መነሻ ገጽአንደበት‹‹አቅም ያላችሁ ሴቶች ወደኋላ አታፈግፍጉ፤ እድሎችን ተጠቀሙ›› ኢየሩሳሌም ሰለሞን የትምራን ሥራ አስኪያጅ

‹‹አቅም ያላችሁ ሴቶች ወደኋላ አታፈግፍጉ፤ እድሎችን ተጠቀሙ›› ኢየሩሳሌም ሰለሞን የትምራን ሥራ አስኪያጅ

‹‹ወደ ሴቶች የእኩልነትና የመብት ጉዳይ ያመጣኝ በቅርብ የማውቀው የቤተሰብ ሁኔታ ነው›› ይላሉ። ነገር ግን ጉዳዩን በቅርበት ለመከታተል መነሻ ከሆናቸው ምክንያት ይልቅ በዛው እንዲቆዩ ያደረጋቸው ምክንያት ብዙ እንደሆነ ነው የሚናገሩት፤ ኢየሩሳሌም ሰሎሞን።
ኢየሩሳሌም የሕግ ባለሞያ ናቸው። ከዚህ ቀደም በመምህርነት ያገለገሉ ሲሆን፣ አብዛኛውን የሕግ ልምምዳቸው ግን ከሴቶችን መብት ጋር በተገናኘ የሕግ አገልግሎት መስጠት ነው። ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሞያ ሴቶች ማኅበር ከጀማሪ የሕግ ባለሞያነት እስከ ተጠባባቂ ሥራ አስፈጻሚነት ደረጃ ድረስ አገልግለዋል። በተለያዩ ተቋማትም በተመሳሳይ ዓላማ የሠሩ ሲሆን፣ አሁን ያገኘናቸው ደግሞ ከ‹ትምራን› ጋር ነው።

ትምራን የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ እና አመራርነት ላይ በማተኮር የምትሠራ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት ናት። ከተመሠረተች ኹለት ዓመታትን አስቆጥራለች። መሥራቾቿ ደግሞ በቁጥራቸው ዘጠኝ የሆኑና በተለያየ መስክ ተሰማርተው ያሉ ብርቱ ሴቶች ናቸው። ትምራን በቅርቡ ባለው የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ላይ ሴቶች ትርጉም ባለው መልኩ እንዲወከሉና እንዲያገለግሉ ለማስቻል ጥረት ስታደርግ ነበር፤ እያደረገችም ትገኛለች።

ኢየሩሳሌም ታድያ ትምራንን በሥራ አስኪያጅነት እየመሩ ይገኛሉ። እናም የትምራንን አሁናዊ እንቅስቃሴ፣ ከምክክር ኮሚሽኑ ጋር በተገናኘ ያለውን ሁኔታ እንዲሁም አጠቃላይ የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎና አመራርነት በሚመለከት ከአዲስ ማለዳዋ ሊድያ ተስፋዬ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርገዋል።

በሴቶች ጉዳይ ላይ የሚሠሩ ብዙ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አሉ። ትምራን በምን ዓላማና ምን ለመሥራት ነው የተመሠረተችው?
እንደሚታወቀው በአገራችን በአመራርነት ላይ ያሉ ሴቶች ቁጥር አናሳ ነው። አሁን የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች ቢኖሩምና ሴቶች ወደ ከፍተኛ አመራርት እየመጡ ቢሆንም፣ አሁንም ታች ወረዳ እና ክልል ያሉትን ስንመለከት፣ የሴት አመራሮች ቁጥር አናሳ ነው።
ሴቶች አመራር ላይ ሲሆኑ ነው አሁን በአገራችን የምናነሳቸው ችግሮች ሊቀረፉ የሚችሉት የሚል እምነት በመኖሩ ነው ትምራን የተመሠረተችው። ለምሳሌ ጾታዊ ጥቃት፣ ድብደባ፣ ዛቻ እና የመሳሰለውን ብናነሳ፣ ይህ ሊቆም የሚችለው አንደኛ ሴቶች በብቃት አመራር ደረጃ ላይ ሆነው፣ ያንን የሚከላከል ሕግ ማውጣትና ሕጉ በተግባር መሬት ላይ እንዲወርድና ውሳኔ እንዲሰጥበት ማድረግ ሲችሉ ነው። የዛኔ አጥፊው ሲቀጣ፣ ሌሎች ደግሞ ትምህርት ያገኛሉ።

