ሸኔና የጋምቤላ ነፃነት ግንባር (ጋነግ) በፈፀሙት ጥቃት የኹለት ሰዎች ህይወት ሲያልፍ ሦስት ሠዎችን ታፍነው መወሰዳቸው ተገለፀ

0
911

ሐሙስ ግንቦት 25 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በጋምቤላ ወረዳ ጎሊ በሚባል አካባቢ ሸኔና የጋምቤላ ነፃነት ግንባር (ጋነግ) ብሎ የሚጠራው ቡድን በፈፀሙት ጥቃት የኹለት ሰዎች ህይወት ሲያልፍ ሦስት ሠዎችን ደግሞ አፍነው መውሰዳቸውን የክልሉ መንግስት አስታወቀ።

የጋምቤላ ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኡገቱ አዲንግ እንዳሉት፤ ትናንት ከቀኑ 10 ሰዓት ገደማ በጋምቤላ ወረዳ ጎሊ በሚባል አካባቢ በእርሻ ሥራ ላይ የነበሩ የኹለት ሰዎች ህይወት ሲያልፍ ሦስት ሠዎች ታፍነው ተወስደዋል።

ኃላፊው ሟቾቹ አንድ ወንድና አንድ ሴት መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ታፍነው የተወሰዱትም ኹለት ወንድና አንድ ሴት እንደሆኑ አስታውቀዋል።

ጥቃቱን ያደረሱት ራሱን የጋምቤላ ነፃነት ግንባር (ጋነግ) ብሎ የሚጠራው ቡድን ከህወሓት ተላላኪው ከሸኔ ጋር በማበር እንደሆነ አስረድተዋል።

ጥቃቱ ቡድኖቹ ለዘመናት በህዝቦች መካከል የነበረውን ወንድማማችነትና ሠላም በማደፍረስ ግጭት ለመፍጠር ያደረጉት ጥረት እንደሆነ ጠቅሰው ከዚህ ቀደምም ተመሳሳይ ሙከራ አድርገው እንዳልተሳካላቸው አመልክተዋል።

በመሆኑም ህብረተሰቡ ከዚህ በፊት የጀመራቸውን የአብሮነትና የሠላም እሴት አጠናክሮ በማስቀጠል ለክልሉ ዘላቂ ሠላምና ልማት የበኩሉን ሊወጣ ይገባል ሲሉ ኡገቱ ማሳሰባቸውን ከጋምቤላ ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።

የመንግስት ሀይል ጥቃት አድራሾቹ ላይ እርምጃ ለመውሰድ የተጠናከረ ክትትል እያደረጉ እንደሚገኝ ጠቁመው ህብረተሰቡ ተገቢውን ትብብር እንዲያደርግም ኃላፊው ጠይቀዋል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here