በአማራ ክልል ከተቋረጡ 45 የመንገድ ፕሮጀክቶች 12 የሚደርሱት መጀመራቸው ተገለጸ

0
1715

በአማራ ክልል በጦርነቱ ምክንያት ተቋርጠው ከነበሩ 45 የመንገድ ፕሮጀክቶች ውስጥ ከ10 እስከ 12 ፕሮጀክቶች ዳግም ሥራ መጀመሩን የአማራ ገጠር መንገድ ኮንስትራክሽን ኤጀንሲ ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።

የተመረጡት መንገዶች ለክረምት እርዳታ አስፈላጊ የሆኑ እንዲሁም ለአገልግሎት አስፈላጊነታቸው ታይቶ እንደሆነ ኤጀንሲው ጠቁሟል። ባለፈው ዓመት ተጀምረው የቀጠሉ አልያም ተጀምረው ሊያልቁ ትንሽ የቀራቸው፣ በተለያየ የግንባታ አደረጃጀት ላይ ያሉ ስለመሆናቸውም ነው የተገለጸው።

የአማራ ገጠር መንገድ ኮንስትራክሽን ኤጀንሲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ጌትነት ዘውዱ፣ በበጀት ዓመቱ ሊገነቡ ታስበው የተቋረጡ መንገዶችን ለማስቀጠል ወደ ተሟላ ሥራ አልተገባም፤ ከኹለት ወር በፊት የተጀመረውም የባሱ ናቸው የተባሉትን ለማስቀጠል ነው ብለዋል። ሆኖም ስለመንገድ ፕሮጀክቶች አጠቃላይ በጀት እና ከዚህ በላይ ዝርዝር መረጃ ለመጥቀስ፣ ኃላፊው ለጊዜው የተደራጀ መረጃ የለም ማለታቸውን ተከትሎ ማካተት አልተቻለም።

በሌላ በኩል፣ በክልሉ ዞንን ከዞን እና ወረዳን ከወረዳ የሚያገናኙ ነባር የገጠር መንገዶችን በዘጠኝ ወራት ለመጠገን 3 ሺሕ 2 ኪሎ ሜትር ዕቅድ ተይዞ፣ ማሳካት የተቻለው የዕቅዱን 75 በመቶ ነው ብለዋል። ይህም ኹለት ሺሕ 264 ኪሎ ሜትር በላይ ነባር መንገዶችን የመጠገን ሥራ መሠራቱን አንስተው፣ ለዕቅዱ አለመሳካትም ቀደም ብሎ በሕወሓት ወረራ የተነሳ በክልሉ ተከስቶ የነበረውን ጦርነት እንደምክንያት አስቀምጠዋል።

በጦርነት ባልተያዙ የሰሜን ሸዋ፣ ጎንደርና ጎጃም አካባቢዎች የሚገኙ የጽሕፈት ቤት መኪኖች በጦርነቱ ወቅት የስንቅና ሎጂስቲክስ ማመላለሻ ሆነው እንደነበር ያነሱት ኃላፊው፣ መሣሪያዎችም ለዚያው አገልግሎት ውለው ነበር ነው ያሉት። በእኛ ግምገማ የተሠራውም ከፍተኛ የአፈጻጸም ውጤት ነው፣ የዘጠኝ ወር ዕቅዱም ክረምቱን የጨመረ ይሁን እንጂ በክረምት የጥገና ሥራ መሥራት ስለማይቻል የምንጀምረው ኅዳር ወር አካባቢ ነው በማለት አስረድተዋል።

በኤጀንሲው በኩል በ2014 አጠቃላይ በጀት ዓመት ሦስት ሺሕ 751 ኪሎ ሜትር ነባር ጠጠር መንገዶችን ለመጠገን ዕቅድ የተያዘ ስለመሆኑ ገልጸዋል። ለዚህም 264 ሚሊዮን 41 ሺሕ ብር በላይ በጀት መመደቡን እና ከዚህ ውስጥ 150 ሚሊዮን 89 ሺሕ ብር በላይ በዘጠኝ ወራት ወስጥ ጥቅም ላይ መዋሉን አመላክተዋል።

በአማራ ክልል የሚገነቡ መንገዶች ባለቤትነታቸው ለሦስት አካላት ሲሆን፣ አንዱ የፌዴራል ተቋም የሆነው የኢትዮጵያ መንገዶች የሚያስገነባቸው በአብዛኛው አስፓልት የሆኑ መንገዶች እና ሎሎች ጥቂት ጠጠር መንገዶችም አሉ ተብሏል። የአማራ ገጠር መንገድ ኮንስትራክሽን ኤጄንሲ እንዲሁ ስፋታቸው ሰባት ሜትር የሚሆን የጠጠር መንገዶችን እንደሚያስገነባ ለማወቅ ተችሏል።

በወረዳዎች ባለቤትነት የሚተዳደረው ኹሉን ዐቀፍ የገጠር መንገድ ተደራሽነት ፕሮግራም (ዩራፕ) እንዲሁ በክልሉ የሚገኙ ወረዳዎች የሚገነባቸው እና የሚጠግናቸው መንገዶች ስለመኖራቸውም ነው የተገለጸው።


ቅጽ 4 ቁጥር 186 ግንቦት 20 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here