ለስኳር ፋብሪካዎች ግብዓት የሚሆን የሸንኮራ አገዳ ምርት እጥረት መከሰቱ እና በዚህም በርከት ያሉ የስኳር ፋብሪካዎች ሥራ መስተጓጎሉ ተገለጸ።
መረጃውን ለአዲስ ማለዳ ያደረሱት በስኳር ፋብሪካዎች የሚሠሩ ሠራተኞች እንደገለጹት፣ በዚህ ወቅት ለስኳር ፋብሪካዎች የስኳር ምርት ግብዓት የሚሆነው ሸንኮራ አገዳ ምርት እጥረት አለ። በዚህም ሥራ ያቆሙ እንዲሁም በከፊል የሚሠሩ ፋብሪካዎች ስለመኖራቸው ነው ጥቆማ የሰጡት።
ለአብነትም ጣና በለስ ስኳር ፋብሪካ በአገዳ እጥረት የተነሳ በሙሉ አቅሙ ምርት እየሰጠ አይደለም ነው የተባለው። ወንጂ ስኳር ፋብሪካም እንዲሁ በአገዳ እጥረት የምርት መስተጓጎል እንዳጋጠመው ተጠቁሟል። ወንጂ ስኳር ፋብሪካን የአካባቢው የከርሰ ምድር ውኃ ከፍታ እየጨመረ በመምጣቱ የአገዳ ምርታማነት መቀነስ እያጋጠመው ይገኛል ሲሉ የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን የኮምዩኒኬሽን ኃላፊ ረታ ደመቀ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
በዚህም በአካባቢው ያሉ አገዳ አብቃይ ማኅበራት ከልማቱ የመውጣት ሁኔታ ቢኖርም፣ ፋብሪካው በስምንት ሺሕ ሄክታር መሬት ላይ እያለማው የሚገኝ የራሱ የሸንኮራ አገዳ ማሳ ያለው እንደመሆኑ የሸንኮራ አገዳ ዕጥረት ይቀረፋል ነው ያሉት። በመተኻራ ስኳር ፋብሪካም እንዲሁ የበልግ ዝናብ በወቅቱ ባለመዝነቡ ምክንያት፣ በአካባቢው ያለው የድርቅ መጠን ከሌላው ዓመት የተለየ በመሆኑ የአርብቶ አደር ከብቶች በሸንኮራ አገዳው ላይ ጉዳት በማድረሳቸው የተወሰነ የአገዳ እጥረት አጋጥሟል ብለዋል።
ኮርፖሬሽኑ ለአዲስ ማለዳ በሰጠው ማብራሪያ፣ ለጣና በለስ ቁጥር አንድ ስኳር ፋብሪካ በ13 ሺሕ ሄክታር መሬት ላይ የለማ ሸንኮራ አገዳ መኖሩን ጠቅሶ፣ ፋብሪካው ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ምርት እየገባ እንደመሆኑና አንድ የስኳር ፋብሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ምርት ሲገባ ወደ ሙሉ የመፍጨት አቅሙ የሚደርሰው በሂደት እንደመሆኑ፤ ፋብሪካው አሁን ላለው የመፍጨት አቅም በቂ የሆነ የሸንኮራ አገዳ ለምቶ ዝግጁ በመሆን ለፋብሪካ እየቀረበ ይገኛል ነው ያለው።
ይሁንና የፋብሪካው ግንባታ ተጠናቆ ወደ ሥራ መግባት ከነበረበት ጊዜ ከሰባት ዓመት በላይ በመጓተቱና በተወሰነ ሄክታር መሬት ላይ የለማ አገዳ ለፋብሪካ መቅረብ የነበረበት ጊዜ በማለፉ፤ ከፊሉና የሱክሮስ ይዘቱ በቂ የሆነ አገዳ ለፋብሪካው እንዲቀርብ የሚደረግ ይሆናል ነው የተባለው።
ያረጀው አገዳ (የሱክሮስ ይዘቱ በቂ ያልሆነው) ደግሞ ተቆርጦ እንደገና እንዲለማ (Ratoon) እየተደረገ በመሆኑ በፋብሪካው የአገዳ ዕጥረት አለመኖሩን ኮርፖሬሽኑ ገልጿል።
በአፋር ክልል የሚገኘው የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካም በአካባቢው በተደጋጋሚ በሚከሰት ድርቅ ምክንያት የሸንኮራ አገዳ ማሳው የወደመ በመሆኑና ጉዳዩ የፌዴራልና የክልሉ መንግሥታትን ልዩ ትኩረትና መፍትሔ የሚጠይቅ በመሆኑ፣ ጉዳዩ ለፌዴራል መንግሥት መቅረቡን ገልጸዋል።
ከዚሁ ጋር በተገናኘም ከወቅታዊ የዓለም ዐቀፍ እና አገር ዐቀፍ ሁኔታ ጋር ተያይዞ ጫናዎች በመኖራቸው፣ ለሸንኮራ አገዳው ልማት የሚውል የማዳበሪያና የፀረ-አረም መድኃኒቶች እንዲሁም ሎሎች አቅርቦት ችግር አጋጥሟል ተብሏል። የፋብሪካዎችና የእርሻ ማሽነሪዎች መለዋወጫን ከውጭ ገዝቶ ለማስገባት ተግዳሮት ሆኖ በመገኘቱም በአገር ውስጥ መለዋወጫዎች የመጠቀም ሥራ እየተተገበረ ይገኛል ነው ያሉት።
በሌላ በኩል፣ በግንባታ ላይ የነበረው በፕሮጀክት ደረጃ የሚገኘው የወልቃይት ስኳር ልማት ፕሮጀክት፣ ከሰሜኑ የኢትዮጵያ ጦርነት ጋር በተያያዘ ሥራው ተቋርጦ ይገኛል ተብሏል። ፕሮጀክቱ ከዚያ ቀደም የግድብ፣ የፋብሪካ እና የመስኖ ልማት ሥራው ከ80 በመቶ በላይ ደርሶ የነበረ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ያለበትን ሁኔታ የሚያጣራ ከስኳር ኮርፖሬሽን፣ ከፌዴራል መንግሥት እና ከአካባቢው ጸጥታ አካላት ተዋቅሮ ወደ ሥራ መግባቱ ነው የተገለጸው።
በፊንጫ፣ በአርጆ ዲዴሳ፣ በኦሞ ኩራዝ ቁጥር ኹለት እና ቁጥር ሦስት ስኳር ፋብሪካዎች መለስተኛ የፀጥታ ችግር አልፎ አልፎ የሚስተዋል ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት ከዚህ ጋር በተያያዘ ሥራ ያቆመ ስኳር ፋብሪካ የለም ተብሏል።
ቅጽ 4 ቁጥር 187 ግንቦት 27 2014



