ዐቃቤ ሕግ በቅርቡ በታሰሩ ሰዎች ላይ እስካሁን ክስ አልመሰረትኩም አለ
ሰዎች በልዩ ሁኔታ ታስረው እንዲመረመሩ የሚያዝ ሕግ የለም ሲል ፍትህ ሚኒስቴር ለአዲስ ማለዳ ገለጸ።
ተጠርጣሪዎች ከተያዙ በኋላ አንዳንዶች የት እንደታሰሩ እንደማይታወቅና ከቤተሰቦቻቸውም እንዳይገናኙ የሚከለከሉት ከምን አግባብ እንደሆነ ለቀረበ ጥያቄ፣ በሕገ መንግሥቱ፣ በሥነ ስርዓት ሕጉም ይሁን በፈረምናቸው ዓለም ዐቀፍ ስምምነቶች ሰዎች በልዩ ሁኔታ ታስረው እንዲመረመሩ የሚያዝ ሕግ አለመኖሩ ነው የተጠቀሰው።
የፍትህ ሚኒስቴር የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አወል ሱልጣን፣ ወንጀል ሠርቶ ለማምለጥ ከሚሞክር ሰው በስተቀር ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰዎች እንደማይታሰሩ ሕጉ ላይ ተቀምጧል። በየትኛውም ወንጀል የተጠረጠረ ሰው በ48 ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት መቅረብም አለበት ነው ያሉት።
የተያዙ ሰዎች በቤተሰቦቻቸው፣ በሐይማኖት አባቶቻቸውና በሚፈልጉት የመጎብኘት መብት አላቸው። ይህ በማይሆንበት ቦታ ሰዎችን ማሰርም በሕጉ መሠረት የተከለከለ ነው። ይልቁንም የተጠረጠሩበት ወንጀል የአገርን ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥል ጠንካራ ከሆነ ምርመራውን ማዘመንና የመብት ጥሰትን በሚቀንስ መልኩ መሆን አለበት ብለዋል።
ሆኖም አሁን እየታየ ያለው አሰራር የአገር እና የብዙኀኑን ደኅንነት ለመጠበቅ ሲባል የተወሰደ ጥንቃቄ ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ምክር ቤት፣ በአሁኑ ወቅት በቁጥጥር ሥር የዋሉት ጋዜጠኞች በሕግ ከተደነገገው በተቃራኒ እንደተያዙ፣ በቅድመ-ፍርድ ጊዜ ለረጅም ቀናት ያለ ክስ ታስረው መቆየታቸውን፣ የታሳሪዎችን አድራሻ መደበቅ እና በቤተሰብና የሕግ ባለሙያ እንዳይጎበኙ መከልከል፣ እንዲሁም መደበኛ ባልሆኑ እስር ቤቶች ማሰር መኖሩን ጠቅሶ፣ ይህም የመገናኛ ብዙኀን አዋጁን የሚፃረር ተግባር መሆኑን በቅርቡ መግለጹ ይታወሳል።
በሌላ በኩል በቅርቡ የፌዴራል መንግሥትና የአማራ ክልል እያካሄድን ነው ባሉት የሕግ ማስከበር ዘመቻ የተነሳ፣ በፌዴራል ደረጃ በታሰሩ ሰዎች ላይ እስከ አሁን ክስ አልመሰረትኩም ሲል ፍትህ ሚኒስቴር ገልጿል።
በክልሎች ያለውን የሚመለከታቸው ራሳቸው ክልሎችን ነው ያለው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ፣ በፌዴራል ደረጃ በቁጥጥር ስር የዋሉ ሰዎች እስከ አሁን ክስ ያልተመሠረተባቸው ፖሊስ እያካሄደ ያለውን ምርመራ ባለማጠናቀቁ መሆኑን አስታውቋል።
የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አወል ሱልጣን፣ ሐሰተኛ መረጃና የጥላቻ ንግግር ስርጭትን በተመለከተ ወንጀል ፈጽመዋል። አገሪቱ ውስጥ የብሔርና የሐይማኖት ግጭት እንዲነሳ የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም፣ ሐሰተኛ መረጃና የጥላቻ ንግግር ስርጭትን ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ጥሰዋል ተብለው የተጠረጠሩ ለጊዜው ሥማቸውን የማንጠቅሳቸው 11 ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተካሄደባቸው ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ተጠርጣሪዎቹ በአብዛኛው በማኅበራዊ፣ ብሮድካስትና ህትመት ሚዲያ ሥራዎች ላይ የተሰማሩ መሆናቸውን የገለጹት ኃላፊው፣ ቃል የመስጠት፣ ማስረጃ የማሰባሰብና ሰዎችን ተጠያቂ ለማድረግ ምርመራ መጀመሩን አንስተዋል።
በቀጣይም ማንነታቸውን፣ የተጠረጠሩበትን ተግባር፣ ፖሊስ የወሰደውን እርምጃ፣ የዐቃቤ ሕግን ሚና እንዲሁም ክስ ሲመሠረትባቸው ደግሞ አንቀጽ ጠቅሰን በዝርዝር የምናሳውቅ ይሆናል ነው ያሉት።
ሆኖም የምርመራ ጊዜው መች እንደሚጠናቀቅ የሚወስነው የወንጀሉ ሁኔታ ነው ብለዋል። እንደ ወንጀሉ ክብደት እንዲሁም የወንጀሉን መነሻ ለማወቅ ወርም ኹለት ወርም ሊወስድ ይችላል ነው ያሉት።
እንደከዚህ ቀደሙ ፖሊስ ምርመራውን ሲጨርስ የሚያመጣው ሳይሆን፣ ዐቃቤ ሕግም አብሮ በምርመራ ሥራው የሚሳተፍበት ሁኔታ በመኖሩ የምርመራ ጊዜው እንዲያጥር የራሱን ሚና ይጫወታል ሲሉ ገልጸዋል። አክለውም፣ ፖሊስ ምርመራውን ከጨረሰ በኋላ ዐቃቤ ሕግ ከ15 ቀን በታች ክስ እንደሚመሠርት ተናግረዋል።
አራት ሺሕ ገደማ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር እንዳዋለና ወደፊትም ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር የማድረግ ተግባሩን እንደሚቀጥል በገለጸው አማራ ክልል፣ ምን ያህል ተጠርጣሪዎች ክስ እንደተመሠረተባቸው ለማወቅ አዲስ ማለዳ የክልሉን ፍትህ ቢሮ ደጋግማ ብትጠይቅም የቢሮው ኃላፊ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ሳይሳካ ቀርቷል።
ቅጽ 4 ቁጥር 187 ግንቦት 27 2014



