እስከ ግንቦት ወር አጋማሽ ድረስ በሰባት የአፍሪካ አገራት ውስጥ በአጠቃላይ 1 ሺሕ 400 የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ ክስተት መመዝገቡን የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ።
የበሽታው ክስተት የተመዘገበባቸው አገራት ካሜሩን፣ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ዲሞክራቲክ ኮንጎ፣ ላይቤሪያ፣ ናይጄሪያ፣ ኮንጎ ብራዛቪል እና ሴራሊዮን ናቸው፡፡ ከአጠቃላይ ቁጥሩ 1 ሺሕ 392ቱ በቫይረሱ የተጠረጠሩ እና 44ቱ ደግሞ በበሽታው መያዛቸው የተረጋገጠ ነው ተብሏል።
ድርጅቱ እንደገለጸው፣ ቫይረሱ ቀደም ሲል ከተከሰተባቸው አገራት ውጪ ያልተስፋፋ ቢሆንም፣ በቅርብ ዓመታት ውስጥ ግን በሽታው የሚታይበት መልክዓ ምድራዊ አካባቢ እየሰፋ ይገኛል።
በሽታው ከዚህ በፊት ታይቶባቸው በማይታወቁት አገራት ውስጥ መከሰቱ እንዲሁም ቫይረሱ ወደታየባቸው አገራት ያልተጓዙ ሰዎች ላይ በሽታው መገኘቱ አጠያያቂ ሆኗል ነው የተባለው።
ስለዚህም የዓለም ጤና ድርጅት አጠቃላዩን የቫይረሱን ሁኔታና በዓለም ዙሪያ የመከሰቱን ምክንያት ለማወቅ ከአጋሮቹ ጋር እየሠራ መሆኑን ገልጿል።
የዓለም ጤና ድርጅት የተጠናከረ የበሽታ ቅኝት፣ በሽታው አሁን የደረሰበት ደረጃ በዝርዝር የመረዳት እንዲሁም የበለጠ የሚስፋፋም ከሆነ ለመቆጣጠር ዝግጁ በመሆን አገራት የጋራ ምላሽ እንዲሰጡ ጥሪ አቅርቧል።
ለበሽታው ምላሽ በመስጠት በኩል አሁን በስፋት በሽታው ለተከሰተባቸው ምዕራባውያን አገራት እንዲሁም ለአፍሪካ ተብሎ ተለይቶ ኹለት የተለያየ እርምጃ የመውሰድ ሁኔታ እንዳይኖር ማድረግ አለብን ሲል የአፍሪካ አካባቢ የዓለም ጤና ድርጅት ተወካይ አስገንዝቧል፡፡
የዝንጀሮ ፈንጣጣ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1970 በአፍሪካ ውስጥ ሲሆን፣ አብዛኛው የበሽታው ክስተት የተመዘገበው በገጠራማ እና ጥቅጥቅ ደን ባላባቸው አካባቢዎች ነበር።
ቅጽ 4 ቁጥር 187 ግንቦት 27 2014


