የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የመመስረቻ መስፈርቱን ላሟሉ ስምንት አዳዲስ ባንኮች ፈቃድ መስጠቱን አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ በፋይናንስ ዘርፍ ተግባራዊ እየተደረጉ ያሉ ለውጦችን ተከትሎ በርካታ ባንኮች የመመሥረቻ ፈቃድ ለማግኘት ጥያቄ እያቀረቡ መሆኑን ገልጿል።
ባንኩ ባለፈው ጥቅምት ወር ባንክ ለመመሥረት የሚያስፈልገው ዝቅተኛ የካፒታል መጠንን ከ500 ሚሊዮን ወደ 5 ቢሊዮን ብር ከፍ ማድረጉ የሚታወስ ሲሆን፣ አጠቃላይ መስፈርቱን ላሟሉ ፈቃድ እየተሰጠ መሆኑ ተጠቅሷል።
በዚህ መሠረት የመመሥረቻ ፈቃድ ከጠየቁ 25 አዳዲስ ባንኮች መካከል ብሔራዊ ባንክ ያወጣውን መስፈርት አሟልተው ለተገኙ ስምንት ባንኮች ፈቃድ መስጠቱ ነው የተነገረው።
በብሔራዊ ባንክ ፈቃድ ካገኙ ስምንት ባንኮች በተጨማሪ ሦስት ባንኮች ፈቃድ የማግኘት ሂደቱን እያጠናቀቁ በመሆናቸው፣ ሦስት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ፈቃድ እንደሚያገኙ ተገልጿል።
ብሔራዊ ባንክ ከቅድመ ማመልከቻ ሂደት ጀምሮ ፈቃድ ከተሰጠ በኋላ ቁጥጥር የሚያደርግ ሲሆን፣ የምሥርታ ሂደቱ ካልተሳካ ለባለአክሲዮኖች ገንዘባቸው ተመላሽ እንደሚሆን አመላክቷል።
ቅጽ 4 ቁጥር 188 ሰኔ 4 2014


