መነሻ ገጽሕይወት እና ጥበብነገረ ጤናአዲስ ተስፋ በኤችአይቪ እና ቁንጭር በሽታ ለተጠቁ ሕሙማን

አዲስ ተስፋ በኤችአይቪ እና ቁንጭር በሽታ ለተጠቁ ሕሙማን

በተያዘው ሰኔ ወር መጀመሪያ ላይ ነበር፣ የዓለም ጤና ድርጅት በኤች አይ ቪ ኤድስና ቁንጭር (ካላዛር) በሽታዎች የተጠቁ ሕሙማንን ሕክምና ለማዘመንና ለማሻሻል የሚያስችል መመሪያን ይፋ ያደረገው። ይህም የዘመነ እና የተሻለ ውጤት ያስገኛል የተባለ የሕክምና መመሪያ፣ በኢትዮጵያ እንዲሁም በሕንድ የተሠሩ ጥናቶች መሠረት ማድረጉ ተጠቅሷል።

ጥናቶቹ የተሠሩት ትኩረት የተነፈጉ በሽታዎች ላይ በሚሠራው የዲኤንዲ ኢኒሺዬቲቭ (Drug for Neglected Diseases Initiative)፣ በዓለም ዐቀፉ ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን እና በሌሎች በጉዳዩ ላይ በሚሠሩ አጋር አካላት ትብብር ነው ተብሏል።

በኢትዮጵያ ይህ አዲስ የሕክምና መንገድ ወትሮ ከነበረው አንጻር የጎላ የውጤት ልዩነት እንደሚያመጣ ከወዲሁ ተገምቷል። ይህ እንዲባል ያስቻለው፤ በጥናቱ መሠረት እስከ አሁን አገልግሎት ላይ ያለው አካሄድ ውጤታማነቱ 55 በመቶ ብቻ መሆኑና፣ በአንጻሩ አዲሱ የሕክምና ስልት ሲጠናቀቅ (ማለትም ከ58 ቀናት በኋላ) 88 በመቶ ውጤታማ ይሆናል መባሉ ነው። በተመሳሳይ በሕንድ አገርም በተሠራው ጥናትም፣ 96 በመቶ ለሚሆኑ የጤና እክል ክስተቶች መልስ መስጠት መቻሉን ነው የተገለጸው።

‹‹በኤችአይቪ እና በቁንጭር በሽታ ለተጠቁ ሕሙማን በሚሰጥ ሕክምና የጤና መሻሻልን ማምጣት አዳጋች ነው። ይህንን ከግምት ስናስገባ፣ አሁን ላይ አስደናቂ ውጤት ማየት ችለናል። አዲሱ የዓለም ጤና ድርጅት መመሪያ በኹለቱም በሽታዎች የተጠቁ፣ መገለልና መድሎ የደረሰባቸውን እና በገቢ ማጣት እንዲሁም በተደጋጋሚ የበሽታ ማገርሸት የሚሰቃዩትን ታካሚዎች ሕይወት በእጅጉ የሚያሻሽል ጉልህ እርምጃ ነው።›› በማለት ያስረዱት፤ በዲ.ኤን.ዲ. ትኩረት የተነፈጉ የትሮፒካል በሽታዎች፣ የቁንጭር እና ማይሲቶማ ክላስተር ዳይሬክተር ናቸው።

በኤች አይ ቪ የተያዙ ሰዎች ለቁንጭር በሽታ የመጋለጥ እድላቸው ከ100 እስከ 2,300 እጥፍ ይደርሳል። ቁንጭር፤ በሳይንሳዊ መጠሪያው ‹ቪሰራል ሌሽማናይሲስ› ወይም በተለምዶ ‹ካላዛር› በመባል የሚታወቅ ሲሆን፣ ትኩረት የተነፈጉ የትሮፒካል በሽታዎች ውስጥ ይመደባል። የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴርም ‹ችላ የተባሉ የትሮፒካል በሽታዎች› ዝርዝር ውስጥ አካትቶ፣ ባላቸው ተጽእኖ መሠረት ቅድሚያ እሰጣቸዋለሁ ካላቸው በሽታዎች መካከል ይገኛል።

ቁንጭር በአሸዋ ዝንብ ንክሻ የሚተላለፍ በሽታ ሲሆን፤ ትኩሳት፣ የክብደት መቀነስ እና ከፍተኛ ድካም ያስከትላል። በቁንጭር በሽታ የተጠቃ ሰው በተገቢው ጊዜ ሕክምና ካልተደረገለትም ለሞት የመጋለጥ እድል አለው።

