ አልያም በመንገድ እጦት እንደጥንቱ እግራቸውንና እንስሳትን መጠቀም ግዴታ የሆነባቸው የትየለሌ ናቸው።
መኪና ማለፉ ብርቅ ሆኖ ሕፃናትም ሆኑ ትልልቆች ሥራቸውን አቁመው እስኪያልፍ ቆመው የሚያዩበት የውስጥ ለውስጥ የገጠር ፒስታ መንገድ ብዙ ነው። ውሾች እየጮሁ የሚከተሉበት ቦታ መኖሩ ባይገርምም፣ አልፎ አልፎ ብቻ ከሚያልፉ ተሽከርካሪዎች በስተቀር መጓጓዣ ዝር በማይልባቸው የገጠር መንገዶች ድንገት መኪና የደረሰባቸው እንስሳቶች ሲደነብሩና ባለቤቶቻቸውም ለማስቆም ሲሯሯጡ ማየትም ምን ያህል ለከተማ ቅርብ ሆኖ በመጓጓዣ እጦት ምክንያት ሩቅ መሆን እንደሚቻል ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።
ጉዟችን በአብዛኛው ቱሪስትም ሆነ ማንኛውም መንገደኛ የሚጠቀምበት የተለመደ መንገድ ባለመሆኑ የሚታየው ነገር አጀብ የሚያስብል ነው። ከአዲስ ዓለም ወደ ሚዳ መራኛ የሚወስደው ፒስታ መንገድም እንደተራራማነቱ ልዩ ነው። ከከተማዋ ራቅ ብሎ ወደሚገኘው የሚዳው አቡነ መልከፃዲቅ ገዳም የሚወስደውም መንገድ በተመሳሳይ ውብ ዕይታ የተላበሰ ነው። ወደ ታሪካዊው የገዳሙ ዋሻ ለመድረስ መኪና አቁሞ ቁልቁል ከ800 በላይ እንደነገሩ የተሠሩ ደረጃዎችን መውረድ ግድ ይላል።
ርዝመታቸውና ከፍታቸው እንደገደላማነቱ የሚለያዩትን ደረጃዎች ጨርሰው ሲወርዱ የሚታየው የገዳሙ ዋሻ ከትልቅ ቋጥኝ ስር የሚገኝ ሲሆን፣ ምድሩ ድርቅ ባለ የላመ አፈር የተሞላ ነው። ከስሩ የበርካቶች አስከሬን ማረፊያ እንደሆነ የሚነገርለት ይህ ቦታ፣ አካል ሳይበሰብስ የሚቆይበት መሆኑ ዝነኛ አድርጎታል። በርካቶች ለፀበልም ይሁን ለመሳለም ቦታው የሚገኙ ሲሆን፣ ለጎብኚዎችም ተብሎ ከቤተክርስቲያኑ ሕንጻ በተጨማሪ ለሙዚየም የሚሆን ቤትም በዘመናዊ መልኩ ዋሻውን ታኮ ተገንብቷል።
በቦታው ያለሳጥን የተቀበረ አስከሬን ከተወሰነ መስመር ውስጥ ሳያልፍ የተቀበረ ከሆነ ለዘመናት እንደማይበሰብስ ይነገርለታል። ከተገባለት ቃልኪዳን በተጨማሪ ማረጋገጫ የሚሆኑ ያልበሰበሱ በርካታ አስከሬኖችም በሙዚየሙ ቆመው ይገኛሉ። በጀርባቸው አርፈው የመነሻ ቀናቸውን መጠባበቅ የነበረባቸውን ቅሪተ አካሎች ደርድሮ ማቆሙ ተገቢ ነው አይደለም የሚለውን እንተወውና፣ የቦታውን አስተማሪነት ማንሳት ግድ ይላል።
ለተመልካች ማስተማሪያነት እንዲሁም ምስክር እንዲሆኑ ተብለው ከአፈሩ ተለይተው ሲሚንቶ ላይ እንዲቆሙ መደረጋቸውን በተመለከተ፣ እንዳይበሰብሱ ከሚያደርጋቸው አፈር መለየቱ ተገቢ ነው ወይ? የሚለው ጥያቄ ምላሽ ይሻል። ሳጥን ውስጥ የተደረገ እንኳን ይበሰብሳል እየተባለ እየተነገረ፣ ከአፈሩ ለይቶ ቤት ውስጥ ማቆሙ ማስተማሪያነቱስ ምን ያህል ይዘልቃል፣ ዓላማውንስ አይስትም ወይ ብሎ መጠየቅ እንደሚገባ ልብ ሊባል ይገባል። ሀብቱም ሆነ ቃልኪዳኑ የአንድ አካባቢ ብቻ ባለመሆኑም እንደሌሎች ላሊበላን እንደመሳሰሉ ሀይማኖታዊ የጎብኚ መስህቦች አስፈላጊው ጥንቃቄ ሊደረግላቸው እንደሚገባ እንደ ተራ ተመልካች ሐሳብ ማስተላለፍም ግድ ይላል።
የገዳሙ ጉዟችንን አጠናቀን ለአዳር ወደ አቅራቢያዋ ሚዳ መራኛ ከተማ አምርተን ነበር። ከ11 ሰዓት ገደማ ጀምሮ ርችት እየተተኮሰ ወጣት ሠርገኛ የከተማዋ አውራ ጎዳና ላይ እየተመላለሰ ለሰዓታት ሲጨፍር ማየት እጅግ ልዩ ስሜት ይፈጥራል። አቧራውን በእርግጫ እያጨሱት ሲመላለሱ አለመድከማቸው ያስደንቃል። ከወጣት ውጭ ሌላ የሌለበት ይህ የሠርገኛ ቡድን ሆቴል ገብቶ ለ30 ደቂቃ ካረፈው ውጭ ያለማቋረጥ እስከ ሌሊቱ ስድስት ሰዓት በአካባቢው የዜማ ስልት ሲጨፍር ማየት ወደጦር ሜዳ ሊያመራ ይመስላል።
ያሆ እየተባለ ከድል ዘመቻ መልስ ጭፈራ ይመስል፣ እንዲህ ከማይደክም ወጣት ስብስብ ጋር አብሮ ውጊያ ቢገባ ራሱ እንደሚያኮሩ ወኔያቸው ያሳያል። ድግስ ይቅርና የጦር ዘመቻ አብሮ ለመሄድ የሚያስመኙት እነዚህ የመራኛ ወጣቶች፣ የተለያዩ ባህላዊም ሆኑ ዘመናዊ ዜማዎችን ከልባቸው እየዘፈኑ አጀባውን አሳምረውታል። በተለይ “መውዜር አማረኝ” የሚለውን ዘፈን እነሱ ያደጉበት እስኪመስል ከዋናው ዘፈን በላይ እንደራሳቸው አድርገው ውብ አድርገው ለረጅም ደቂቃ ሲጫወቱት ማየትም መስማትም ልብን ይሰርቃል። በዋና ዋና ከተሞች እንዲህ አይነት የማይደክም የሠርግ አጃቢ ይቅርና ለሌላም ነገር ተከፍሎት እንኳን እንደነሱ የሚበረታ ስለመኖሩም ያጠራጥራል።
ጉዟችን በዚህ አላለቀም። ቀጥሎ የደረስንበትን፣ ያየንና የሰማነውን እነግራችሁ ዘንድ በቀጥይ ክፍል እንገናኝ!
ቅጽ 4 ቁጥር 185 ግንቦት 13 2014



