ደኅንነት ይቀድማል

0
1245

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

ዋናው ነገር ጤና እንደሚለው ብሂል፤ እንደ አገር እና እንደ ሕዝብ ዜጎች ያላቸውን የትኛውም ጥያቄ ለማንሳት በቅድሚያ የአገር ደኅንነት ወሳኝ መሆኑ አያጠያይቅም። ሰላም ከሌለ፣ ሰላምን አስከባሪና የዜጎችን ደኅንነት ጠባቂ ቸል ካለ፤ መብትን መጠየቅ በእርግጠኝነት ከቅንጦት ይቆጠራል።

ከሰሞኑ በወለጋ እንዲሁም ከዚህ ቀደሞም በተለያዩ ቦታዎች ግድያዎችና ጭካኔ የተሞሉ የንፁሐን ዜጎች ጭፍጨፋዎች ተፈጽመዋል። ጅምላ መቃብሮች እዛም እዚህም ታይተዋል። ለመሳም እንኳ የሚያሳሱ ሕፃናት ላይ ስለት አርፏል፤ እናቶችና ሴቶች በአሰቃቂ ሁኔታ ሕይወታቸውን ተነጥቀዋል። በኢትዮጵያ ይፈጸማል ብሎ ለማመን የሚቸግር ዘግናኝ ድርጊት ተፈጽሟል።

ከዚህ ቀደም በታሪክ ሆኗል ተብሎ ከሚሰማውና እውነት ነው ሐሰት ነው ብለው ከሚከራከሩበት ጉዳይ የላቀ፣ እጅግ ዘግናኝ ድርጊት እየተፈጸመ የዐይን እማኝ ሆነናል። የሰውነት ጥግ እና የሚዘመርለት የኢትዮጵያዊነት ከፍታ ከአፈር ተደባልቋል። ልብ ሰባሪ ክስተት የየእለት ዜና ሆኗል።

በዚህ ሁኔታ ውስጥ የሴቶችን መብት መጠየቅ እንደቅንጦት ሊቆጠር ይችላል። ምንም እንኳ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆኖም መንግሥት ስለችግኝ ማውራት የተወ ባይሆንምና ቅድሚያ ነገሩ ያ ሆኖ ቢታይም፣ ሕሊና ላለው ሰው አንዳንዴ የቡድን መብትን እንኳ በዚህ ወቅት መጠየቅ ያስጨንቃል። የሕፃናትን የመማርና አእምሮአቸውን ከክፋ የመጠበቅ መብትን ማንሳትም ‹እዬዬም ሲደላ!› የሚል ግብረ መልስ የሚያሰጥ ሊመስል ይችላል።

ይህ ሁሉ የሰላም መጉደል፣ የባለሥልጣናት ፍፁም ቸልተኛነትና ግድ የለሽነት ውጤት ነው። በዚህ ሁሉም ዜጋ ሰለባ መሆኑ እሙን ነው። በቀጥታ የጥቃት ሰለባ ከመሆን ባለፈ የመንፈስ ሕመምና ስብራት፣ ጭንቀትና ውጥረት ውስጥ ያለው ሕዝብ ቁጥርም ጥቂት አይደለም። ሴቶችና ሕፃናት ደግሞ የሚበረታውንና የማያባራውን መከራ ይቀበላሉ።

አሁን ላይ ወላጆቻቸውን በሞት የተነጠቁ ሕፃናት ቁጥር እጅግ በርክቷል። ሥራ አጥ ወጣት እልፍ ነው፤ ተፈናቅሎ በየመጠለያ ጣቢያው የሚገኘው ተቆጥሮ አላለቀም። በዚህ ከቀጠለ ደግሞ ገና ስጋት ያለውና ቀዬውን ጥሎ የሚወጣ ብዙ ዜጋ አለ። በዚህም ሁሉ ውስጥ ሴቶች ብዙ ሸክምን ተቀባይ ናቸው።

አሁን የሴቶች መብትን አቆይተን ሴቶችን ማጠንከርና ፈተናውን የሚቋቋሙበትን ኃይል ማስታጠቅ ያሻል። የሆነው ሆኗልና፤ ፍትህና እውነት ሰፍኖ እስኪታይ፤ ትውልድን ወልደው የሚያቀርቡ እናቶች ብርታትን ጥንካሬን ሊሰንቁ ይገባል። ለዛም የሥነልቦናም የአቅምም ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል። ነገ የሚሆነውን አናውቅም፤ ትላንት በሆነውም ላይ አንዳች እንኳ ሥልጣን የለንም፤ አሁን ግን ማድረግ የምንችለው ይህን ነው። ተፅናንተን ማፅናናት፤ በርትተን ማበርታትና የነገ ትውልድ እናቶችን ማገዝ።
መቅደስ ቹቹ


ቅጽ 4 ቁጥር 190 ሰኔ 18 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here