መነሻ ገጽዜናወቅታዊክረምት እና ጎርፍ

ክረምት እና ጎርፍ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገራት ጎርፍ በአብዛኛው በይበልጥና በሰፊው የሚከሰተው ክረምት ተብሎ በሚጠራው ዝናባማ ወቅት ነው። አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በክረምት ወራት ሊከሰት የሚችለው የጎርፍ መጠንና የሚያስከትለው አደጋ ከሌሎች ወቅቶች በተለየ መልኩ ላቅ ያለ ነው። በኢትዮጵያም 88 በመቶ የሚሆነው የጎርፍ መጠን የሚከሰተው በክረምት ወራት መሆኑን በ2008 በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ በተዘጋጀ ጥናት ተብራርቷል።

ክረምት ከሰኔ አጋማሽ “ሀ” ብሎ ጀምሮ በቀጣዮቹ ኹለት ወራት እየተፈራረቀ የሚቆይ ሲሆን፤ በመጀመሪያው ወቅት ሊደርስ ከሚችለው የጎርፍ መጠን ይልቅ በሐምሌና ነሐሴ የሚመጣው ጎርፍ የበረታ ነው። ይህ የሚሆንበት ዋነኛ ምክንያት ለወራት ውሃ ተጠምቶ የኖረው መሬት ጥማቱን ካረካ በኋላ እና ክረምቱ በይፋ በሚጀምርበት ወቅት (ሐምሌ እና ነሐሴ) የጎርፍ መጠኑ ስለሚጨምር መሆኑ ይነገራል።

ይህ ማለት ግን በሰኔ ጎርፍ የለም ማለት አይደለም። ክረምት ሲገባ ጎርፍ ሊኖር አይችልም ከማለት ይልቅ በመጀመሪያ ጊዜ የሚከሰተው ጎርፍ ድንገታዊ በመሆኑ ይበልጥ ለጉዳት የሚዳርግ መሆኑንም መገንዘብ ሌላኛው ብልሃት ነው ሲሉ የዘርፉ ምሁራን በአጽንኦት እየተናገሩ ይገኛሉ።

መጀመሪያ በሚዘንብ ድንገተኛ ዝናብ በሚደርስ የጎርፍ አደጋ በገጠሩም ሆነ በከተማው ጉዳቶች ተስተናግደዋል። በገጠሩ አካባቢ መጀመሪያ በሚጥለው ያልተጠበቀ ዝናብ በወንዝ ውስጥ የተሰማሩ በርካታ የከብት ጠባቂዎች፤ ከብቶች በጎርፍ ሲንኮታኮቱ ይስተዋላል። በከተማውም ቢሆን ከሰው ሕይወት መጥፋት እስከ መሠረተ ልማት ግንባታ ውድመት ተከስቷል።

ይሁን እንጂ፣ ክረምት ኢትዮጵያ ዓመት ጠብቃ የምታገኘው ተናፋቂ ወዳጇ እንጂ ጉዳቱ ለብቻው ጎልቶ የሚታይበት አይደለም። ከጉዳቱም ባሻገር የተቆራመደው መሬትና እጽዋት ውበት የሚለግሱበት፤ አርሶ አደሩ ዘርቶ የሚያበቅልበት፤ ቡቃያው ለፍሬ የሚበቃበት፤ እንስሳት ከደረቅ መኖ ይልቅ በለመለመ መስክ የሚሰማሩበት ልዩና ተወዳጅ ወቅት ጭምር ነው።

ሆኖም ጥቅሙን ብቻ ማግኘት እንዳልተቻለ በየዓመቱ በሰው፤ በእንስሳት፤ በንብረት፤ በመሠረተ ልማትና በግንባታ ላይ የደረሱ አደጋዎች ሕያው ምስክር ናቸው። አደጋውን ለመቀልበስ በዘርፉ የተሰማሩ ባለድርሻ አካላት ወቅቱን ጠብቀው ቅድመ ጥንቃቄ ቢያደርጉም በየዓመቱ የሚደርሰው አደጋ ግን ቀጥሏል።

ክረምት በይፉ ሳይጀምር እንኳ ሰኔ 1/2014 በመዲናዋ በዘነበው ድንገተኛ ዝናብ በጎርፍ ተወሰደ የተባለውና ይህ ዘገባ እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስ ያለበትን ማወቅ ባልተቻለው በአራት ዓመት ሕጻን (ሕጻን ማርኮን) የደረሰው አደጋ የቅርብ ጊዜ ክስተት ነው።

በርካታ የዓለም አገራት በየወቅቱ የሚደርሱ ቀላል የማይባሉ የጎርፍ አደጋዎችን ከከተማ እስከ ገጠር ባሉ ግዛቶቻቸው አስተናግደዋል። በዚህም ከህልፈተ ሕይወት እስከ ንብረት ውድመት የሚደርስ ቀላል የማይባል አስከፊ ችግር ስለማስተናገዳቸው ያለፉትን ጊዜያት መለስ ብሎ ማየትን ይጠይቃል።

ትውስታ
በኢትዮጵያ በሚገኙ ልዩ ልዩ ስፍራዎች ጎርፍ ቀላል የማይባሉ ጉዳቶችን እንዳስከተለ በየወቅቱ የወጡ የተለያዩ መረጃዎች ይጠቁማሉ። በሰዎች፣ በንብረትና በመሠረተ ልማት ላይ ጎርፍ ጉዳት የሚያስከትለው በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን አፍሪካን ጨምሮ በተለያዩ የዓለም አገራት ጭምር ነው። ለአብነትም በ2012 የአፍሪካ አገራት ከሌሎቹ ዓመታት በተለየ በዝናብ ቢንበሸበሹም፤ ከህልፈተ ሕይወት እስከ መፈናቀል ድረስ ቀላል የማይባል ጉዳት በጎርፍ ምክንያት እንደደረሰ ጥናቶች ይጠቁማሉ።

የቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ማኅበራት ጥምረት የሆነው ዓለም ዐቀፉ ተቋም (አይ.ኤፍ.አር.ሲ) በ2012 ያወጣው መረጃ እንደጠቆመው፤ ብዙ የአፍሪካ አገራት ከተለመደው ለየት ባለ መልኩ ዝናብ ያገኙ ሲሆን፤ በዚህም ከአንድ ሚሊዮን በላይ በሚሆኑ ሰዎች ላይ የጎርፍ አደጋ ደርሷል። እንደ መረጃው ከሆነ፤ በዚሁ ዓመት በሰባት የአፍሪካ አገራት ብቻ ማለትም በኒጀር 363፤ በኬንያ 194፤ በሱዳን 99፤ በቻድ 10፤ በኢትዮጵያ ስምንት እንዲሁም በኡጋንዳ ስድስት በአጠቃላይ 680 ሰዎች ሞተዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ደቡብ ሱዳን 600 ሺሕ፤ ቻድ 120 ሺሕ፤ ኬኒያ 100 ሺሕ፤ ኡጋንዳ አምስት ሺሕ ዜጎች የተፈናቀሉ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ 200 ሺሕ፤ ሱዳን 500 ሺሕ፤ በኒጀር 88 ሺሕ ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው በጥናቱ ተረጋግጧል።

ጎርፍ ከሌሎች ችግሮች በተጨማሪ ለዜጎች ህልፈተ ሕይወት ምክንያት እየሆነ ዘመናት ቢቆጠሩም ችግሩን መቅረፍ የተቻለ አይመስልም። የጎርፍ አደጋ በኢትዮጵያ ዜጎች ላይ የሚያደርሰው ጉዳት በየዓመቱ እንደቀጠለ ነው።

የአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ንጋቱ ማሞ ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ የሕጻን ማርኮንን ጉዳይ አንስተው፤ አሳዛኝና አስደንጋጭ ክስተት ነው ብለዋል። እስከ አሁን የጎርፍ አደጋ ደርሷል ተብሎ ተነግሯቸው ሳያገኙት የቀረ ተጎጅ እንደሌለ አስታውሰው፣ ሰው በጎርፍ ተወስዶ አለመገኘቱ በእሳትና አደጋ ተቋም የመጀመሪያ ክስተት ነውም ብለዋል።

ታዲያ ክስተቱ ከጅምሩ በብዙዎች በኩል ስጋትን ፈጥሯል። በተለይም ጉዳቱ ደጋግሞ ያጠቃቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ቀድመው የድረሱልን ጥሪያቸውን እያስተላለፉ ነው። በርካቶች ስጋታቸውን የሚገልጹት በ2014 በሰኔ ወር በአራት ዓመቱ ሕጻን የደረሰውን ጉዳት፣ እንዲሁም በሌሎች የአፍሪካ አገራት ዘንድሮ እና ከአሁን በፊት በተለያዩ ወቅቶች የደረሱትን ክስተቶች መለስ ብለው በማስታወስ ነው።

በ2014 የጎርፍ አደጋ እየጀመረና ጥቃት እያደረሰ ያለው በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካና በዓለም አገራትም ጭምር መሆኑን በየወቅቱ የሚወጡ መረጃዎች ያመላክታሉ። ለአብነትም በሚያዚያ 2014 በደቡብ አፍሪካ በዘነበ ከባድ ዝናብ 400 ሰዎች ሕይወታቸው እንዳለፈ፤ 40 ሺሕ ገደማ ሰዎች ላይ ጉዳት እንደደረሰ፤ 13 ሺሕ 500 ቤቶች እንደወደሙ እና ወደ 300 ገደማ የሚሆኑ የትምህርትና የጤና ተቋማት አገልግሎት መለገስ አለመቻላቸውን የተለያዩ ሚድያዎች ዘግበዋል።

ወደኋላ መለስ ብለን መዲናችንን ስንዳስስ ደግሞ ባለፈው ዓመት በመካነ ኢየሱስ ሴሚናሪ በደረሰው የጎርፍ አደጋ የስምንት ሰዎች ሕይወት ማለፉ ይታወሳል። በየዓመቱ በሚከሰተው የጎርፍ አደጋ የሰዎች ሕይወት እያለፈ እንደሚገኝ ኢትዮጵያ በየዓመቱ የምታስተናግዳቸው አደጋዎች ያመላክታሉ።

- ይከተሉን -Social Media

በ2008 በኢትዮጵያ ተከስቷል በተባለ የጎርፍ አደጋ 72 ሰዎች የሞቱ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካካል ስድስት ሰዎች አስከሬን አልተገኘም። በዚህም 80 ሺሕ ዜጎች መፈናቀላቸው በወቅቱ በመንግሥት ሲገለጽ ነበር። በ2012 ከአዲስ አበባ በስተምዕራብ በምትገኘው ቡራዩ ከተማ በተከሰተ የጎርፍ አደጋ ዘጠኝ ሰዎች፤ ድሬዳዋ ለአንድ ሰዓት ባለማቋረጥ በዘነበው ዝናብ ቤት ደርምሶ በገባው ጎርፍ ሁለት ሰዎች መሞታቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

በአጠቃላይ ባለፉት ዓመታት በኦሮሚያ፤ በአፋር፤ በጋምቤላ፤ በአማራ፤ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እንዲሁም በሶማሌ ክልል በተከሰተው የጎርፍ አደጋ 10 ሚሊዮን 95 ሺሕ 350 ዜጎች ጎርፍ አደጋ እንደደረሰባቸውና 313 ሺሕ 179 ዜጎች መፈናቀላቸው ይነገራል።
በ2013 በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ 10 ሰዎች በጎርፍ አደጋ እንደሞቱ የተነገረ ሲሆን፤ በሌሎች የኢትዮጵያ ሥፍራዎችም የሰዎች ሕይወት አልፏል። በመሆኑም በየጊዜው የሚከሰተው የጎርፍ አደጋ ተጨምሮ ሲሰላ የብዙዎችን ሕይወት እንደነጠቀ መረዳት ይቻላል።

ስጋት
የጎርፍ አደጋ ስጋት ነጋ ጠባ የሚያሳስባቸው ሰዎችን ቢሆንም፣ በጎርፍ የሚጎዱት ግን እንስሳትና ግኡዛን አካላትም ጭምር ናቸው። በሰዎች ከሚደርሰው የጎርፍ አደጋ ይልቅ በእንስሳትና በግኡዛን አካላት የሚደርሰው ጉዳት የጎላ ባይሆንም፣ የሚያስከትለው ችግር ግን ቀላል እንዳልሆነ አንክሮ ሰጥቶ ማሰብ ጉዳዩን ለመረዳት ያስችላል።

በክረምት ወቅት ጉዳት ያደርሳል ተብሎ የሚፈራውና በብዛት ትኩረት የሚሰጠው የጎርፍ አደጋ ሆኖ ይስተዋላል። ሆኖም ግን በሰውና በእንስሳት፤ በንብረትና በመሠረተ ልማት ጉዳት የሚያደርሱ የመሬት መንሸራተትን የመሳሰሉ በርካታ የአደጋ መንስኤዎች ክረምቱን ተንተርሰው ይመጣሉ።

ጎርፍ ጉዳት የሚያደርሰው በሰዎች ሕይወት ላይ ብቻ ሳይሆን በንብረትም ጭምር ነው። እንስሳት፣ ድልድዮች፣ ሕንጻዎች፣ ተሽከርካሪዎች፣ የኤሌክትሪክ ገመዶች፣ ግድቦች፣ እፅዋት እና ሌሎችም የአደጋው ተካፋይ ናቸው።

በክረምት ወራት ድልድዮች ሲሰበሩ፤ እንስሳት በጎርፍ ሲወሰዱ፤ ተሽከርካሪዎች ሲሰጥሙ፤ ሕንጻዎች ሲደረመሱ፤ ግድቦች ሲፈነዱ፤ እፅዋት በጎርፍ ሲወሰዱ፤ ቤቶች ሲፈርሱ፤ የኤሌክትሪክ ገመዶች ተቆርጠው ሲወድቁ፤ ቡቃያዎች በደለል ሲጠፋ፤ ተዳፋታማ ማሳዎች በጎርፍ ሲሸረሸሩና ኢንዱስትሪዎች በመብራት እጦት ሥራቸው ሲስተጓጎል ተስተውሏል።

በኢትዮጵያ የክረምት ወቅት ከጎርፍ በተጨማሪ ሌሎች አደጋዎችም ለዓመታት እንደተከሰቱ በአንዳንድ ተቋማት የሚሰጡ መግለጫዎች ያሳያሉ። ለአብነትም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮምዩኒኬሽን ቢሮ ባለፉት ዓመታት ጎርፍ የመሬት መንሸራተት የቆሻሻ መደርመስ እና ሌሎች መሰል አደጋዎች በመዲናዋ አጋጥሟል ሲል ሰሞኑን በሰጠው መግለጫ አስቀምጧል።

ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ በሚገኙ የተለያዩ ክልሎች የሰው ሕይወት የታጣባቸው የጎርፍ አደጋዎች መከሰታቸው የሚታወስ ሲሆን፤ በዘንደሮው ዓመትም የሜትሮሎጂ ኢንስቲትዩት ከሰኔ አጋማሽ ጀምሮ ክረምት እንደሚገባና በክረምቱ ከባድ የጎርፍ አደጋ እንደሚኖር ከወዲሁ እያሳወቀ ነው።

- ይከተሉን -Social Media

ምን እየተሠራ ነው?
የተለመደው አደጋ እንዳይከሰት ለጎርፍ ተጠቂ የሆኑ ሥፍራዎችን በመለየት ቅድመ ጥንቃቄ እየተደረገ መሆኑን የአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ንጋቱ ማሞ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። በ2013 በተከሰተው የጎርፍ አደጋ የ10 ሰዎች ሕይወት አልፏል ያሉት ንጋቱ፤ ተመሳሳይ ችግር እንዳይደገም የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን አንስተው በቶሎ ማጠናቀቁ ተመራጭ ነው ብለዋል።

እንደ ባለሙያው ገለጻ ከሆነ፤ በ2014 የክረምት ወቅት በአዲስ አበባ የጎርፍ አደጋ ይደርስባቸዋል ተብለው የተለዩ 142 ቦታዎች ናቸው። በዚህም መሠረት በወንዝ ዳር ያሉ ሰዎች ቦታ እንዲቀይሩ፤ የተዘጉ ቱቦዎች እንዲፈተሹ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በየዓመቱ ሰው የሚነጥቀውን የጎርፍ አደጋ ለመከላከል የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ በየዓመቱ ቅድመ ዝግጅት ቢያደርጉም አደጋውን ከማስተናገድ ፈቀቅ አልተባለም። በዚህ ዓመትም ቢሆን ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነው ቢባልም ገና አለመጠናቀቁ እየተነገረ ነው። እንኳን ቅድመ ዳሰሳው ሳይጠናቀቅ፣ ተጠናቆም አደጋ ሳይከሰት ቀርቶ አያውቅም። እንደ ሚትሮሎጂ ኢንስቲትዩት ገለጻ ከሆነ፤ ቀድመው ሥራዎች አለመጠናቀቃቸው አደጋውን ሊያከብደው ይችላል የሚል ቅሬታ በበርካቶች ዘንድ እየተሰማ ነው።

ጎርፍ በየዓመቱ እንደሚከሰትና በንብረት ላይም ቀላል የማይባል ጉዳት እያስከተለ እንዳለፈ የዘርፉ ምሁራንም ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። ባለፈው ዓመት 25 የሚደርሱ ከባድ የጎርፍ አደጋዎች እንደተከሰቱ ያስታወሱት ንጋቱ፤ በዚህም 407 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ወድሟል ነው ያሉት።

በመሆኑም፣ ከባለድርሻ አካላት ጀምሮ ሁሉም ማኅበረሰብ ከወዲሁ ቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 189 ሰኔ 11 2014

ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች