መነሻ ገጽሕይወት እና ጥበብየተጓዥ ማስታወሻበጦር መሣሪያ ሳጥን የተጠለሉ ነፍሶች

በጦር መሣሪያ ሳጥን የተጠለሉ ነፍሶች

ይህ የጉዞ ማስታወሻ በቁጥር 187 ‹በጦርነት የቆዘሙ ከተሞች› ከሚለው የቀጠለ ሲሆን፣ በዚህ ክፍል ከሚሴንና የኢንዱስትሪ ከተማ የሆነችውን ኮምቦልቻን አቆራርጠን ወደ አፋር ክልል አብረን እንጓዛላን። በአፋር ክልል ጉዟችን በጦር መሣሪያ ሳጥን የተጠለሉ ነፍሶችና ወና የሆኑ የአፋር ከተሞችን እንቃኛለን።

ወደ አፋር ክልል የማደርገው ጉዞ ጦርነቱ ከተገታባት የሽዋ ደብረ ሲና ከተማ እስከ ከሚሴ ያለውን ሁኔታ፣ በእጅጉ የጦርነትን አስከፊነት በወሬ ሳይሆን በተግባር ያስመከረ ነው ማለት ይቻላል። በጉዞዬ ከደብረ ሲና እስከ አጣዬ በመሀል አስፋልት ላይ ተቃጥለው የጦርነቱ ሰለባዎች የሆኑ የቆሙ ተሽከርካሪዎችን፣ እንደተመከትኩት ከሚሴ እስከ ኮምቦልቻ ተመሳሳይ ነው።

ከሚሴ በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ ልዩ ዞን መቀመጫ ስትሆን፣ ከአዲስ አባባ በ325 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ መጠነኛ ሙቀት የማያጣት ከተማ ናት። ከሚሴ የሕወሓት ኃይሎች እና ራሱን “የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት” ብሎ የሚጠራው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “ሸኔ” ተብሎ በሽብርተኝነት የተፈረጀው ታጣቂ ኃይል የተገናኙባት ከተማ ናት።

ከተማዋ እንደሌሎች ከተሞች ጉዳት ማስተናገዷ ባይቀርም፣ እንደ አጣዬና ሸዋሮቢ የከፋ ጉዳት አልደረሰባትም። ምንም እንኳን በቤቶችና በሕንፃዎች ላይ የከፋ ጉዳት ባይደርስም፣ የተቃጠሉ መኪኖች ሰለባ አሁንም በመሀል አስፋልት ላይ ይታያሉ። መሀል አስፋልት ላይ የተቃጠሉና የውስጥ እቃቸው ተወስዶ የቆሙ ከትንሽ እስከ ትልቅ ተሽከርካሪዎች ከደብረ ሲና እስከ ከሚሴ ባሉበት እንደቆሙ ናቸው።

ወደ አፋር ክልል ለመጓዝ ከከሚሴ የተነሳሁት ረፋድ አራት ሰዓት አካባቢ ነበር። የጦርነት ሰላባዎችን በየመስመሩ እየቃኘሁ፣ የኢንዱስትሪ መንደሯ ኮምቦልቻ ከደረስኩ በኋላ ወደ አፋር ክልል የሚሄደው ተረኛ መኪና ሰው አጥቶ እየጠበቀ ነበር።

ወደ አፋር ክልል የሚያቀናው ተረኛ መኪና ተሳፋሪ አልሞላለትም። ገና ከአምስት የማይበልጡ ሰዎች ናቸው በሰዓቱ የነበሩት፣ አጋጣሚውን ተጠቅሜ ኮምቦልቻን ለማየት ሻንጣዬን መኪና ውስጥ አስቀምጬ ወደ ከተማ ወጣሁ። ገና ከመናኸሪያ እንደወጣሁ መሀል አስፋልት ላይ ስፔርፓርቱ ተወስዶ የቆመ ሲኖ ትራክ ተመለከትኩ። በእግሬ ከተማዋን ተዘዋውሬ ስመለከት ከዚህ በፊት የማውቃት ደማቋ ኮምቦልቻ ጠባሳዋን ማጥፋት ባትችልም ወደ ወትሮው እንቅስቃሴዋ የተመለሰች ትመስላለች።

የኢንዱስትሪ መንደሯ ኮምቦልቻ ኢንዱስትሪዎቿ የተዘረፉባት፣ የወደሙባትና በውስጧ አቅፋ የያዘቻቸው የኢንዱስትሪ ሠራተኞችና ነዋሪዎቿ የተፈናቀሉባትና ጉዳት ያስተናገዱባት ከተማ መሆኗን አሁንም ታሳብቃለች። የወደሙ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ ለመግባት ጥረት እያደረጉ ቢሆንም፣ ሠራተኞቻቸውን ሙሉ በሙሉ መልሰው ማቀፍ እንዳልቻሉ የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ መግለጹ የሚታወስ ነው።

ኮምቦልቻ ላይ ከኹለት ሰዓት በላይ ቆይቼ፣ ወደ አፋር የማደርገውን ጉዞ ከሚሴንና የኢንዱስትሪ መንደሯን ኮምቦልቻን አቆራርጦ ሌላ የጦርነት ጠባሳ ወዳስተናገዱ አፋር አካባቢዎች ቀጥሏል። ከኮምቦልቻ በ202 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው የአፋር መዲና ሰመራ ገብቶ ለማደር የማደርገው ጉዞ፣ በጠራራ ፀሐይ ነበር የተጀመረው።

በዚያ ጠራራ ፀሐይ ወደ አፋር ክልል መግባት እንደኔ ለበረሃ አዲስ ለሆነ ሰው ከባድ ነበር። መኪና ውስጥ የተዋወኩት ከአዲስ አበባ ወደ ሎጊያ የሚያቀና ወጣት፣ ገና ከኮምቦልቻ ስንወጣ አፋር የምሄደው ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን ስነግረው “ተፈርዶብሃል” ነበር ያለኝ። ሙቀቱን አትችለውም ማለቱ ነው። እንዳለውም ሙቀቱ ቀላል አይደለም።

ባቲን አልፈን አፋር እንደገባን አብሮኝ የነበረው ልጅ “ተመልከት” እያለ፣ በግራ በቀኝ የጦርነት ሰላባ የሆኑ አፋር ድክዬ መንደሮችን ያሳየኝ ጀመር። ልጁ የአፋር ልጅ ስለነበር እያንዳንዱን ቦታ ያውቀዋል። አፋር አየር ንብረት ሞቃታማ ቢሆንም፣ ሙቀቱን ረስቼው በጦርነቱ የተጎሳቆሉ ከተሞች ጉዳት ቀልቤን ስቦታል።

በጦርነቱ የተቆሉ የአፋር መንደሮች በግራ በቀኝ እየተመለከትንና እያዘንን፣ አብሮን የነበረው ልጅ ስለ ከተሞቹ ማብራሪያ እየሰጠኝ ከፍተኛ ውጊያ የተደረገባት ካሳጊታ ደረስን። ካሳጊታ በተለይ ሕወሓት ከተቆጣጠራት በኋላ ከፍተኛ ውጊያ ተደርጎባታል።

ካሳጊታ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጦርነቱን ለመምራት ወደ ግንባር መዝመታቸውን ይፋ ያደረጉባት አካባቢ ስትሆን፣ እስከ አሁን በጉዞዬ ካየኋቸው የጦርነት ጠባሳዎች በእጅጉ የተለየ ጠባሳ አርፎባታል። በተለይ ከፍተኛ ጦርነት እንደተካሄደ የሚመሰክሩ በርካታ ታንኮች፣ የመከላከያ ተሽከርካሪዎች በዚያ በረሃ በየግራሩ ስር ተቃጥለው ይታያሉ።

ከአፋር ክልል መዲና ሰመራ በ140 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ካሳጊታ ከተማ፣ ፈራርሳና ወድማ እንደነበር የሚያሳዩ ደማቅ ሰላባዎች በውስጧ ይዛለች። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በካሳጊታ ግንባር ዘምተው ጦሩን መምራት መጀመራቸውን ካበሰሩ በኋላ ነጻ የወጣችው ካሳጊታ፣ ከታንክ እስከ ጥይት ሳጥን በየመስመሩ ዳር ተሰድረውባታል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዘመቱባት ካሳጊታ ግንባር ነጻ ስትወጣ የመንግሥት ሚዲያዎች “ሰበር የድል ዜና” እያሉ የካሳጊታን ግንባር ምሽግ መሰበርንና የአካባቢው ነጻ መውጣት ሲዘግቡ ብዙዎቻችን ካሳጊታን አውቀናታል። ከተማዋ ነጻ መውጣቷና ጉዳት ማስተናገዷ ከተነገረ በኋላ፣ ስለ ካሳጊታ ሁኔታ በሚዲያም ይሁን በሌላ በሌላ መንገድ ሲወራ አይደመጥም።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ መዝመትና ”ሰበር ድል ዜና” ሥሟ ተደጋግሞ የተነሳው ካሳጊታ፣ አሁን ላይ ማንም ስላለችበት ሁኔታ ባይሰማም በጦር መሣሪያ ሳጥን የተጠለሉ ነፍሶች መከተሚያ ሆናለች። ካሳጊታ ከፍተኛውን ውጊያ አስተናግዳ ነጻ ከወጣች በኋላ ነዋሪዎቿ፣ ወደ ቀያቸው ተመልሰው እየኖሩ ነው።