ስለዚህ ይህን ለማስቀረት፣ ሴቶች ላይ የሚደርሱ ችግሮችን ለመቅረፍ ሴቶች ወደ አመራርነት መምጣት አለባቸው። በዛ ላይ መብታቸውን መለማመድ አለባቸው። ሴት ልጅ ሰው ናት። ሰው ያለው መብት ሁሉ አላት። ስለዚህ እንደ ሰው መሪ ሆና አገሯን ማገልገል ይኖርባታል።
በዛ ላይ ሴቶች ወደ ሥልጣንና ወደ አመራርነት በመጡ ቁጥር አገራችን ላይ የምናያቸው ብዙ ችግሮች የሚቀረፉበት ሁኔታ የላቀ ነው የሚሆነው። በዓለማቀፍ ደረጃ ያሉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ ሴቶች ወደ አመራርነት ሲመጡ ሰላማዊ በሆነ መንገድ የሰውን ችግር የመቀረፍና ሰላም የመስፈን እድሉ ሰፊ ነው። ሴቶች በሰላም ማስፈጽም እንቅስቃሴ ላይ ግንባር ቀደም ሚና ሲወስዱ፣ ሰላም የመስፈን እድሉ ከፍተኛ ነው የሚሆነው። እና ይህንን በማሰብ የሴቷ ወደ አመራርነት መምጣት ለአገራችንም ለሴቷም እጅግ ጠቃሚ መሆኑን በማሰብ ነው ትምራን የተቋቋመችው።

አሁን ላይ አነሰም በዛ በኢትዮጵያ ሴት አመራሮች አሉ። የተባለውን ዓይነት ውጤት ሊያስገኝ የሚችል ምን ተስፋን በእነዚህ አመራር ላይ ባሉ ሴቶች ዐይታችኋል?
እሱን ለመመለስ በእርግጥ ጥናት ማድረግ ያስፈልጋል። አሁን እንዲህ ነው ብዬ ልነግርሽ የምችለው ነገር የለም። ግን የምናያቸው ነገሮች አሉ። ለምሳሌ በፕሬዝዳንት ደረጃ ሴት ናቸው አመራራችን። ሴቶች ጉዳይ ላይ ለመሥራት ብዙ ፍላጎት፣ ተነሳሽነት ያላቸውና እየሠሩም ያሉ ናቸው። የእርሳቸውን አረአያነት ሌሎች ከታች ያሉ አመራሮችም ሆነ ተማሪዎች እንዲከተሉ ለማድረግ ብዙ ጥረት እያደረጉ ነው። ይህ የምናየው ነው።

ሌላው ደግሞ እንዳልኩት ጥናት ያስፈልጋል፤ ማነጻጸር ያስፈልጋል። በፊት በነበረው አመራር የነበረው ስኬት ምንድን ነው፣ አሁን ሴቷ ስትሆን የተቀየረው ምንድን ነው የሚለውን ማየት ያስፈልጋል።

ግን ደግሞ ማኅበረሰባችን ጋር አንድ ችግር አለ። ሴት ልጅ ወደ ሥልጣንና አመራርነት ስትመጣ ውድቀቷን የምንጠብቅ ነው የሚመስለው። ሁሉም ዐይኖች እርሷ ላይ ነው የሚሆኑት። ከዚህ ቀደም ሀምሳ በመቶ ካቢኔ አባላት ሴቶች በሆኑበት ወቅት፣ እነዚህን ሴቶች ሰብስቦ ጥሩ ውጤት ሊኖር ነው ወይ የሚል ስጋት ነበር። ሁሉም ዐይኖች እነርሱ ላይ ነበሩ። ወንድ ቢሆን ኖሮ በዛ ቦታ የተሾመው የማይባለው ሁሉ ሴቶቹ ላይ ይባል ነበር።

