የማዕድን ሚኒስቴር የማዕድናት ፍለጋ ፈቃድ ወስደው ለረጅም ጊዜያት በገቡት ውልና አቅርበው ባፀደቁት መርሀ ግብር መሠረት መስራት ባልቻሉ ኩባንያዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን አስታወቀ።
ፈቃዳቸው የተሰረዘው ኩባንያዎች ማዕድን ወደ ውጪ ለመላክ የብቃት ማረጋገጫ ምሥክር ወረቀትና ፈቃድ ወስደው ያለአግባብ ሲጠቀሙ የተገኙ መሆናቸውን የማዕድን ሚኒስትሩ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ባሳለፍነው ረቡዕ ሰኔ 15 ቀን 2014 በሰጡት መግለጫ ላይ አስታውቀዋል።
ኩባንያዎቹ በየደረጃው ባሉ ባለድርሻዎች ማስጠንቀቂያ ቢሰጣቸውም፣ በሚገባው መልኩ ወደ ልማት ባለመግባታቸው የ116 ኩባንያዎች የማዕድን ፍለጋ ፈቃድ መሠረዙን የማዕድን ሚኒስትሩ ተናግረዋል። በተጨማሪም በማዕድናት ምርት ፈቃድ ወስደው ነገር ግን በአግባቡ አልሰሩም የተባሉ የ6 ኩባንያዎች ፈቃድ መሰረዙንም አስረድተዋል።
ከወርቅ ማዕድናት ውጪ ያሉ ሌሎች ማዕድናት ወደ ውጪ ለመላክ የብቃት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት ወስደው ፈቃድ የተሠጣቸው ነገር ግን፤ በህጋዊ ሽፋን በኮንትሮባንድ ንግድ ላይ ተሠማርተው የተገኙ 850 የማዕድን ላኪዎች ፈቃድ መሠረዙንም ሚንስትሩ ተናግረዋል ። በአጠቃላይ 972 በማዕድን ምርመራ ፤ ምርትና ኤክስፖርት ዙሪያ ፈቃድ የወሰዱ ኩባንያዎች ፈቃድ ተሰርዟል።
በክልሎች በኩል የተሠጡ ፈቃዶች በዚህ ወር መጨረሻ ተገምግሞ ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ ከሥምምነት መደረሱም ተገልጿል። የተወሰደው እርምጃ በዘርፉ ጥሩ እየሠሩ የሚገኙትን የሚያበረታታና ሕገወጥ የሆኑትን ወደሕጋዊ መሥመር የማስገባት ፋይዳ እንዳለውም ተጠቁሟል።
ቅጽ 4 ቁጥር 190 ሰኔ 18 2014