የሚኖሩበት ሁኔታ ግን በእጅጉ እንግዳ ለሆነ ሰው ያሳቅቃል። ነዋሪዎቿ ሕይወታቸውን የሚመሩት፣ የወደሙ ቤቶቻቸውን ትተው በጦር መሣሪያ ሳጥን ጎጆ ቀልሰው ነው። ነገሩ የሆነው ከሆነ በኋላ ሕይወትም መቀጠሉ ግድ ሆኖባቸው በጦር መሣሪያ ሳጥን የተጠለሉ የካሳጊታ ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች መሠረታዊ ኑሮ የሚኖሩበት ሁኔታ የሚያመቻችላቸው አካል ይሻሉ።

- ይከተሉን -Social Media

በካሳጊታና አካባቢዋ የሚኖሩ ዜጎች ኑሯቸው ምድረ በዳ የሆኑ መንደሮች መሆኑ በእጅጉ ያሳዝናል። አፋሮች መጠለያ ለመሥራት ብዙ ወጪና ቁሳቁስ አያስፈልጋቸውም። ወትሮውንም ኑሯቸውን የሚመሩት በቀላሉ በሚቀልሷቸው ጎጆዎች ነው። ከጦርነት በኋላ ግን በጦር መሣሪያ ሳጥን ውስጥ ለመጠለል ተገደዋል።

ከካሳጊታ ወደ ባቲ፣ ኮምቦልቻና ደሴ የሚያልፉ እንዲሁም ከኮምቦልቻና ከደሴ ወደ አፋሯ መዲና ሰመራ የሚያቀኑ ተጓዦች አረፍ ብለው ሻይ፣ ቡና እና ቁርስ የሚያደርጉባትም እንደነበረች አብሮን የነበረው የአፋር ወጣት አጫውቶኛል። አሁን ላይ በመሃሏ የሚያልፉ ተጓዞች ካሳጊታ ላይ አርፈው ሻይ ቡና የሚሉባት መሆኗ ቀርቶ አልፎ ለመሄድ እንኳን በጦርነት መሣሪያ ሳጥን ጎጇቸውን የቀለሱ ነዋሪዎቿና በየቦታው ተቃጥለው የቆሙ ታንኮች ያሳቅቃሉ።

ተባብሮ መኖር አፋሮች ዘንድ እጅግ ትልቅ ክብር የሚሰጠው ነገር መሆኑ በተደጋጋሚ ሲነገር ሰምቻለሁ። አብሮኝ የነበረው ወጣት እንደነገረኝ ካሳጊታም ነዋሪዎቹ ተባብረው ሠርተው እርስ በእርሱ ተጋግዘውና ተከባብሮ የሚኖርባት የፍቅር ከተማ ነበረች። ሞቃቷ ካሳጊታ በሽብር ቡድኑ ወራሪ የእብሪት ድርጊት የቀደመ ድምቀቷን ተገፋ በፍርስራሽና በቃጠሎ የተሞላች ሞገሷን ያጣች ከተማ ሆናለች።

የሕወሓት ኃይሎች ካሳጊታን ተቆጣጥረው በቆዩባቸው ጊዜያት ከግለሰብ እስከ መንግሥት ንብረት ዘረፋና ውደመት መፈጸመቸው ሲነገር ነበር። በካሳጊታ እንደታዘብኩት ሱቅና ምግብ ቤቶችን ጨምሮ የሕዝብና የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ጤና ጣቢያ፣ ትምህርት ቤት እና መኖሪያ ቤቶች በከባድ መሣሪያ ወድመዋል።

የከተማዋ ነዋሪዎች ኑሯቸውን እንደ ምንም እየገፉ ነው። ይሁን እንጂ ቤት ንብረታቸውን ያጡና ከተማቸው ወደ ፍርስራሽነት የተቀየረችባቸው የካሳጊታ ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች ኑሯቸውን በሀዘን ጥላ ሥር እንዲመሩ አስገድዷቸዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 189 ሰኔ 11 2014

ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች