በሶማሌ ክልል በድርቅ የተራቡ ጦጣዎች ሕጻናትን ማጥቃት መጀመራቸው ተገለጸ

0
1211

በሶማሌ ክልል በተከሰተው ከፍተኛ ድርቅ የተራቡ ጦጣዎች ሕጻናትን ማጥቃት መጀመራቸውን ሴቭ ዘ ችልድረን ሪፖርት እንደደረሰው አስታወቀ።

ሴቭ ዘ ችልድረን ሰኔ 9/2014 የዱር እንሰሳት ሕጻናትን ማጥቃት ስለመጀመራቸው ባወጣው መግለጫ፣ በኢትዮጵያ የተከሰተው ድርቅ የዱር እንሰሳት ‹ከተፈጥሮ ውጪ› ሕጻናትን እንዲተናኮሉ ምክንያት ሆኗል ብሏል።

‹‹ጦጣዎች ከጫካ ወርደው እቃ የተሸከሙ ሕጻናትና ሴቶችን እያጠቁ ነው›› የሚለው የሴቭ ዘ ችልድረን መግለጫ፣ ሰዎች የያዙትን ነገር ውሃ ነው ብለው በማሰብ ነጥቀው ለመጠጣት ወይም ዕቃ ለመውሰድ ይሞክራሉ ብሏል።

የሕጻናት ቤተሰቦች ጦጣዎችን በዱላ ለመከላከል እየተገደዱ መሆኑን የሐረሪ ክልል፣ የሶማሌ ክልል እና የምሥራቅ ኦሮሚያ ክልሎችን ጨምሮ የምሥራቅ ኢትዮጵያ ክልሎች የሴቭ ዘ ችልድረን አካባቢ ኦፕሬሽን ሥራ አስኪያጅ አብዱራዛቅ አሕመድ ገልጸዋል። ከጦጣዎች በተጨማሪ ድኩላዎች ምግብ እና ውሃ ፍለጋ ባልተለመደ ሁኔታ ከሰዎች ቤት እየገቡ መሆኑንም ተናግረዋል።

አብዱራዛቅ በምሥራቅ ኢትዮጵያ ክልሎች ከ18 ዓመታት በላይ የኖሩ ሲሆን፣ በሶማሌ ክልል ከሰባት ዓመታት በላይ ሠርተዋል። የተከሰተው ድርቅ ጥንካሬ እና ቆይታ በአካባቢው በቆዩበት ጊዜ ታይቶ እንደማይታወቅ ጠቁመዋል።

በርካታ ቤተሰቦች የተራቡ ጦጣዎችን በዱላ ለመከላከል እንደተገደዱ ሪፖርት እየደረሰን ነው የሚሉት አብዱራዛቅ፣ የጦጣዎች ጥቃት ሁኔታው አስፈሪ ነው ብለዋል። በተለይ በዳዋ እና በሸበሌ አካባቢዎች በድርቁ በተጎዱ ቦታዎች ላይ ከተፈጥሮ ውጭ የሆነ ባህሪ እያሳዩ ነው ብሏል። እስካሁን በልጆች ላይ ጉዳት እንዳልደረሰባቸው የገለጹት ሥራ አስኪያጁ፣ ነገር ግን ሕዝቡ ወደፊት ምን እንደሚያመጣ ስጋት ገብቶታል ብለዋል።

‹‹ሁኔታው ጦጣዎች ብቻ ሳይሆኑ የተራቡ ድኩላዎች እንኳን ቤት እየወረሩ ነው። በሰዎች ጠረን የሚሮጡ የዱር አራዊት አሁን መሄድ አሻፈረኝ አሉ። ሰዎችን ያበላሻሉ እና ውሃ እና የሚበላ ነገር ለማግኘት ወደ ቤት ይገባሉ። ለመኖር ሲሉ ብቻ ሳይፈሩ ወደ መንደሮች ይመጣሉ›› ሲሉ ሥራ አስኪያጁ ሁኔታውን አብራርተዋል።

ሴቭ ዘ ችልድረን በመግለጫው፣ የአገር ሽማግሌዎች አሁን የተከሰተውን ድርቅ በእድሜያቸው ካጋጠማቸው ድርቅ ጋር ሲያነጻጽሩ እንዲህ ዓይነት የከፋ ድርቅ ሲያጋጥመን ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ማለታቸው ተጠቅሷል። ጦጣዎች ማኅበረሰቡ ውስጥ ገብተው ሕጻናትን ማጥቃት የጀመሩት ከሦስት ወራት በፊት ሲሆን፣ ድኩላዎች ደግሞ ምግብ ፍለጋ ወደ ሰዎች ቤት መግባት መጀመራቸውና ድርቁ እንስሳት ከተፈጥሮ ውጪ የሆነ ተግባር እንዲጀምሩ አድርጓል ብሏል።

በምሥራቅ አፍሪካ የተከሰተው ድርቅ በ40 ዓመታት ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ሲሆን፣ ድርቁ በሶማሊያ እና ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ የረሃብ ቀውስ አስከትሏል።

በኢትዮጵያ ኦሮሚያ፣ ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፣ ሶማሌ እና ደቡብ ምዕራብ ክልሎች ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ተብሏል። 185 ሺሕ የሚጠጉ ሕጻናት ገዳይ በሆነ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እየተሰቃዩ ነው ተብሎ እንደሚገመትም ሴቭ ዘ ችልድረንን ጠቅሶ ዴይሊ ሜል ዘግቧል። ሴቭ ዘ ችልድረን የብሪታንያ መንግሥት እርዳታ ወደ ኢትዮጵያ እንዲልክ መጠየቁንም ደይሊ ሜል አስነብቧል።

ድርቁ በከፋባቸው በሶማሊያ፣ በኬንያ እና በኢትዮጵያ አካባቢዎች አንድ ሰው በየ48 ሰከንዱ በረሃብ እየሞተ ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ሕጻናት በተመጣጠነ ምግብ እጥረት እየተሰቃዩ መሆናቸውን በጎ አድራጎት ድርጅቱ ሴቭ ዘ ችልድረን በመግለጫው አስታውቋል። ወደ 30 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ወይም ሩብ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰብዓዊ እርዳታ ያስፈልገዋል ሲልም አክሏል።

በድርቁ ምክንያት የቤት እንስሳት እልቂት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ሲሆን፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ምግብና ውሃ ፍለጋ ቤታቸውን ለቀው እንዲወጡ አድርጓል።


ቅጽ 4 ቁጥር 189 ሰኔ 11 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here