ጩኺ!

0
1208

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

በሕዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርቶች ውስጥ ሴቶች የሚገጥመን ጾታዊ ትንኮሳ ብዙ ነው። ይህን አንድ ዓረፍተ ነገር በማንበብ ብቻ እንኳ የደረሰብን ወይም የሰማነውንና ያየነውን አጋጣሚ አለማስታወስ አንችልም። ታክሲ ውስጥ፣ አውቶብስ እና ባቡር ላይ ይህ ዓይነት ችግር በተደጋጋሚ ያጋጥማል።

ከዚህ ቀደም በሴቶች ጉዳይ ላይ የሚሠሩ ማኅበራት ‹የሕግ ያለህ!› ሲሉ የትራንስፖርት ነገር ትኩረት እንዲሰጠው እንቅስቃሴ ጀምረው እንደነበር አስታውሳለሁ። ቀጥሎ ምን ደረሰ የሚለውን የተከታተልኩኝ ባይሆንም፣ አሁንም ችግሩ እንዳለ መሆኑ ግን ግልጽ ነው።

ሁኔታው አይመችም! በተለይ የትራንስፖርት ችግር በከፍተኛ ሁኔታ በሚስተዋልባት በመዲናይቱ አዲስ አበባ፣ ትራንስፖርት ውስጥ እጭቅ ሳይሉ ወይም ሳይጋፉ መጓዝ የሚታሰብ አይደለም። የቦታ ርቀትና የአቅም ሁኔታ ደግሞ የሚኖረንን የትራንስፖርት ምርጫ አጥብቦ፣ የአውቶብስ አልያም የባቡር ተጠቃሚ ያደርገናል።

ጥቅጥቅ ባለ አውቶብስ ውስጥ ‹ተነካሁ!› ማለት የማይዋጥለት ብዙ ሰው ይኖራል። ግን ደግሞ ሴቶች እናውቀዋለን! በጾታዊ ትንኮሳ መልክ የሚደረጉ ንክኪዎችን ከጤናማው ግፊያ መለየት አያዳግተንም። እናም ጥቅጥቅ ባለ ባቡር ውስጥ ወይም በሞላ አውቶብስ ውስጥ ጾታዊ ትንኮሳ ይደርሳል ስንል፤ ሁኔታውን ከመረዳት ውጪ በመሆን እንዳልሆነ መታወቅ አለበት ባይ ነኝ።

የሰውን በነጻነት የመጓጓዝ መብት መንካት እንደማይገባና ሴቶችን እየተነኮሱ ሰላም መንሳት ወንጀል ጭምር እንደሆነ፣ ነፍስ አውቋል ተብሎ ራሱን ችሎ ለሚንቀሳቀስ ‹ሰው› ማስረዳት አስቸጋሪ ነው። ሴሰኝነት ካልሆነ በቀር የሚያደርገው ትክክል እንዳልሆነ የማያውቅ ነው ብዬ አላምንም።

መንግሥት እርምጃ ይውሰድ፣ ትራንስፖርት አማራጭ ይፈጠር፣ በሴቶች ጉዳይ የሚሠሩ ማኅበራት ንቅናቄ ይፍጠሩ…ወዘተ ብዙ አማራጭ እናስቀምጥ ይሆናል። በበኩሌ እነዚህ ሁሉ መፍትሄ ያመጣሉ ብዬ እርግጠኛ አልሆንም።
መፍትሄ የሚመስለኝን ልንገራችሁ! መጮኽ! ተንኳሹን ማሳቀቅ!

ጥቃት የደረሰበትን ሰው መልሶ እንደመውቀስ (Victim Blaming) ሁሉ፣ መንገድ ላይ ለሚላከፈው፣ ጎንትሎ ለሚያልፈው፣ በአለባበስ አልያም በመልክና በቁመና ላይ በድፍረት ‹ወሲባዊ› አስተያየት ለሚሰጠው፣ ለሚማታው…ለዚህ ሁሉ ነውረኛ ሰው የምትሸማቀቀው ሴቷ ናት። የተሰረቀ ሰው ነው ወይስ ሌባ ነው ማፈርና መቀጣት ያለበት?

ይፈር! ጩኺ! ዝም አትበይ! ዝም አንበል! ግፊያውን ተጠቅሞ አጓጉል ንክኪ ለማድረግ ሲሞክር ጮክ ብለሽ ተናገሪ፤ ሰው ይስማ! ‹ተው! እጅህን ሰብስብ!› ብለሽ ድምጽ አሰሚ። ተሳቅቀሽ አትቆይ፤ አትታገሺ! አትቻይው! ጮክ ብለሽ ተናገሪው። ጩኸትሽ ያልገባው ሰው በኋላ ይገባዋል፤ የገባው ሰው ደግሞ ተላካፊውን ያሳፍረዋል። ሌላ ቦታ ቢደግመው እህትሽ እንደዛው ታሸማቅቀዋለች። አንቺም እኔም ይህን ብናደርግ፣ እርስ በእርሳችን እየተጠባበቅን ነው ማለት ነው። አይመስልሽም?


ቅጽ 4 ቁጥር 188 ሰኔ 4 2014
መቅደስ ቹቹ

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here