“ኢትዮጵያ ሰብዓዊ ዕርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች ያለማሰለስ ዕርዳታውን እያደረሰች ነው።“:-አፈ-ጉባዔ ታገሠ ጫፎ

0
660

ሐሙስ ግንቦት 25 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ታገሠ ጫፎ ኢትዮጵያ ሰብዓዊ ዕርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች ያለማሰለስ ዕርዳታውን እያደረሰች መሆኗን አስገነዘቡ።

አፈ-ጉባዔ ታገሠ ጫፎ ከአሜሪካ የሕዝብ ተወካይ ትሬንት ኬሊ ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም በተለያዩ መንስዔዎች ለችግር የተጋለጡ ወገኖች አስፈላጊው ድጋፍ እንዲደረግላቸው መንግስት በያዘው በጎ አቋም የተነሳ፣ በአስቸጋሪ ኹኔታዎችም ቢሆን ዕርዳታ የማቀበሉ ነገር ቀጥሏል ብለዋል።

ከዚህም ባሻገር ሰብዓዊ መብቶች ሲጣሱ ተገቢው ክትትል እና ማጣራት ተደርጎ የሕግ ተጠያቂነት እየሰፈነ መሆኑንም አያይዘው አብራርተዋል። የሕግ ከለላ የሚያስፈልጋቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች ሁሉ ተገቢውን ጥበቃ እንዲያገኙ በመንግስት በኩል ባለው ተነሳሽነት የተነሳ፤ ሕግ የማስከበሩ ሥራም ትኩረት እንዳልተነፈገው ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ውስጣዊ ሰላሟን እና አንድነቷን በተሻለ ኹኔታ ጠብቃ ለማቆየትም አገራዊ የምክክር ኮሚሽን በቅርቡ መመሥረቷን አፈ-ጉባዔ ታገሠ አስረድተዋል።

ትሬንት ኬሊ በበኩላቸው፤ መልካም የሆኑት ጅማሬዎች ኹሉ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ያላቸውን ፍላጎት አስታውቀዋል። ኢትዮጵያ ተቀብላ ያጸደቀቻቸው ዓለም-አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሥምምነቶች እና ሕግጋት በሙሉ መከበራቸውን መንግስት እንደሚያረጋግጥ ያላቸውን ዕምነት ገልጸዋል።

አፈ-ጉባዔ ታገሠ ጫፎ ከአሜሪካው የሕዝብ ተወካይ ጋር ያካሄዱት ውይይት፤ በኹለቱ አገራት የቆየ ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት እና በጋራ ጉዳዮችም ላይ ያተኮረ እንደነበርም የምክር ቤቱ መረጃ አመላክቷል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here