የሎደር ጎማ ዋጋ ከ80 ወደ 150 ሺሕ ብር ማሻቀቡ ተገለጸ

0
1861

የሎደር ተሽከርካሪ ጎማ ዋጋ በሦስት ወር ውስጥ ከ80 ሺሕ ወደ 150 ሺሕ ብር ከፍ ማለቱን የሎደር አሽከርካሪዎች ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
የአንድ ሎደር ተሽከርካሪ ጎማ ዋጋ ውድ ተብሎ ከአሁን በፊት 80 ሺሕ ብር እየገዙ እንደነበር የሚያስታውሱት ታደሰ አሰፋ፣ ከኹለት ወር በፊት ወደ ማከፋፈያ ባቀኑበት ወቅት ዋጋው ከ80 ወደ 95 ሺሕ ብር ከፍ ብሎ እንዳገኙት ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል።

‹‹ሠርተን የምናገኘው ገቢና የጎማው ዋጋ አይመጣጠንም።›› ያሉት ሹፌሩ፤ ቀድሞ በነበረው የኑሮ ውድነት በአንዴ የ15 ሺሕ ብር ጭማሪ ማድረግ፣ የኑሮ ሁኔታችንን አዛብቶብን ነበር ሲሉ አስታውሰዋል። ጭማሬው በዚህ አልተቋጨም ያሉት ሹፌሩ፣ ዋጋው ከ85 ወደ 100 ሺሕ ብር ከፍ ማለቱን ጠቅሰው፤ ከዚህም አልፎ ሰሞኑን ደግሞ ወደ 150 ሺሕ ብር በማሻቀቡ የ55 ሺሕ ብር ጭማሪ አሳይቷል ነው ያሉት።

ወደ ማከፋፈያ ሄደን ለምን ይህን ያህል ጭማሪ ተደረገ? ብለን ስንጠይቅ “የጊዜው ጉዳይ ነው” የሚል ምላሽ ነው የሚሰጡን ያሉት ታደሰ፤ የዋጋ መናሩ በሥራቸው ላይ መስተጓጎልን እንዳሳደረባቸውም አንስተዋል።
የጎማ ዋጋ ጭማሬው ከሚያገኙት ገቢ ጋር ስለማይመጣጠን በርካታ አሽከርካሪዎች ሥራቸውን ለማቆም እንደተገደዱ ታደሰ ይገልጻሉ። እርሳቸውም በበኩላቸው የነዳጅና የጎማ ዋጋ ስላማረራቸው መኪናቸውን መሸጣቸውንም ይናገራሉ።
“የተፈጠረው የሥራ መስተጓጎል ቀላል አይደለም። ታዲያ ሠርተን የምናገኘውን ገቢ ለጎማ ብቻ ወጭ አድርገን እንዴት እንኑር?” ብለዋል ቅሬታ አቅራቢው።

ጥጋቡ ሲሳይ የተባሉት ሹፌር 17.5/25 የሆነ የግሬደር ተሽከርካሪ ጎማ ከዓመት በፊት ከ38 እስከ 40 ሺሕ ሲገዙ እንደነበር ገልጸው፣ አሁን ላይ ከ85 እስከ 90 ሺሕ ብር እየገዛን ነው ብለዋል። ከዓመት በፊት 65 ሺሕ ብር ሲገዙት የነበረውን የሎደር ጎማም፣ ሰሞኑን 120 ሺሕ ብር እንደገዙ ገልጸዋል።

በተጨማሪም ከ18 እስከ 20 ሺሕ ብር ሲገዛ የነበረው የአይሱዚ ጎማ ሰሞኑን ከ42 ሺሕ ብር በላይ እየተሸጠ መሆኑን ጠቁመዋል።
ከዚህ በፊት ኹለት ሺሕ 500 ብር ሲሸጥ የነበረው ወደ ስድስት ሺሕ ብር፣ ሦስት ሺሕ ብር ሲሸጥ የነበረው የሚኒባስ ጎማ ደግሞ ከሰባት እስከ ስምንት ሺሕ ብር እየተሸጠ መሆኑን የአይሱዚ አሽከርካሪ ሲሳይ ዓለሙ ተናግረዋል።

ከቅሬታ አቅራቢዎቹ መካከል ጥጋቡ ሲሳይ ችግሩ የተከሰተው ገበያው ነጻ ገበያ ስለሆነ ነጋዴዎችን የሚቆጣጠራቸው ስለሌለ መሆኑን አንስተው፣ መንግሥት ሊያተኩርበት እንደሚገባ አሳስበዋል።
በተጨማሪም፣ መጠኑ 8/25 የሆነ የትንንሽ ገልባጭ ተሽከርካሪዎች ጎማ 16 ሺሕ ብር፤ 9/25 የሆነው 23 ሺሕ ብር፤ 10/20 የሆነው ጎማ ደግሞ 25 ሺሕ ብር መሆኑን ማረጋገጥ ተችሏል። እንዲሁም መጠኑ 12/20 የሆነ የሲኖ ትራክ ጎማ ከ43 እስከ 45 ሺሕ ብር እየተሸጠ መሆኑን ማወቅ ተችሏል።

አዲስ ማለዳ በአዲስ አበባና በደሴ ከተማ ባሉ የሽያጭ ማዕከሎች የጎማ ዋጋ ስንት እንደሆነ ባጣራችው መሠረት፣ ቅሬታ አቅራቢዎቹ በጠቆሙት ዋጋ እየተሸጠ ነው።


ቅጽ 4 ቁጥር 187 ግንቦት 27 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here