‹‹ብዙውን ጊዜ ከእነዚህ ኹለት በሽታዎች ጋር የሚኖሩ ሰዎችን ማከም አስቸጋሪ ነው። ምክንያቱም በሽታ የመቋቋም አቅማቸው የተዳከመ ስለሚሆን፣ ለመደበኛ ሕክምና አዎንታዊ ምላሽ አይሰጡም። እነዚህ ታካሚዎች በሕክምናው ወቅት ተደጋጋሚ እና የከፋ የጎንዮሽ ጉዳቶችን ያስተናግዳሉ። በጊዜ ሂደትም ለሚበረታ የቁንጭር ሕመም የመጋለጥ እና ከፍ ሲል የመሞት እድላቸው ይጨምራል። አሁን በዓለም ጤና ድርጅት መመሪያዎች ውስጥ የተካተተው አዲሱ የሕክምና ስርአት ታድያ ከቁንጭር በሽታ የመዳን እድላቸውን በእጅጉ ይጨምራል።›› ይላሉ፤ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የውስጥ ሕክምና ረዳት ፕሮፌሰርና በጥናቱ ዋና ተመራማሪ ዶክተር ረዚቃ መሐመድ።

በኢትዮጵያ ወቅት ጠብቀው ከቦታ ቦታ እየተንቀሳቀሱ የእርሻ ሥራን የሚሠሩና ለአሸዋ ዝንብ ንክሻ የተጋለጡ ወጣቶች፣ ለተጓዳኝ በሽታ ተጋላጭ ከሆኑ መካከል ተጠቃሽ ናቸው። ታድያ መደበኛው የሕክምና አሰጣጥ ካለው ዝቅተኛ ውጤት ባሻገር፣ እነዚህ ታካሚዎች በሽታው በተደጋጋሚ ያገረሽባቸዋል፣ ረጅም ጊዜን በጤና ተቋማት ለማሳለፍ ይገደዳሉ፣ ገቢያቸውን ስለሚያጡም ወደ ከፋ ድህነት የመውደቅ እድላቸው ሰፊ ነው።

እነዚህ ዜጎች በሥራ ባልደረቦቻቸው እና ማኅበረሰቡ አልፎ አልፎም በራሳቸው የቤተሰብ አባላት ጭምር መገለል ሊደርስባቸው ይችላል።
በሌላ በኩል ጥናቱ ባካተታት በሕንድ፣ የቢሃር ግዛት በአንዳንድ ወረዳዎች እስከ 20 በመቶ የሚደርሱ የቁንጭር በሽታ ተጠቂዎች በኤች አይ ቪ የተያዙ ናቸው። እነዚህ በተጓዳኝ ሕመም የተያዙ ታካሚዎች የቁንጭር በሽታ መክረሚያ ስለሚሆኑም፣ በሀገሪቱ ውስጥ ዘላቂ የሆነ በሽታውን የማስወገድ ጥረት እንዳይሳካ እንቅፋት ሆኗል።

ስለ አዲሱ የሕክምና ክትትል?
አሁን በትግበራ ላይ የሚገኘው የኤችአይቪ/ቁንጭር ተጓዳኝ ኢንፌክሽን መደበኛ ሕክምና፣ ‹ሊፕሶማል አምፎቴሪሲን ቢ› (LAmB) በተሰኘ የአንድ መርፌ ሕክምናን የያዘ ነው። አዲሱ የሕክምና ክትትል በአንጻሩ ሚልቴፎሲን (miltefosine) የተባለ በአፍ የሚወሰድ መድኃኒትን (ኪኒን) በመርፌው ላይ ያክላል። ይህም የተሻለ ውጤታማነት ማምጣት መቻሉን በኹለቱም አገራት (በኢትዮጵያ እና በሕንድ) ከተሠሩ ጥናቶች መረዳት ተችሏል።

‹‹ለመጀመሪያ ጊዜ የኤችአይቪ/ቁንጭር የጋራ ኢንፌክሽን ያለባቸው ታካሚዎች በጥናት ላይ የተመሠረተ ሕክምና ያገኛሉ። ይህም ታካሚዎች ከሕክምና አገልግሎትም ሆነ ከማኅበራዊ ተጽእኖ አንጻር በጣም የተጋለጡ መሆናቸውን ለመረዳት አንድ እርምጃ ነው። እንዲሁም እነሱን የምንይዝበት/የምንንከባከብበት መንገድ መሻሻሉ ሕሙማንን ብቻ ሳይሆን የሚጠቅመው ቁንጭርን የማስወገድ ፕሮግራምንም ያግዛል። ይህም ሆኖ ግን አሁንም ብዙ የሚቀሩ ሥራዎች አሉ። እነዚህ ታካሚዎች እጅግ ከፍተኛ የሆነ የቲቢ ስርጭትን ጨምሮ አጠቃላይ መፍትሄ የሚሹ በርካታ ውስብስብ የሕክምና ተግዳሮቶች አሉባቸው።›› ሲሉ በዓለም ዐቀፉ ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን የሕክምና አማካሪ እና የጥናቱ አስተባባሪ ዶክተር ሳኪብ ቡርዛ ተናግረዋል።

ሕንድ፣ ኢትዮጵያ እና ሌሎች ኹለቱ በሽታዎች ስር የሰደዱባቸው አገራት፣ የዓለም ጤና ድርጅት የሚመክረውን አዲሱን ሕክምና ለማካተት የራሳቸውን የሕክምና መመሪያ እንዲከልሱ ይጠበቃል ተብሏል።

