ከ110 ሚሊዮን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

0
991

ማክሰኞ ግንቦት 30 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ባሳለፍነው ሳምንት ከ110 ሚሊዮን 66 ሺህ ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የገቢና የወጭ የኮንትሮባንድ እቃዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የጉምሩክ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡

ኮሚሽኑ ባሳለፍነው ሳምንት ባደረገው ክትትል 87 ነጥብ 9 ሚሊዮን የገቢ ኮንትሮባንድ እቃዎች እና 22 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ የወጭ ኮንትሮባንድ እቃዎች በተለያዩ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ተይዘዋል፡፡

የገቢ ኮንትሮባንድን በመቆጣጠር ረገድ ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዙት ሞያሌ፣ ጅግጅጋ፣ እና ድሬድዋ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ሲሆኑ፤ በቅደም ተከተላቸው 25 ነጥብ 1 ሚሊዮን፣ 12 ነጥብ 8 ሚሊዮን እና 12 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የኮንትሮባንድ እቃዎችን መያዝ መቻላቸው ተገልጿል፡፡

በቁጥጥር ሥር ከዋሉት የኮንትሮባንድ እቃዎች መካከል አልባሳት፣ ነዳጅ፣ የቁም እንስሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ቡና፣ መድሀኒት ፣ተሽከርካሪዎች፣ የመዋቢያ እቃዎች የጦር መሳሪያዎች፣ጫት፣ አደንዛዥ እጾች፣የምግብ ዘይት እና የተለያዩ አገር ገንዘቦች ይገኙበታል፡፡

የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ በጉምሩክ ኮሚሽን ሰራተኞች፣ በፌደራል ፖሊስ፣ በክልል ፖሊስ አባላትና ህብረተሰቡ ባደረጉት የጋራ ጥረት በፍተሻ፣ በበረራና በጥቆማ የተያዙ ሲሆን፤ ኮንትሮባንድ ሲያዘዋዉሩ የተገኙ ሰባት ሰዎችም በቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡

የጉምሩክ ኮሚሽን በዚህ የህግ ማስከበር ሥራ ላይ ለተሳተፉ የኮሚሽኑ ሰራተኞች፣ የክልልና የፌደራል ፖሊስ አባላት እንዲሁም ለመላው ህዝብ ምስጋናውን አቅርቧል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here