የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ለሁሉም ዘርፍ የሚሆን የኢንቨስትመንት ማበረታቻ ደንብ መዘጋጀቱን ገለጸ።
በተዘጋጀው ደንብ በተለይ የቴክኖሎጂ ዘርፉን ለማሳደግና በዘርፉ የሚሰማሩ አካላትን ለማበረታታት በሚል ከግብር እና ከቀረጥ ነጻ የአሰራር ስርዓት መኖሩን ነው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ያመላከተው።
ባለፉት ዓመታት የነበረውም ይሁን አሁን ያለው የፋይናንስ ስርዓት፣ የፈጠራ ሥራና ቴክኖሎጂን ለመደገፍ አሰራር ያልነበረው በመሆኑ፣ ከዚህ በኋላ በዘርፉ ለሚሰማሩ ባለሀብቶችና ኢንተርፕራይዞች የማበረታቻ አሠራር ስርዓት መዘጋጀቱ ነው የታወቀው።
በመሆኑም፣ በሶፍትዌር ልማት፣ ዳታ ማዕከል ግንባታ፣ የምርምር ፈጠራና ማበልጸግ ሥራ እንዲሁም መሰል ተግባራት ላይ የሚሰማሩ አካላት የካፒታልና የግንባታ ዕቃዎችን በሚያስገቡበት ወቅት የማበረታቻው ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ለማወቅ ተችሏል።
በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የዲጅታል ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም ኃላፊ አብዮት ባዩ (ዶ/ር)፣ ደንቡ የተዘጋጀው በቅርቡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባካሄደው ስብስባ ሲሆን፣ በቅርቡም በህትመት ይወጣል ሲሉ ገልጸዋል።
ደንቡ የትኛው ዘርፍ ምን ማግኘት አለበት እንዲሁም እንዴት ነው የሚያገኘው የሚለውን በዝርዝር ይገልጻል ያሉት ኃላፊው፣ በተለይ በዲጂታል ኢኮኖሚው ላይ ከፍ ያለ ጠቀሜታ ያሳድራል ብለዋል።
በተጨማሪም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከተሰጡት ኃላፊነቶች አንዱ ፈንድ ማፈላለግ በመሆኑ፣ የማስጀመሪያና የኢኖቬሽን ፈንድ የተሰኘ አዋጅ ለማጽደቅ እየሠራ መሆኑን አንስተዋል። ከዚህ በፊት በውድድር መልክ የማስጀመሪያ ፈንድ ሲሰጥ እንደነበር ጠቅሰውም፣ ሆኖም ይህ እንደማሳያ ሲደረግ የቆየ በመሆኑ ጉዳዩ ሳይቆራረጥ ለልማት አስተዋጽኦ በሚያደርግበት መልኩ አሰራር ሊዘረጋለት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
በዚህም ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ከግሉ የቴክኖሎጂ ዘርፍ ጋር ውይይት እንደተደረገበትና ለመንግሥት እንደቀረበ ተናግረዋል።
ከ2004 ጀምሮ ሲሠራበት የነበረው የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ፖሊሲ በዚህ ዓመት በአዲስ መተካቱን ያነሱት ኃላፊው፣ መንግሥት የሕግ ማዕቀፎችን፣ መሠረተ ልማቶችንና ሌሎች ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታዎችን በማመቻቸት የግሉን ዘርፍ ወደ መሪነት ለማሸጋገር እየሠራ ነው ሲሉ ተደምጠዋል።
ሆኖም በተለይ በአይሲቲ ዘርፍ ለሚሰማሩ አካላት ከግብር እና ቀረጥ ነጻ የማበረታቻ ስርዓት ከማቅረብ በተጨማሪ፣ የኢኖቬሽን ሥነምህዳሩን ለማስፋት በሚደረግ እንቅስቃሴም በተለይ ለጀማሪ ተቋማት የፋይናንስ፣ የቴክኒክ፣ የመሥሪያ ቦታ እና መሰል ድጋፎች የሚያገኙበት የአሰራር ሥርዓት ይዘረጋል ነው የተባለው።
ውጤታማነታቸው የተረጋገጠና ወደ ምርትና አገልግሎት የተቀየሩ የቴክኖሎጂ ውጤቶች በመንግሥት የግዥ ሥርዓት ውስጥ እንዲታቀፉ ከማድረግ ባለፈም፣ ወደ ውጪ ለሚልኩ፣ የገቢ ምርትን ለሚተኩ እንዲሁም ወደ ሌሎች አገራት ለሚስፋፉ የቴክኖሎጂ ኢንተርፕራይዞች የማበረታቻ፤ የድጋፍ እና የክትትል አሠራሮች እንደሚዘረጉ ተጠቁሟል።
የቴክኖሎጂ ልማት ላይ ትኩረት የሚያደርጉ የምርምር ዩኒቶች (Technological research units) በማምረቻና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እንዲቋቋሙ፣ ለኢኖቬሽን ልማት ሥራዎች የግሉ ዘርፉ ከመንግሥት በቀጥታ የገንዘብ ድጋፍ የሚያገኝበት አሰራር ይዘረጋል ተብሏል።
የግሉ ዘርፍም በምርምር የታገዙ ምርትና አገልግሎቶች ላይ ትኩረቱን እንዲያደርግ ብሎም የአይሲቲ ዘርፉን የመቆጣጠር ኃላፊነት ወስዶ፣ የተዘጋጁ ፖሊሲዎችንም አብሮ እንዲከታተልና እንዲገመግም የሕግ ማዕቀፍ እየተዘጋጀለት መሆኑ ነው የተገለጸው።
ቅጽ 4 ቁጥር 186 ግንቦት 20 2014