‹‹ይህ አዲስ ሕክምና በመርፌ የሚወሰዱ መድኃኒቶችን መጠቀምን ስለሚቀንስ እና ለታካሚዎች የመዳን እድሎችን በእጅጉ ስለሚጨምር ታላቅ የምሥራች ነው። አዲሱ መመሪያ መድኃኒቱ የሚሰጥበትን ጊዜ በ14 ቀናት ውስጥ (ተከታታይ ያልሆነ) እንዲሆን ሲመክር፤ አስቀድሞ በ38 ቀናት የሚሰጥ ነበር። በዚህም ውጤት እጅግ ኩራት ይሰማናል።›› ሲሉ በህንድ የራጄንድራ መታሰቢያ የምርምር ተቋም ዳይሬክተር እና በጥናቱ ዋና ተመራማሪ ዶክተር ክሪሽና ፓንዲ ተናግረዋል።ከዚህም የተሻለ የሕክምና ዘዴ ለማምጣት ጥናቶች እንደሚቀጥሉም ተነግሯል።

‹‹አዲሱ ጥምር ሕክምና አሁንም ሚልተፎሲን የተባለው በአፍ የሚወሰድ መድኃኒት (ኪኒን) ላይ የተመረኮዘ ነው። ይህም በነፍሰ ጡር ሴቶች የጽንስ እድገት ላይ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። በተመሳሳይ ለዚሁ ሕክምና የሚውለው የሊፖሶማል አምፎቴሪሲን ቢ፣ ፈሳሽ መድኃኒት ለአወሳሰድ አስቸጋሪ እና ሆስፒታል መተኛት እና ክትትል ማድረግ የሚጠይቅ ነው። ረጅም ጊዜ የሚወስድ የሆስፒታል ቆይታ ወይም ተደጋጋሚ የሆነና በአንቡላንስ የታገዘ ተመላላሽ የሕክምና ክትትል ደግሞ ታካሚውንም ሆነ ተንከባካቢውን ለከፍተኛ ወጪ ሊዳርግ የሚችል ነው።” ያሉት ደግሞ መቀመጫውን ኬንያ ናይሮቢ ያደረገው የዲኤንዲ የምሥራቅ አፍሪካ ክልላዊ ጽሕፈት ቤት ዳይሬክተር ዶክተር ሞኒኬ ዋሱና ናቸው።
በቁንጭር በሽታ የተያዙ ታካሚዎች አሁንም የተሻሻለ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ እና ፈዋሽ ሕክምና ያስፈልጋቸዋል። ለዚህም ነው ዲኤንዲ እና አጋሮቹ ሙሉ በሙሉ በአፍ የሚወሰድ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ እና ውጤታማ የሆነ በመጀመሪያ ደረጃ ባሉ የጤና ተቋማት ጭምር ለሁሉም የቁንጭር በሽታ ሕሙማን ሊሰጥ የሚችል ሕክምና ለማስገኘት እየተጋ ያለው።

ኢትዮጵያ በቁንጭር በሽታ ምክንያት የሚከሰት የሞት መጠንን ከ3 በመቶ በታች ለማድረስ እየሰራች ትገኛለች።
በኢትዮጵያ የተደረገው የተሻሻለ የቁንጭር ሕክምና ክሊኒካዊ ጥናት በአውሮፓ ኅብረት ሰባተኛ ማዕቀፍ ፕሮግራም (European Union Seventh Framework Programme)፣ በጀርመን የፌዴራል የትምህርት እና ጥናት ሚኒስቴር፣ በኔዘርላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ በስፔን የዓለም ዐቀፍ ልማትና ትብብር ኤጀንሲ፣ በብሪታንያ መንግሥት ተራድኦ ድርጅት (UK Aid)፣ በስዊዘርላንድ የልማትና ትብብር ኤጀንሲ፣ በዓለም ዐቀፉ ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን እና በሜዲኮር ፋውንዴሽን በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የተካሄደ ነው።

እንዲሁም፣ ዲኤንዲ በአውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በ2003 ለትርፍ ያልተቋቋመ የምርምር እና ልማት ድርጅት ሲሆን፣ ትኩረት ለተነፈጉ ታካሚዎች፣ እንቅልፍ ሕመም (አፍሪካዊ ትራይፓኖሶሚሲስ)፣ በቁንጭር፣ በፋይላር ኢንፌክሽን፣ ማይሴቶማና ሄፓታይተስ ሲ ለሚሰቃዩ፣ እንዲሁም በኤችአይቪ ለተጠቁ ሕፃናት የተሻሻሉ ሕክምናዎችን ለማቅረብ ይሠራል። በአፍሪካ ከቀላል እስከ መካከለኛ ለሆኑ የኮቪድ-19 ጉዳዮች ሕክምና ለማግኘት የጸረ-ኮቪድ ክሊኒካዊ ሙከራን በማስተባበር ላይም ይገኛል።


- ይከተሉን -Social Media

ቅጽ 4 ቁጥር 189 ሰኔ 11 2014

ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች