መምህራን ከዞን ዞን ዝውውር ስለዘገየባቸው ቅሬታ አነሱ

0
1251

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል መምህራን ደመወዝ አልተሰጣቸውም

በተለያዩ የትምህርት ተቋማት እያገለገሉ የሚገኙ መምህራን እስከ አሁን ከዞን ዞን ዝውውር ተሠርቶ እጃቸው ስላልደረሰ የዘገየበትን ምክንያት አለማወቃቸው ቅሬታ እንዳሳደረባቸው ገለጹ።

ቅሬታ ተሰምቶናል ባዮቹ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፤ እስከዛሬ የዞን ዞን ዝውውራቸውን የሚያውቁት ግንቦት እንደገባ የነበረ ሲሆን፤ በዚህ ዓመት ግን ይህ ዘገባ እስከተዘጋጀበት ቀን ድረስ መረጃውን ባለማግኘታቸው ዝውውሩን ማወቅ አልቻልንም ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ቅሬታ ካቀረቡት መምህራን መካከል ምህረቱ አከለ፣ መምህራን እስከ ዛሬ ከዞን ዞን ዝውውራቸው ይፋ የሚደረገው ግንቦት ወር መጀመሪያ ላይ እንደነበር አስታውሰው አሁን ግን መምህራን መረጃው እንዳልደረሳቸው ለአዲስ ማለዳ አሳውቀዋል።
ጉዳዩ በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ ለማረጋገጥ ወደሚመለከተው አካል ሁሉ በተዋረድ ስልክ ቢደውሉም፣ ምላሽ ማግኘት አለመቻላቸውንም ቅሬታ አቅራቢዎቹ ተናግረዋል።

ወደ አማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ስልክ ቢደውሉም ምላሽ እንዳላገኙ የገለጹት መምህሩ፤ በሌሎች ከትምህርት ውጭ በሆኑ ተቋማት የሚያገለግሉ ሠራተኞች ዝውውር እንደተሠራላቸው ገልጸው፣ በክልሉ ላሉ መምህራን በሙሉ ግን እንዳልተሠራ ጠቁመዋል።
ለአብነትም በጤናው ዘርፍ የተሰማሩ ሠራተኞች የዞን ዞን ዝውውር ይፋ እንደተደረገ የተገለፀ ሲሆን፤ የመምህራን የዘገየበት ምክንያት ምንድን ነው? እስከ ዛሬ ሲነገረን በነበረው ወቅት ይፋ ያልተደረገበትስ ምክንያት ምንድን ነው? ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል።
ሌላኛዋ ፋሲካ ሞላ የተባሉት መምህርት በበኩላቸው፣ ዝውውሩን በተስፋ እየተጠባበቁ ቢቆዩም እስከ አሁን ባለማወቃቸው ቅሬታ እንደተሰማቸው ተናግረዋል።

ማንም ሰው ሥራውን በአግባቡ ለመሥራት ሞራል የሚኖረው አስፈላጊ ነገሮች በተባለው ሰዓትና ወቅት ሲፈጸሙለት ነው ያሉት ቅሬታ አቅራቢዋ፤ አንድ አካባቢ ብዙ ጊዜ መቆየት በማኅበራዊ፤ በኢኮኖሚያዊ እና በፖለቲካዊ ጉዳዮች ጫና አለው ሲሉ አብራርተዋል።
በአንድ ትምህርት ቤት ለ14 ዓመት ሲሠሩ የነበረበትን ወቅት አስታውሰው፣ ቀላል የማይባል ጫና እንዳሳለፉ የጠቀሱት ፋሲካ፤ አሁንም ቢሆን ዝውውሩን አጥብቀው እንደሚሹት አልደበቁም። በመሆኑም ቅሬታ አቅራቢዎቹ የሚመለከተው አካል አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጠን ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ጌታቸው ቢያዝን፣ ዝውውሩ እሰከ አሁን ይፋ እንዳልተደረገ ያመኑ ሲሆን፤ በመሠራት ላይ እንደሆነና ከኹለት ሳምንት በኋላ ይፋ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።
የዞን ዞን ዝውውር እየተሠራ ስለሆነ ይጠብቁ ያሉት ኃላፊው፤ የዘገየበትን ምክንያት ሲጠየቁ ዝውውር ምን ጊዜም በክልል ስኬጁል መሠረት ነው የሚሠራው ነው ያሉት። ቀደም ብሎ ሊሠራ ይችላል፣ በተለያየ ምክንያት ደግሞ ሊዘገይ ይችላል ያሉ ሲሆን፤ የዘገየው አንዳንድ መመሪያዎች እየተሠሩ ስለነበር ነውም ብለዋል።

በሌላ በኩል በአዲሱ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የሚያገለግሉ መምህራን ደመወዝ ስላልተከፈላቸውና ከ2011 ጀምሮ የደረጃ ዕድገት ስላልተሠራላቸው ቅሬታ እያነሱ ነው። ደመወዛቸውን አለመሰጠታቸውን ተከትሎም የመማር ማስተማር ሂደቱ በመስተጓጎሉ ተማሪዎች እየተበተኑ መሆናቸውን መረጃዎች አመላክተዋል። የጠለምት ኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራን ደመወዝ ስላልተከፈላቸው በመበታተናቸው ተማሪዎች ትምህርት ቤት ሄደው የሚያስተምራቸው በማጣታቸው እየተጉላሉ ነው። መምህራኑ እንዲመለሱም የጠለምት ወረዳ ጥሪ አስተላልፏል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መምህራን ደመወዝን፤ የደረጃ እድገትን፤ ዝውውርን በተመለከተ ተደጋጋሚ ቅሬታ እያቀረቡ ነው።


ቅጽ 4 ቁጥር 187 ግንቦት 27 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here