ሴት ስትሆን ሁልጊዜ በችሎታዋ ነው የሚል ሐሳብ የለም። ግን ደግሞ ቦታቸውን አስጠብቀው ጥሩ ሥራ እየሠሩ የቀጠሉ የካቢኔ አባላት አሉ። በዛው ልክ ደግሞ አጥጋቢ የሆነ ውጤት ያላስገኙ ብለን የምናስባቸው ወንድ የካቢኔ አባላት ሊኖሩ ይችላሉ። ወንድ ሲሆን ሰው ነው፣ ሲሳሳትም ‹ሰው ይሳሳታል!› ነው የሚባለው። ሴት ስትሆን ግን ችሎታና አቅም ስለሌላት የሚባል ነገር አለ።

ሴቶች በምክክር ኮሚሽን ውስጥ ቁጥራቸው ማነሱ ቅሬታ አስነስቶ ነበር። ከዛም በኋላ ከኮሚሽኑ ጋር ውይይት እንደነበራችሁ ሰምተናል። እንዴት ተስተናገደ፣ ምን ተባለ?
የምክክር ኮሚሽን አባላት ምርጫ ላይ በተቻለን መጠን ጥቆማ እንዲደረግ ጥረት አድርገን ነበር፤ እንደ ትምራን። ወርክሾፖችን በማዘጋጀት፣ የሴቶች ማኅበራት ቅንጅት የሚያዘጋጀው ውይይት ነበርና፣ በዛም ቅስቀሳ በማድረግ ፍላጎት እና ብቃት ያላቸው ሴቶች ወደዚህ ቦታ እንዲመጡና እንዲጠቆሙ የማድረግ ሥራ ሠርተን ነበር።

እንዳየሽው የተመረጡት ሦስት ሴቶች ናቸው። ምን ያህል እንደተጠቆመና ከዛም ምን ያህል ሴቶች እንዳሉ አናውቅም። አርባ ኹለቱ ውስጥ ምን ያህል ሴቶች እንደገቡም አናውቅም። በምን መስፈርትስ ተመረጡ የሚለው ላይም ግልጽነት ይጎድል ነበር። ይህ ቅሬታ ነበረን።
ከዚህ በፊት ትምራን ባዘጋጀችው ሥልጠና እና ልምድ ልውውጥ ላይ አንድ ጥምረት ተፈጥሮ ነበር። ይህም ሴቶች በብሔራዊ ምክክሩ እንዲወከሉና ትርጉም ባለው ሁኔታ እንዲሳተፉ አካታችነት ዙሪያ የሚሠሩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጥምረት ነው። የጥምረቱ ሥም ጥምረት ለሴቶች ድምጽ፣ ለአገራዊ ምክክር መድረክ የሚል ነው። በዚህ ጥምረት ቅሬታችንን በሚመለከት የአቋም መግለጫም ልከን ነበር።

ዞሮ ዞሮ ወደኋላ ተመልሰን አቅማችን ከመጨረስ ይልቅ የመረጥነው ወደፊት መሄድን ነው። ከዚህ በኋላ በሚኖረው ሥራ ላይ በደንብ ለመሥራት ነው ፍላጎት ያለን። ወደ ኋላ ተመልሰን አቅም ከመጨረስ ይልቅ፣ አሁንም ከዚህ በኋላ በሚኖረው የብሔራዊ ምክክር መድረኩ ላይ ሴቶች ትርጉም ባለው ሁኔታ እንዴት ሊሳተፉ ይችላሉ የሚለውን፤ ሴቶች ጉዳይ ላይ እንደሚሠሩ ተቋማት አንድ ሆነን፣ ተደራጅተን ልንሠራ ነው ሐሳባችን።

ለዛም ከብሔራዊ ምክክር ኮሚሽኑም ጋር ውይይት አድርገናል። ጥሩ ተቀብለውናል፤ ጥሩ የሚባሉ ግብዓቶች ሰጥተዉናል፤ ከእኛ ጋር ለመሥራት ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸውልናል። ስለዚህ ሴቶች በበቂና ትርጉም ባለው ሁኔታ መወከል እንዲችሉ፤ እንደተወያይ፣ እንደ አወያይ፣ ውሳኔ እስከ መስጠት ደረጃ እስከሚደርሱ ሴቶች እንዲሳተፉ፣ የሴቶች ድምጽ እንደ አጀንዳ እንዲወከል፣ እነዚህ ነገሮች ላይ ተወያይተናል።

ብሔራዊ ምክክር ኮሚሽኑ እንዳልኩሽ በጣም ጥሩ የሆነ ግብረ መልስ ነው የሰጠን። የእኛን ፍላጎት ሁሉ የእነሱም ፍላጎት እንደሆነ፤ ሀምሳ በመቶ የሆኑትን ሴቶችን ትቶ ብሔራዊ መግባባት ሊኖር እንደማይችል፣ የሴቶች የብቻቸው ጉዳይ የሆኑትም እንደ አጀንዳ እንዲቀረጹ እነርሱም ጥረት እንደሚያደርጉ፣ እኛም ቅስቀሳ እንድናደርግ ነው የነገሩን። እና በጣም ጥሩ የሚባል ውይይት ነው የነበረው።

ስለዚህ ከዚህ በኋላ ታች ድረስ ሴቶችን ለማስተማር አስበናል። ታች ድረስ ማለት በየክልሉ፣ በወረዳና ቀበሌ ደረጃ ወርደን የማስተማር ፍላጎት አለን። ሁሉም ሴቶች ስለብሔራዊ ምክክሩ ግንዛቤ እንዲኖራቸው፣ እውቀቱ ከኖራቸው በኋላ ደግሞ ምክክሩ ላይ መወያየት፣ ፍላጎትና ዕይታቸውን ማንጸባረቅ እንዲችሉ ማድረግ ነው።

ትልቅ ኃላፊነት ነው ላያችን ላይ የወደቀውና ምንድን ነው ኃላፊነታችን፣ ምንድን ነው ፍላጎታችን፣ ልጆቻችን ወደፊት ጥሩ ኑሮ እንዲኖሩ፣ አገራችን ሰላማዊ ሆና መቀጠል እንድትችል፣ ሴቷ ምን ትፈልጋለች የሚለውን አሁን ነው መናገር የምንችለው። ይህ እድል ተፈጥሮልናል፤ ይህን እድል መጠቀም አለብን።

- ይከተሉን -Social Media

ይህ እንዳለ ሆኖ፣ በዚህ የምክክር ኮሚሽን ውጤታማነት ላይ ምን ያህል ተስፋ አድርጋችኋል?
አሁን ይህን እንደ እድል ነው የምንጠቀመው። እንዲሠራም እንዳይሠራም ለማድረግ እድሉ አለን፤ አሁን ላይ። የአቅማችን ያህል ሠርተን ይህ ብሔራዊ ምክክሩ ውጤታማ እንዲሆን ነው ማድረግ ያለብን። እንደ ሲቪል ማኅበረሰብ ተቋማት፣ ማኅበረሰቡን በማንቃት፣ ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ ድምጻቸው ሳይታፈን መወያየት እንዲችሉ የማድረግ ኃላፊነት አለብን።

ይህንን ኃላፊነታችንን በመወጣት ከብሔራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ጎን በመሆን ብሔራዊ ምክክሩ እንዲሠራ ነው ማድረግ ያለብን። ምክንያቱም በመነጋገርና በመወያየት ነው አገር ልትመራና ልትመሠረት የሚገባው። ዘላቂነት ባለው ሁኔታ በሰላማዊ መንገድ ልትቆም የምትችለው በመግባባትና በመወያየት ነው።

ይህ ለእኛ ትልቅ እድል ነው፤ የእኛም ፍላጎት ስለሆነ። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ያለን የሲቪል ማኅበረሰብ ተቋም ነን። አገራችን ሰላማዊ እንድትሆን እንፈልጋለን። ይህን ለማስቻል ደግሞ አሁን ላይ እድል ተሰጥቶናል።

