ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለለኝ በፖሊሶች ደብደባ እንደተፈፀመበት ወንድሙ ታሪኩ ደሳለኝ ገለፀ

0
945

ሐሙስ ግንቦት 25 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ዛሬ ግንቦት 25 ቀን 2014 አዲስ አበባ ፖሊስ በተለምዶ 3ተኛ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለለኝን ለመጠየቅ መገኘቱን የገለፀው ወንድሙ ታሪኩ ደሳለኝ ጋዜጠኛ ተመስገን በፖሊሶች ተደብድቦ የግራ ዓይኑ ሥር አብጦና የለበሰው ቲ-ሸርት ተቀዶ እንዳገኘው በማህበራዊ የትስስር ገፁ ባሰፈረው መልዕክት አስታውቋል።

“በዚህ እስር ቤት በታሳሪና በጠያቂ መካከል በኹለት ሾቦ የተጋረደ ከ10 ሜትር የሚበልጥ ርቀት አለ” ያለው ታሪኩ “በታሳሪና በጣያቂ መካከል ባለው ርቀት የተነሳ፣ ንግግር ለማድረግ እጅግ አዳጋች ነው። አጠቃላይ ነገሩ መጯጯህ ነው” ሲል ገልጿል።

ጋዜጠኛ ተመስገን ከዚህ በፊት በእስር ቤት እያለ ባጋጠመው በጆሮ ህምም ምክንያት በዚህ ግር ግር ውስጥ ጆሮው ለመስማት እንደሚያዳግተው የገለፀው ወንድሙ፤ ይሄ በመሆኑ ተመስገን ለፖሊሶቹ “ትንሽ ቀረብ ብሎ ቢያወራኝ” ሲለው ፖሊሱ በእጁ የማመናጨቅ ምልክት እንዳሳየውና ተመስገንም ድጋሜ ለማስረዳት ሲሞክር አንዱ ፖሊስ ከነበረበት ከጠያቂ ቦታ ሌላው ፓሊስ ከእስረኞቹ መቆሚያ ደረጃ ላይ በመውረድ ለኹለት ተመስገንን አብረውት ከቆሙት እስረኞች መካከል ጎትተው በማውጣት በቦክስ፣ በጫማ ጥፊ ለኹለት እንደበደቡት ተናግሯል።

”ይህ ሲሆን የሌሎች እስረኛ ጠያቂ ቤተሰቦችና እስረኞችም አይተዋል። ድብደባውን እየፈፀሙ ወደ እስረኛ ክፍል ሳይሆን ወደ ሌላ ቦታ ይዘውት ሄደዋል።“ ሲልም ታሪኩ አክሏል።

ከቆይታ በኃላ በቢሮ ውስጥ ጋዜጠኛ ተመስገንን እንዳገኘው የገለፀው ወንድሙ፤ “የግራ ዓይኑ ሥር አብጦ የለበሰው ቲ-ሸርት ተቀዶ አግኝተነዋል። አሁን ከእስር ቤቱ አስወጥተውኝ በሩ ላይ እገኛለሁ።” ሲልም ስለነበረው ሁኔታ አስረድቷል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here