ኤስ ኦ ኤስ የሕጻናት መንደር በጦርነቱ ምክንያት ከፍተኛ ሰብዓዊ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ድጋፍ የሚውል የ145 ሚሊዮን ብር ፕሮጀክት ባሳለፍነው ሐሙስ ሰኔ 2/2014 በስካይ ላይት ሆቴል በተካሄደ መርሃ ግብር በይፋ አስጀምሯል።
ፕሮጀክቱ በቀጣይ ኹለት ዓመታት ውስጥ የሚተገበር ሲሆን፤ ኸርማን ገማንደር ፈንድ ደችላንድ ከተሰኘና በጀርመን አገር ከሚገኝ የኤስ ኦ ኤስ ድርጅት በተገኘ የ4 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ እንደሚተገበር በኢትዮጵያ የኤስ ኦ ኤስ የሕጻናት መንደር ዋና ዳይሬክተር ሳህለማርያም አበበ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ እንደተናገሩት፤ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ከሚገኙ ኤስ ኦ ኤስ ድርጅቶች የ6 ነጥብ 72 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ የተጠየቀ ቢሆንም፤ ለጊዜው ከኸርማን ገማንደር ፈንድ ደችላንድ በተገኘው የ4 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ ፕሮጀክቱን ለማስጀመር ዕቅድ ተይዟል።
ፕሮጀክቱ በአሁኑ ሰዓት በአማራ ክልል በሚደረግ የ145 ሚሊዮን ብር ወይንም የ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ ይጀመር እንጂ፤ በቀጣይ በትግራይ እና አፋር ክልሎች ለሚገኙ እና በጦርነቱ ምክንያት ከፍተኛ ሰብዓዊ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ቀሪው 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ዩሮ ድጋፍ ተደራሽ እንደሚሆን ሳህለማርያም ጨምረው አስረድተዋል።
በዚህም መሠረት በሰሜን ሸዋ፣ በሰሜን ወሎ፣ አድዋ፣ መቀሌ እና ምሥራቅ ሀረርጌ ዞኖች የሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች የፕሮጀክቱ ተጠቃሚዎች መሆናቸውን የኤስ ኦ ኤስ የሕጻናት መንደር በኢትዮጵያ የሰብዓዊ ድጋፍ ሥራዎች አስተባባሪ ቢንያም አስፋው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ በክልሎቹ በተሠራ የፍላጎት ዳሰሳ ጥናት ላይ ተመሥርቶ መቀረፁን የተናገሩት ቢንያም፤ ድጋፉም በክልሎቹ ለሚገኙና አስቸኳይ ድጋፍ በሚያስፈልጋቸው የተመረጡ ወረዳዎች ለሚገኙ ሰዎች፤ የምግብ እርዳታ፣ የመድኃኒትና የሕክምና ቁሳቁሶች ድጋፍ፣ የትምህርት መገልገያ መሣሪያዎች ድጋፍ እንዲሁም ለገበሬዎች ዘር እና ለእርሻ የሚውሉ በሬዎች ማቅረብን እንደሚያካትት ገልፀዋል።
ቅጽ 4 ቁጥር 188 ሰኔ 4 2014


