‹‹ጋዜጠኞች ከሥራቸው ጋር በተያያዘ ክስ ከመቅረቡ በፊት ለእርስ በእርስ የቁጥጥር ሥርዓት ሊቀርቡ ይገባል››:- የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት

0
1214

ሐሙስ ግንቦት 25 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ጋዜጠኞች ከሥራቸው ጋር በተያያዘ ክስ ከመቅረቡ በፊት ለእርስ በእርስ የቁጥጥር ሥርዓት ሊቀርቡ ይገባል ሲል የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት አሳሰበ።

ሰሞኑን የኢትዮጵያ መንግስት በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ላይ የሚሰሩ 18 ያህል ጋዜጠኞችን ህግ ከማስከበር እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ሥር በማድረጉ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለ እንደሚገኝ ምክር ቤቱ ለአዲስ ማለዳ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

መንግስት በቁጥጥር ሥር ያዋላቸን ጋዜጠኞች አንዳንዶቹን ህጉ በሚፈቅደው መሠረት ፍርድ ቤት ቀርበው የጊዜ ቀጠሮ የተሰጣቸው ቢሆንም፤ አሁንም ፍርድ ቤት ያልቀረቡና የታሰሩበት ቦታ የማይታወቁ ጋዜጠኞች መኖራቸው ምክር ቤቱን እንዳሳሰበውም በመግለጫው ገልጿል።

በቅርቡ የፀደቀውና ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የመገናኛ ብዙኀን አዋጁም ሆነ የኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ ጋዜጠኞች ከሥራቸው ጋር በተያያዘ ከፍርድ ቤት መደበኛ ክስ በፊት እንዳይታሰሩ ይከለክላል! ያለው ምክር ቤቱ፤ ጋዜጠኝነት ሥራቸው ጋር በተያያዘ የፈጸሙት የህግ ጥሰትም ሆነ የሥነ ምግባር ግድፈት ካለ በመገናኛ ብዙሃን ፖሊሲውም ሆነ በአዋጁ እውቅና ለተሰጠው የእርስ በእርስ ቁጥጥር ሥርዓት ተግባራዊ ማድረጊያ አማራጭ ዘዴ ሊቀርቡና ሊዳኙ ይገባል ብሏል።

ነገር ግን ጋዜጠኞችን አስሮ የምርመራ ጊዜ መጠየቅ በህገ መንግስቱ እውቅና ያገኘውን ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን ይጋፋል ብሎ እንደሚያምንም የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት አስታውቋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በቁጥጥር ሥር የዋሉት ጋዜጠኞች በህግ ከተደነገገው በተቃራኒ መያዛቸው፤ በቅድመ-ፍርድ ጊዜ ለረጅም ቀናት ያለ ክስ ታስረው መቆየታቸው፣ የታሳሪዎችን አድራሻ መደበቅ እና በቤተሰብና የህግ ባለሙያ እንድይጎበኙ መከልከል እንዲሁም መደበኛ ባልሆኑ እስር ቤቶች ማሰር የመገናኛ ብዙኀን አዋጁን የሚፃረር ተግባር በመሆኑም ጋዜጠኞቹ የታሰሩት ከመገናኛ ብዙሃን ሥራቸው ጋር በተያያዘ ከሆነ ክሱም ሊቀርብባቸው የሚገባው በመገናኛ ብዙሃን አዋጁ መሠረት በመሆኑ ጋዜጠኞቹ ከእስር ተለቀው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ሲልም ምክር ቤቱ ጠይቋል፡፡

ምክር ቤቱ ጋዜጠኞች በሰሯቸው ሥራዎች ሀላፊነት መውሰድ እንዳለባቸውና መጠየቅ እንደሚገባቸው እንደሚያምን የገለፀ ሲሆን፤ ሆኖም ከህገ መንግስትቱ ጀምሮ እውቅና ያገኘው ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን እንዳይጋፋ ህግና ሥርዓትን በተከተለ መልኩ እንዲሆን በአፅንኦት አሳስቧል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት በመገናኛ ብዙሃን አማካኝነት የተላለፉ ዜናዎች፣ ፕሮግራሞችና ማስታወቂያዎች ላይ ከመንግስት ከግለሰቦችና ከተቋማት የሚቀርቡ ቅሬታዎችን ተቀብሎ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተወጣጥተው ባቋቋመው የግልግል ዳኝነት አካል ውሳኔ የሚያሰጥበትን ሥርዓት ተግባራዊ ማድረግ የጀመረ መሆኑን በመግለፅ፤ መንግስትም ሆነ ሌላ አካል አቤቱታውን ከክስና እስር በፊት ለምክር ቤቱ እንዲያቀርብም ጥሪውን አቅርቧል።

ጋዜጠኞችን ከእስር በፊት ለምክር ቤቱ የእርስ በእርስ ቁጥጥር ሥርዓት ማቅረብ ያለመንግስት ጣልቃ ገብነት ስህተቶች እየታረሙ እንዲሄዱ እድል የሚሰጥ መሆኑን የገለፀው ምክር ቤቱ፤ የፍርድ ቤቶችን ውድ ጊዜ እንዳይባክን ከማድረጉም በተጨማሪ ከፕሬስ ሥራ ጋር ተያይዞ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለመንግስት የሚሰጠውን አሉታዊ ምስል ያስወግዳል ብሎ እንደሚያምንም በመግለጫው አስታውቋል።

መገናኛ ብዙሃንና ጋዜጠኞች ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ መምጣት ጀምሮ እስከ ህልውና ዘመቻውና ህግ የማስከበር እንቅስቃሴው ድረስ ዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶችን በየተቋሞቻቸውን እያስተናገዱ እንደሆነ ምክር ቤቱ እንደሚገነዘብም በመግለፅ በመሆኑም የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ችግሮቹን ለመፍታት በመጣር ላይ መሆኑንም ገልጿል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት በሥነ ምግባር የታነፀ በሃላፊነት ስሜት ህዝብን የሚያገለግል ሚዲያ በአገራችን እንዲጎለብት የሚሰራ ሲሆን፤ ከ60 በላይ የመንግስትና በግል መገናኛ ብዙሃንን እንዲሁም የጋዜጠኞች የሙያ ማህበራትን በአባልነት ያቀፈ ተቋም ነው፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here