ውጤት አልባ እንዲሆን (ፌል እንዲያደርግ) አንፈልግም። እንዲሠራ እንፈልጋለን። ሲሠራ ግን ሴቶችም ተካተው ነው እንዲሠራ የምንፈልገው። እንደ ማኅበረሰብ የአገሪቷ ጥያቄ የሴቶችም ጥያቄ ነው። ከዛ በተጨማሪ ወንዱ የሌለው ሴቷ ብቻ ያሏት ጥያቄዎች ይኖራሉ። ያ ጥያቄ ምንድን ነው የሚለውን ለይተን አውጥተን፣ እንደ አጀንዳ እንዲቀረጽ ቅስቀሳ አድርገን፤ ይህ ብሔራዊ ምክክር ውጤታማ እንዲሆን ነው የምንፈልገው።

ከዚህ ጉዳይ ስንወጣ፣ በብዙዎች ዘንድ ለፌሚኒዝም ያለው ዕይታ ማኅበሩ ላይ የፈጠረው ችግር አለ?
አዎን! በየቀኑ ሥራችን ላይ የሚገጥመን ነገር ነው። በእርግጥ እንደ ትምራን፣ ትምራን የተነሳችው የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ እና አመራርመት ለማስፋት ነው። ሴቶች አመራርነት ላይ በበቂ ሁኔታ እንደሌሉ ሁሉም ይስማማል። አሁን የተሻለ ነገር ቢኖርም፣ አመራርነት ሲባል በሚኒስትር ደረጃ ያሉትን ብቻ ሳይሆን በየወረዳና ቀበሌ ደረጃ ነው።

ብዙዎች ሐሳቡን ይደግፉታል፤ ተቀብለዉታል። ሴት ወደ አመራርነት ስትመጣ ችግሮች ይቀረፋሉ የሚሉ ወንዶችም ሴቶችም አሉ።

ግን ደግሞ እኔ እንደ ግለሰብ፤ ትምራን ብቻ አይደለም የሠራሁት። ከሴቶች መብቶች ጋር በተያያዘ ብዙ ሠርቻለሁ፣ ሥልጠናዎችንም እሰጥ ነበር። ይሄ ፌሚኒዝም ያመጣብን ነው የሚሉ ዕይታዎች አሉ። የሚገርመው እንደዛ የሚሉ ሰዎች መሬት ላይ ያለውን ችግር የእውነት ቢያዩትና ቢረዱት ኖሮ ይህን አይሉም ነበር።

ለምሳሌ በፊት እሠራበት የነበረው ተቋም ላይ የሕግ ድጋፍ አገልግለት ይሰጥ ነበር። ያንን ድጋፍ የሚሰጡ ወንዶች ነበሩ። ከሌላው ሰው ይልቅ ወንዶች ለሴቶች መብት ያላቸው ግንዛቤ፣ የሴቶች መብት እንዲከበር ያላቸው ፍላጎትና ተነሳሽት ከሌለው ሁሉ የላቀ ነው፤ መሬት ላይ ያለውን ችግር ስለሚያውቁ። እውቀቱ ካለ ማንም አልቀበልም ብሎ አይገፋም። መብት መሆኑን ካለማወቅ የተነሳ ነው።

- ይከተሉን -Social Media

ያደግሽበትን ነገር ቶሎ ለመተው ከባድ ነው የሚሆነው፤ መግፋት ይኖራል። ይህንን ልንፈታና ልንገፋ የምንችለው ወንዶችን በማካተት ነው። በምንሠረው ሥራ ውስጥ ሁሉ ወንዶች እንዲያውቁት በማድረግ ነው። ያለውን ችግር ባወቁ ቁጥር የመግፋቱ ነገር አይኖርም።

