በምንጃር ሸንኮራ ከ700 ሺሕ ብር በላይ የሚገመቱ የእርሻ በሬዎች በሸኔ ተዘርፈዋል ተባለ

0
1210

በሰሜን ሸዋ ዞን ምንጃር ሸንኮራ አረርቲ ወረዳ አሞራ ቤት ተብሎ በሚጠራው ሥፍራ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀው ሸኔ ከ700 ሺሕ ብር በላይ የሚገመቱ በሬዎችን እንደዘረፈ የአይን እማኞች ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።

ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱ የአካባቢው ነዋሪ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት ከሆነ፤ ባለፈው ሳምንት፣ አሞራቤት ዙሪያ ነጭ ሳር ፍናናጆ አካባቢ ታጣቂ ቡድኑ ከ20 በላይ የሚሆኑ የአርሶአደር ከብቶችን ዘርፏል ብለዋለ።

አሁን ባለው የገበያ ሁኔታ መሰረት በሬዎቹ ለገበያ ቢቀርቡ ከ40 እሰከ 50 ሺሕ ብር ድረስ ይሸጣሉ ያሉት የአዲስ ማለዳ ምንጭ፣ የተዘረፉት ከብቶች በጠቅላላ ከ700 እስከ 800 መቶ ሺሕ ብር ማስገኘት እንደሚችሉም አብራርተዋል።

በአካባቢው የነበሩ ሚሊሻዎችና ታጣቂዎች በሬዎቹን ለማስለስ ሙከራ ቢያደርጉም ሳይሳካላቸው የቀሩ ሲሆን፣ ከሸኔ ጋር ባደረጉት ውጊያ የተወሰኑ መሳሪዎችን እንደማረኩም የአዲስ ማለዳ ምንጭ ተናግረዋል።

የተዘረፉት በሬዎች ለእርሻ አገልግሎት የሚውሉ መሆናቸውን የተገለጸ ሲሆን፣ አሁን ወቅቱ የዘር መዝርያ መሆኑን አስታውሰው ድርጊቱ ከብቶቻቸውን ባጡት አርሶ አደሮች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማስከተሉ የማይቀር ነው ተብሏል።

ፍናናጆ አካባቢ በነበረ ድንገተኛ ጥቃት ሸኔ አንድ ነዋሪ ማቁሰላቸውን ተከትሎ፤ ሰሞኑን የአካባቢው ሰላም ደፍርሶ ነበር ተብሏል።
ታጣቂ ቡድኑ ከዚህ በፊት ኹለት ጊዜ ነዋሪዎቹን የማጥቃትና እንስሳቶችን የመዝርፍ ሙከራ ማድረጉ የተገለጸ ሲሆን፤ ይህን ተከትሎም የአካባቢው ነዋሪዎች ስጋት ውስጥ መሆናቸውም ተመላክቷል።

ሸኔ የሚገኘው በዞኑ ልዩ ልዩ ስፍራዎች ከማህበረሰቡ ጋር ተሰባጥሮ በመሆኑ ጥቃት የሚያደርሰው እንዲሁ በደፈጣ ነው የተባለ ሲሆን፤ ሳማ ሰንበት ተብሎ በሚጠራው ሥፍራም ባሳለፍነው ሳምንት አዲስ ተመራቂ ታጣቂቆች እንዳስመረቀ ነው የተገለጸው።

ታጣቂ ቡድኑ ወታደሮችን ባስመረቀበት ወቅት ሌላ ጥቃት የመሰንዘር ሙከራ ቢያደርግም፣ በአካባቢው የነበሩ ሚሊሻዎችና ታጣቂዎች ባደረጉት መከላከል ሌላ ጉዳት አላስከተለም ተብሏል። ቢሆንም ግን ይህን ተከትሎ የሳማ ሰንበት ዙሪያ ነዋሪዎች ስጋት ውስጥ ናቸው ተብሏል።

እስካሁን መንግሥት ጥብቅ እርምጃ ባለመውሰዱ ታጣቂ ቡድኑ በዞኑ እየተዘዋወረ ወታደሮቹን እያሰራጨ ሲሆን፤ ለአብነትም በባቲ አካባቢ ወደ 300 የሚደርሱ ታጣቂዎች መታየታቸው ተጠቁሟል።

ይህን ተከትሎም በባቲ ቅዳሜ ገበያ አካባቢ ማህበረሰቡ ላይ ጥቃት የማድረስ ሙከራ አድርገው እንደነበርም አመላክተዋል። በመሆኑም ይህ አካባቢ የወሰን አካባቢ በመሆኑ የማህበረሰቡ ፍራቻ ከእስካሁኑ ይበልጥ ጨምሯል ነው የተባለው።

በመሆኑም አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ነዋሪዎቹ “የእስካሁኑ ጥቃት ይበቃል። በክረምት ወቅት መንቀሳቀስ እንኳ ያስቸግራል። የሚመለከተው አካል አፋጣኝ መፍትሄ ይስጠን” ሲሉ አሳስበዋል።

በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ አሞራ ቤት ቀበሌ አውራ ጎዳና ከዚህ በፊት ታጣቂ ቡድኑ ጥቃት ማድረሱ የሚታወስ ነው።


ቅጽ 4 ቁጥር 189 ሰኔ 11 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here