ማክሰኞ ሰኔ 7 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ2015 ራስ ገዝ ዩኒቨርስቲ እንደሚሆን ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ “ትውልድ በመገንባት የተሻለ ነገን መፍጠር” በሚል መሪ ሀሳብ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር እየመከረ ነው።
ውይይቱ የተጀመሩ የሪፎርም ሥራዎች ላይ የጋራ መግባባት መፍጠር፣ ሪፎርሙን ለማሳካት የቦርዱ ሚና ምን መሆን እንዳለበት ማስገንዘብ እንዲሁም በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ያሉ ችግሮችን ለይቶ በጋራ ለመስራት ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፊሰር ብርሃኑ ነጋ፤ ከሚቀጥለው የትምህርት ዘመን ጀምሮ በዩኒቨርስቲዎች የመስክ ልየታ በማድረግ፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማዊ ነፃነት መስጠት እና ለተመራቂ ተማሪዎች የመውጫ ፈተና ተግባራዊ እንደሚደረግ ገልጸዋል።
በተለይ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በአገሪቱ አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች እንደማይገነቡ የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ነገር ግን የትምህርት ልማት ዘርፉን ለማጠናከር ይሰራል ብለዋል።
አዲስ የተቋቋመው የቦርድ አባላት በዩኒቨርስቲዎች ያሉ ብልሹ አሰራሮችን መፈተሽ እንደሚገባቸውም ማሳሰባቸውን ኤ ኤም ኤን ዘግቧል።
በውይይቱ ከፍተኛ የትምህርት አመራሮች፣ በኹሉም ዩኒቨርሲቲዎች የተመደቡ አዲስ የቦርድ አባላት አመራሮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።