እንደ እኔ አመለካከት፣ በሴት ልጅ እኩልነት ማመን ማለት ነው፤ ፌሚኒዝም። የሴት ልጅን እኩልነት የማያምን ሰው አይኖርም። ያ እኩልነት የሌለበት ማኅበረሰብ መኖሩ እስከዛሬ የሴቷ መብት አለመከበሩ ሴቷ ላይ ያመጣውን ችግር ልብ ማለት ያስፈልጋል። ሴቷኮ በአብዛኛው በራስ መተማመን የማጣት ችግር የደረሰባት፣ አመራር ሁኚ ስትባል እንቢ የምትልበት ምክንያት፤ ካሳለፈችው ችግር የተነሳ ነው። ወንድ ከእኔ ይሻላል ብላ እንድታስብ ተደርግ ስላደገች፣ አልችልም የሚል አስተሳሰብ ውስጥ እንድትገባ ስለተደረገ ነው።

በአገራችን ብቻ ሳይሆን በማንኛውም ደረጃ በበቂ ሁኔታ የሴቶችን አቅም አልተጠቀምንም። ስለዚህ ይህን ሀምሳ በመቶና ከዛ በላይ የሚሆነውን ማኅበረሰባችንን አገልግሎት እንዳንጠቀም ማድረጋችን፣ አገራችንም እንዳታድግ ያደረገ ችግር ነው። እኩልነት አለመተግበሩ አገራችንም ወደኋላ እንድትቀር ያደረገ መሆኑ ማኅበረሰቡ ያለውን እውነት ቢያውቀው፣ ወንዶችም ሴቶችም መሬት ላይ ያለውን ችግር ቢያውቁት፤ ለአገራችን እድገት ሲባል የሴቶች እኩል ተሳትፎና እኩልነት መተግበር አለበት የሚለው ሐሳብ ማኅበረሰቡ ራሱ ይመራው ነበር። ካለማወቅ የመነጨ ነው ብዬ ነው የማስበው። እያወቁም ደግሞ የሚያደርጉት በሴቶች ላይ ምን ያህል ችግር እንደሚከሰት ካለማወቅ ነው የሚል እምነት አለኝ።

የቀደመው እንዳለ ሆኖ፣ አዲስ ትውልድ በዚህ መልክ ተቀርጾ እንዲወጣ ለማስቻል ትምራን የምትሠራው ሥራ አለ?
ትምራን በሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎና አመራርነት ላይ ነው የምትሠራው። ሁሉን ዓይነት የሴቶች ጉዳይ የሚቃኙ ማኅበራት አሉ። በበኩላችን የአመራር ሥልጠናዎች እየሰጠን ነው፤ በተለይ ለዩኒቨርሲቲዎች። ከዛ በተጨማሪ ደግሞ ልምድ ልውውጥ መድረኮች እናዘጋጃለን። ከፍተኛ አመራርነት ላይ ያሉ ሴቶች እንዴት እዚህ ደረጃ ላይ እንደደረሱ፣ ያጋጠሟቸውን ተግዳሮቶች እንዴት እንዳለፉ፣ አሁን ምን ዓይነት ችግር ያጋጥማቸዋል፤ ችግሮቹን ለማለፍ ምን ጥረት ይጠበቃል የሚሉትን ነገሮች ልምድ ባገኙ ቁጥር በጣም ይነቃቃሉ። ፍላጎታቸው ይጨምራል፣ ተነሳሽነትም ይኖራል።

ከዚህ በፊት እንዲህ ያለ መድረክ አዘጋጅተን ነበር። ተማሪዎችን በጣም ያነቃቃ፣ በትምህርት ቆይታቸው ውስጥ ባሉ ክበባት ውስጥ በአመራርነት እንዲሳተፉ ተነሳሽት ያሳዩበት፣ ያነቃቃቸው መድረክ ነበር ያዘጋጀነው። እና እንዲህ ያሉ መድረኮችን በብዛትና በስፋት በማዘጋጀት የመቀጠል ሐሳብ አለን። ከተማሪዎች እንዲጀምር።

ምክንያቱም ሁሉም ነገር ልምምድ ነው። ትምህርት ቤት የሆነ ክበብ ውስጥ ተሳትፎ መሪ የመሆን ነገር ሴቶች ጋር ላይኖር ይችላል። ከዛ ጀምሮ ግን ልምምድ ሲደረግ ሕይወት ቀላል ይሆንላቸዋል። ሌላ ከፍ ያለ የአመራር ሥራን ለመሥራት ከባድ አይሆንባቸውም። እና ከዛ ጀምሮ ልምምድ እንዲኖር እንፈልጋለን። በዚህ ላይ ሥራ ጀምረናል፣ ሥልጠናዎችን እየሰጠን ነው።

