የኢትዮ ኤርትራ ግንኙነት ከፓርላማ ጥያቄ ቀረበበት

0
1210

መንግሥት ግንኙነቱ በሚፈለገው ልክ አላደገም ብሏል

የኤርትራ እና የኢትዮጵያ ግንኙነት ተቋማዊነትና ዘላቂነት ላይ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና ከምክር ቤት አባላት ጥያቄ ቀረበበት።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የ2014 ዘጠኝ ወር ዕቅድ አፈጻጻም ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ግንቦት 9/2014 ባቀረበበት ወቅት፣ ስለ ኤርትራ እና ኢትዮጵያ አሁናዊ ግንኙነት ከምክር ቤት አባላትና ከውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጥያቄዎች ቀርበውለታል።

በኹለቱ አገሮች ግንኙነት ላይ ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጥያቄ ካቀረቡት የምክር ቤት አበላት መካከል ክርስቲያን ታደለ አንዱ ሲሆኑ፣ የምክር ቤት አባሉ በጥያቄያቸው ‹‹የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ግንኙነት መቼ ነው ማዕቀፍ ኖሮት ተቋማዊ የሚሆነው?›› ብለዋል። ይህን ጥያቄ ያነሱበትን ምክንያትም ሲያብራሩ ‹‹እኔ እስከ አሁን ባለኝ ግምገማ የኹለቱ አገራት ግንኙነት ግለሰባዊ ፍላጎት ላይ የተንጠለጠለ ሆኖ ስለሚታየኝ ነው›› ብለዋል።

የምክር ቤት አባሉ አክለውም ‹‹መቼ ነው ተቋማዊ የሚሆነው? መቼ ግልጽ የሆነ ማዕቀፍ ኖሮት ግልጽ የሆነ የሕዝብ መብቶች፣ ጥቅሞችና ፍላጎቶች፣ የኹለቱን አገራት ሕዝቦች ፍላጎት ባስከበረ መንገድ ነው የሚከናወነው? መቼ ነው ያን ግንኙነትስ ይሄ የተከበረው ምክር ቤት አፈጻጸሙን ለመገምገም አስቻይ ሁኔታ ቀርቦለት ዕቅዱን ማየት የሚችለው?›› ሲሉ ተደምጠዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የመሥሪያ ቤታቸውን የዘጠኝ ወር ሪፖርት ለምክር ቤቱ ላቀረቡት ለምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን በኢትዮ ኤርትራ ግንኙነት ቀጣይነት ላይ ማብራሪያ ጠይቋል። ከቋሚ ኮሚቴው ጥያቄ ‹‹የኹለቱ አገራት መልካም ግንኙነት በዘላቂነት ለማስቀጠል ምን እየተሠራ ነው?›› የሚል ሲሆን፣ በኢትዮጵያ በኩል ግንኙነቱን አጠናክሮ ለማስቀጠል በትኩረት እንደሚሠራ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።

ከምክር ቤት አበላትና ቋሚ ኮሚቴው ስለ ኹለቱ አገራት ግንኙነት ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት ደመቀ መኮንን፣ ‹‹የመጀመሪያው ትልቁ ነገር ከዚያ የመጠባበቅ መንገድ ወደ ሰላም ጎራ በር መከፈቱ ትልቅ እርምጃ ነው›› ያሉ ሲሆን፣ ይሁን እንጂ ‹‹ያ የተከፈተው የሰላም በር በሚፈለገው ልክና ሊኖረን ከሚገባው ትብብር አኳያ የሚፈለገውን ያህል አድጓል ብሎ መውሰድ አይቻልም›› ብለዋል።

ኹለቱ አገራት በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ፣ በወደብና በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቶች የየራሳቸው ዕቅድ ወጥቶላቸው በሚመለከታቸው አካላት የተጀመሩ ሥራዎች መኖራቸውን የጠቆሙት ደመቀ፣ ‹‹የተጀመረውን ሥራ ሰብሰብ አድርጎ እንደ ማንኛውም አገሮች ሕጋዊ መሆን ያለበትን፣ ወደዚያ ለመድረስ የሚያስችሉትን ሥራዎች አጠንክሮ መሥራትና የኹለታችንንም ጥቅም የሚያስከብሩ ሥራዎች በእጅጉ ይዘን መጓዝ አለብን።›› በማለት ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል።

ሚኒስትሩ አክለውም፣ ‹‹እዚህ አካባቢ የሚሻሙ ነገሮች ሌላ ቅደም ተከተል አጀንዳ የሚያመጡ ጉዳዮች አሉ፣ ያው የምናውቃቸው።›› ያሉ ሲሆን፣ ይሁን እንጂ ‹‹በየትኛውም መመዘኛ ግን ተቋማዊ በሆነና በየሚመለከታቸው አስፈጻሚ አካላት ሥርዓቱን ጠብቆ፣ ተሟልቶ ማዕቀፍ ሆኖ እንዲቀጥል ማድረግ ያስፈልጋል።›› ብለዋል።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ለምክር ቤቱ ባቀረበው ሪፖርት ከኤርትራ ጋር ስላለው ግንኙት በሰጠው ማብራሪያ ‹‹ከኤርትራ ጋር አሁን ያለው ግንኙነት በመልካም ሁኔታ ላይ የሚገኝ ነው።›› ያለ ሲሆን፣ የፖለቲካ ግንኙነቱን ወደ ጠንካራ የኢኮኖሚ ትብብር ለማሸጋገር ድንበር አካባቢ ንግድና የሰዎችን ዝውውር የሚያሳልጡ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች፣ የወደብ አጠቃቀም፣ የንግድ ልውውጥ፣ የጉምሩክና የኢሚግሬሽን የኹለቱን አገሮች ሕዝብ ተጠቃሚ ሊያደርጉ የሚችሉ የትብብር ማዕቀፎች ለማበጀት በትኩረት እየተሠራ መሆኑ ተመላክቷል።


ቅጽ 4 ቁጥር 185 ግንቦት 13 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here