በአፋር ክልል እየተስፋፋ የመጣውን መጤ አረም በመጠቀም ኃይል ማግኘት የሚያስችል ፕሮጀክት በክልሉ አሚባራ ወረዳ በዛሬው ዕለት ይፋ ተደርጓል።
በመርሐ ግብሩ ላይም የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ፣ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ኢ/ር አይሻ መሀመድ፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል፣ የግብርና ሚኒስትር ዑመር ሁሴን፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እና ሌሎችም የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
የኬሚካል እና ኮንስትራክሽን ግብአቶች ምርምር ማዕከል የአካባቢ ጥበቃ ሙያ ደህንነትና ኢነርጂ ዳይሬክተር ዳዊት ዓለሙ እንደገለጹት፤ ፕሮጀክቱን ወደ ሥራ ለማስገባት በፈረንጆቹ ከ2015 ጀምሮ ዝግጅት ሲደረግ ቆይቷል። በአፋርና ሶማሌ ክልሎች 2 ሚሊየን ሄክታር መሬት ላይ አረሙ መከሰቱን ጠቁመው፣ አረሙን በማንሳትና በማቃጠል የኃይል ተጠቃሚ ለመሆን እየተሠራ መሆኑንም ገልጸዋል። ከኃይል ተጠቃሚነት ባለፈ አረሙን በማጽዳት መሬቱ ለምርት አገልግሎት እንዲውል የሚያስችል ፕሮጀክት መሆኑንም ነው የተናገሩት።
ዳይሬክተሩ አክለውም፣ ኢትዮጵያ ለፋብሪካዎች ግብአት የሚሆን የድንጋይ ከሰል ከውጭ ለማስገባት ከ300 እስከ 400 ሚሊየን ዶላር ድረስ ወጪ እንደምታደርግ ጠቁመው፤ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ብቻ በየዓመቱ 1 ሚሊየን ቶን የድንጋይ ከሰል እንደሚጠቀሙ አብራርተዋል። ከፕሮጀክቱ በሚገኘው ኃይል ከውጭ የሚገባውን የድንጋይ ከሰል እስከ 40 በመቶ ለመተካት ግብ መያዙን የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር አስታውቋል።
በ1970 አካባቢ ለአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ተብሎ ወደ አገር ውስጥ የገባው መጤ አረም በአፋርና ሶማሌ ክልሎች በርካታ አካባቢዎች በመስፋፋት ምርታማነት እያሳጣ መሆኑ ተገልጿል። መረጃዎች እንደሚጠቁሙት አንድ የመጤ አረም ተክል በአማካኝ በቀን እስከ 7 ሊትር ውሃ ከመሬት ውስጥ የመምጠጥ አቅም አለው። በአፋር ክልል ብቻ በመጤ አረሙ ምክንያት በዓመት ከ3 ነጥብ 1 ቢሊየን ሜትሪክ ኪዩብ በላይ ውሃ ይባክናል ተብሏል።
ቅጽ 4 ቁጥር 190 ሰኔ 18 2014