የትምራን የወደፊት እቅድና ግብ ምንድን ነው?
የሴቶችን አመራርነት እና የፖለቲካ ተሳትፎ ማሳደግ ነው ዓላማችን። ግባችን የሚሆነው በአገራችን በሚኖረው በማንኛውም የአመራርነት እርከን ላይ ሴቶች ከወንዶች እኩል በሆነ ደረጃ፣ ሀምሳ በመቶ እና ከዛ በላይ በአመራርነት መጥተው ማየት ነው።
ከአገራችን ሰላም ጋር በተያያዘ ሰላም የማስፈን እንቅስቃሴው ላይ፣ መከላከልም ሰላም ማስፈንም ላይ ሴቶች በበቂ ሁኔታ እኩል በአመራርነት እንዲሳተፉ እንፈልጋለን። ሴት ልቧ ለሰላም ቅርብ ነው። እና ሴቷ ሰላምን በመራች ቁጥር የምንፈልገው ሰላም የመስፈን እድሉ ሰፊ ነው የሚሆነው። ሰላም የማስፈን ሥራዎችና እንቅስቃሴዎችም ላይ በአገራችን እንድትሳተፍ እንፈልጋለን።

ብሔራዊ ምክክር ዓላማው አሁን ሰላም ማስፈን ብቻ ሳይሆን ለወደፊትም ለአገራችን ዘላቂ ሰላም ትልቀ ዓላማ ይዞ ነው የተነሳው። የአገራችንን የወደፊት እድል ለመወሰን ነው። እና እዚህም ላይ ሴቷ እንድትሳተፍ እንፈልጋለን። ስለዚህ ሴት ልጅ በቤተሰቧ፣ በሥራ ቦታ፣ በማኅበረሰብ እንዲሁ በአገርም ላይ የመሪነት ቦታ እንዲኖራት፣ ይህንን መሪነት በመለማመድ አገርን የማሳደግ፣ ሰላምን የማምጣት ኃላፊነቷን ልትወጣ ትችላለች።

- ይከተሉን -Social Media

በመጨረሻ የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለ፤
በእርግጥ የምረዳው ነገር ቢሆንም ሴቶች እድል ሲሰጣቸው መሸሽ አለ። ለምሳሌ ቃለመጠይቅ ለሚድያ ለመስጠት ሴቶች የምንፈራና የምንሰጋበት ሁኔታ አለ፤ ከወንዶች ይልቅ። ምክንያታችን ያው ያሳለፍናቸው ነገሮች ራሳችን ላይ የፈጠሩብን ተጽእኖዎች ናቸው። ስለዚህ መጀመሪያ የእኛ ተነሳሽነት ሊኖር ይገባል።

ብሔራዊ ምክክሩ ላይ የኮሚሽን አባላት ሲታጩ፣ እኛ እየደወልን የማሳተፍ ሥራ ሠርተናል። ልንጠቁምሽ ነበር ፈቃደኛ ነሽ ወይ ብለን ፈቃደኝነትም ስንጠይቅ ነበር። ያኔ አብዛኞቹ አይፈልጉም። እና እድሎች ከመጡ እንጠቀምበት። ምክንያቱም የእኛ እዚህ ቦታ ላይ መሆን ለሌላው ከእኛ በኋላ ለሚመጣ ትውልድ በጣም የሚያነሳሳ ነው። አረአያ ነው የምንሆንላቸው።

እና አቅም ያላችሁ ሴቶች ወደኋላ አታፈግፍጉ። አቅም የሌለው ሌላው ሰው መጥቶ ችግሮች አይፈጠሩ። አቅም ያላችሁ ወደኋላ አታፈግፍጉ የሚል ጥሪ ማቅረብ እፈልጋለሁ።


ቅጽ 4 ቁጥር 187 ግንቦት 27 2014

ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች