ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ፈታኝና አስቸጋሪ ሁኔታ ወዴት አቤት ይባላል የሚያሰኝ ሆኗል። መንግሥትም ውሳኔዎቹና አካሄዶቹ ግልጽ ካለመሆናቸው በላይ፣ አስቀድሞ ገዢው ፓርቲ ከገባው ቃል አንጻር የተገኘ ምንም የለም። ሁኔታውን ለመረዳት የሚሞክር ቀና አሳቢ ቢሆን እንኳ፣ ነገሩ ለመረዳት የሚመች አልሆነም። በየእለቱና በየጊዜው የሚሰማው አሰቃቂ የሰዎች ጭፍጨፋና ግድያ ልብን የሚሰብር ነው። መቅደስ ቹቹ ይህን በማንሳት፣ ገዢው ፓርቲና መሪው አስቀድሞ ከገቡት ቃል አንጻር ተመዝነዋል ሲሉ ተከታዩን አጋርተዋል።
ከሦስት ወይም ከአራት ዓመት በፊት ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ከባድ ሁኔታ ውስጥ ትገባለች ብሎ ነብይ ነኝ ያለ የሀይማኖት ሰው ቢናገር እንኳ የሚታመን አይሆንም ነበር። ተስፋና እምነት የተጣለበት፣ ለየአንዳንዱ የዜጎች ሕይወት የሚያስብና የሚሳሳ፣ አክባሪና አገር ወዳድ መሪና ስርዓት መጣ ብሎ ያላመሰገነ የለም።
በጊዜው ገና ፍቅር እንደጀመሩ ጥንዶች፣ የተባለው ቃል ሁሉ ተፈጻሚ ይሆናል የሚል ጽኑ እምነት፣ ተፈቃሪ ነን ባለው ሕዝብ ላይ ጸንቶ ነበር። በአንጻም ‹ይሄ ፍቅር አላማረንም ያሉ ግን አልጠፉም። የሰማቸው የለም። እንደውም አፍቃሪ ነው የተባለለት መሪና ስርዓት ደንቀፍ ያለ እንደሆነም፣ ‹የለም! እገሌ ያስቀመጠው ደንጊያ አደናቀፈው፣ እነ እገሌ ያኖሩት መሰናክል ፈተነው› እየተባለ ስርዓቱን ተሳድቦ ለሰዳቢ ላለመስጠት የሚጠነቀቀው ብዙ ነበር።
በዛው ግን አልዘለቀም። ፍቅሩ እየቀነሰ፣ ጥርጣሬ እየነገሠ መጣ። አስቀድሞ ‹ተዉ! ይህ እፍ እፍ ያለ ፍቅር አያዋጣም!› ብለው የነበሩ ሰዎች ‹እኛ ብለን ነበር!› ማለት ጀመሩ። ልክ መጽሐፉ ‹ማኔ ቴቄል ፋሬስ› እንደሚል፣ በብዛዎች ልብ ስርዓቱም ሆነ መሪው ተመዘኑ። ሆነው የተገኙበትን መጠን ቤትና ልብ ይወቀው!
ሚዛን
ሰፍሮ ለክቶ፣ ይህን ያህል ብሎ እንደመሸጥ አይደለም፤ የሰው ሚዛን። የሰው ሚዛን እንዲሆን የምንጠብቀውና እንደሚሆን ያምመንነው ልክ ነው። ታማኝ ነው፣ አክባሪ ነው፣ መልካም ነው ያልነው ሰው፣ በየትኛውም ወቅት የምንመዝነው ከነዛ መመዘኛዎች አንጻር ነው፤ ከታማኝት፣ ከአክባሪነት እና ከመልካምነት።
የኢዴፌሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደሥልጣን ሲመጡ፣ እርሳቸውንም ሆነ ቀጥሎ የሚያመጡትን ለውጥና ስርዓት የምንመዝንበትንና የምንሰፍርበትን መለኪያ ሰጥተውን ነበር። በመጀመሪያ ቀን በፓርላማ ባደረጉት ንግግርም፣ መመዘኛቸውን (ጠብቆ የሚነበብ) ጠበቅ ጠቅጠቅ አድርገዉታል። ሕዝቡም ሳያንገራግር ያንን ንግግራቸውን እስከ ፍጻሜው የሚመዝንበት ልክ አድርጎ ያዘው።
በዛ መሠረት፣ በሚዛኑ ልክ ቆጥሮ፣ ተስፋና እምነቱንም በመሪው እና በስርዓቱ ንግግር ልክ መዝኖ፣ ሲጠራ አቤት ባይ ብዙ ነበር። ጎዳና ውጣ ሲባል ሆ ብሎ የሚወጣ፣ ዝመት ሲባል የሕይወቱ የማይሳሳ፣ አዋጣ ሲባል የማይሰስት…እንዲህ ያለ ሕዝብ ተገኘ።
በመሶብሽ እንጀራ አለ፣ የእህልሽ ጎተራ ሙሉ ነው ተብላ፣ ጓዳዋን ሳታይ አገልጋዮቿን አምና በጎተራው ልክና አለ በተባለው እንጀራ መጠን እንግዳ እንደምትጠራ ባልቴት ሆነ፣ ሕዝቡ። ‹የዓለም መንግሥተት መሪያችንንም ሆነ ስርዓቱን በክፉ ብታዩ በዐይናችን መጣችሁ!› ሲል ደረቱን ነፍቶ ክብርና ኩራቱን አሟጥጦ አሳየ። አገልጋዮቹን በቃላቸው አመነ፣ በቃላቸው መዝኖ አከበረ።
ግን ይህ ሚዛን እያደር እየሳሳ መጣ። ዐስር ሰው ሳይመጣና ሳይስተናገድ የሌማቱ እንጀራ አለቃ እንደማለት፣ ሌሎች ዐስር ሰዎች ገና ሳይመጡ የእህል ዱቄቱን ገብተው ሲያዩት እንደማጣት፤ የባልቴቷን ስሜት ማሰብ ነው። አገልጋዮቿን ከዛ ወዲህ እንዴት ልታምን ትችላለች?
ስለዚህ ሚዛን ይቀየራል። ሚዛን ሲቀየር መመዘኛው ትላንት ነው። ‹ኧረ እነ እገሌ በስንት ጠዓማቸው› ይባላል። ሚዛኑ ቀድመው በየሥራቸው የተመዘኑ ሰዎች ይሆናሉ፤ ሚዛኑ ወደፊት ተስፋ የተደረገው ሳይሆን ከዘህ በፊት በየመጠኑ ተመዝኖ የነበረው ይሆናል። ኪሳራ ብቻ!
አንዳንድ ሰዎች ያለውን ሁኔታ በበጎ ለመረዳት ጥረት ሲያደርጉ ይስተዋላል። ሚሚኑን ለማቻቻል በዚህ ወገን ነጥቦችን እየጨመሩ ይመለከታሉ።
አሁን እየሆነ የምናየው ቀድሞ የተዘራ የጥላቻና የክፋት ውጤት ነው፣ አሁን የመጣ ነገር ነው ማለት አንችልም፣ የቀደመው የዘራውን ነው አሁን እያጨድን የምንገኘው› የሚሉ ጥቂት አይደሉም።
መንግሥት አሁን ላይ ያለበት ጫና ብዙ ነው በማለትም፣ ዓለም ዐቀፉን ጫና ጨምሮ በሰሜኑ ክልል ያለውን ጦርነት በመጥቀስ ለማስረዳት የሚሞክሩ አሉ። ግን መንግሥት የዜጎችን ደኅንነት እንዳይጠብቅ ምን እልፍ ችግሮች ቢኖሩበት፣ ቢያንስ የዜጎቹን እልቂት ተመልክቶ ሐዘኑን የሚገልጽበት አንድ ደቂቃ እንዴት ያጣል? እንዴት የስድብ ቃልን የሚጠላ መሪ ያለው ስርዓት የሰዎች ሕይወት ያውም የንጹን ዜጎ ሞት ጉዳይ የክብሩን ሩብ ያህል እንኳ አያስጨንቀውም? ብለን የምንጠይቅም ጥቂት አይደለንም።
ሕዝብ ይመዝናል። ምክንያቱም መዝለቁን የሚወስነው የሚያስተዳድረው ስርዓት ነው። ደኅንነቱን መጠበቅ ያለበትም ያው ስርዓት ነውና፣ አትመዝን አይባልም። ያከበረውን እንዲያከብርና ለትውልድ የሆነውን እንዲናገር፣ ያጠፋውም ሥራው እንዲታወቅና ትውልድ እንዲማርበት ሲባል፤ ሕዝብ ስለዛሬም ስለነገም መሪውንና ስርዓቱን ይመዝናል።
እንዳልኩት ነው! መመዘኛውን አንድም ከራሱ ከስርዓቱና ከመሪው ያገኛል፣ አንድም አስቀድሞ ለመመዘን ከወጣውና ከተመዘነው ይሆናል። በሚዛኑ መቅለል ደግሞ ኹለት ነገር ነው። አንደኛ የወል በሆነ ሚዛን ተመዝኖ ቀልሎ መገኘት ነው። ሌላው ደግሞ ከተጠበቀና ተስፋ ከተደረገ መጠን አንሶ መገኘት።
አለመታመን
ገዢው ፓርቲ እንመዝንበት ዘንድ፣ ‹ቆንጥጡን› እስኪል ድረስ አለኝ ያለው መታመን አሁን ላይ የለም። ከታመነም የታመነው አገሪቱን ገነት ለማድረግ ሳይሆን በአረንጓዴ አትክልት በማሳመር ገነት ለማስመሰል ሥራው ብቻ ነው። ከዛ ውጪ ኢትዮጵያ የተገባላት ቃል አንዱም እውን አልሆነም።
ምንአልባት እንዲህ ለማለትና መሪውንም ሆነ ስርዓቱን ሚዛኑ ላይ ለማስቀመጥ ምነው አራት ዓመት ብቻ የሚል ሊኖር ይችላል። ‹የቀደመው ሠላሳ ዓመታትን ተሰጥቶት የለምን?› ዓይነት ሙግት። ግን ያኔ በሠላሳ ዓመት የተደረሰበትን አሁን በአራት ዓመት ውስጥ ብቻ አንድ ብሎ ጀምሮ መዝለቅ እንዴት አያስመዝን?
በነገራችን ላይ መታመን ማለት የገቡትን ቃል ሁሉ መፈጸም ላይሆን ይችላል። ለልጆቹ ሁሉን እንደሚያሟላ ቃል የገባ አባት፣ ቃሉን ለማክበር የሚችለውን ሁሉ ማድረግ መቻሉ ከመታመን ይቆጠራል። በተለያየ ምክንያት ቃሉን መጠበቅ ባይችል እንኳ ሁኔታውን በግለጽና በእውነት ለልጆቹ ቢያስረዳ፣ ቃሉን ለመፈጸም ጊዜ እንደሚያስፈልገው በማመን ልጆቹ አባታቸውን ሊያግዙት ሁሉ ይችላሉ። እንጂ! ‹ያኔ ነበር ቃል የገባሁት! አበቃ አሁን አለፈ፤ አሻራችኋለሁ ያልኩት እዚህ ድረስ ነው በቃ!› ካለ፤ ችግሩ እዚህ ጋር ነው።
ይህ ማለት ያሉ ፈተናዎችንና ሁኔታዎችን መረዳት ይቻላል ነው። ጠላት አጥታ የማታውቀው ኢትዮጵያ ጦር የሚወረወርባት በተለያየ አንጻር ነው። መሪዎችና ስርዓትም በዚህ የተነሳ ከባድ ፈተና ሊገጥማቸው እንደሚችል እሙን ነው። ግን መታመን ማለት የገቡትን ቃል ሁሉ መፈጸም ብቻ ሳይሆን ለመፈጸም ወደኋላ አለማለትና መታገል ነው። ይህን ትግል ካላየን፣ እንግዲያው መታመን የለም ማለት አይደለ?
አለማክበር
አሁን ያለው መንግሥትን የሚመራው ስርዓት ሕዝብን አላከበረም። ከሰዎች ሕይወት ይልቅ የተጋባው እልህ የበለጠበት ይመስላል። ‹እናንተ ሰው በመግደል ብትጠመዱም እኔ በበኩሌ ሥራ ላይ ነኝ› እያለ፣ የሰው ሕይወት በሚጠፋበት እለትም ችግኝ ሲተክል እየታየ ነው። ሰው የሚያውቀው የሚያየውን ነው፤ መንግሥት የሚያሳየውም ሕዝብ እንዲያይ የሚፈልገውን ነው። በዛም መሠረት አሁን በየትዕይንተ መስኮቶቻችን ውስጥ መንግሥት የሚታየው አረንጓዴ አሻራውን እያኖረ ነው።
የሕዝብን ደም እና እንባ በዚህ መጠን ቸል ማለት አገርን፣ ሕዝብን እንዲሁም ራሱን የሰው ልጅን አለማክበር ነው። አገርን ማሻገርና ማበልጸግ የሚቻለው ሕዝቧን በሞት ቀንሶ በሬሳ ላይ ተረማምዶ ወይም የለውጡ አካል ነው እየተባለ በሚፈስስ ደም መንገድና ጎዳናን እያጠቡ አይደለም።
ዛሬ ላይ ያደጉ የሚባሉ አገራት አንድ ለመሆን ጦርነት ገጥመው ያውቃሉ፤ ብዙ የሕይወት መስዋዕትነትን ከፍለዋል። ግን አሁን ኢትዮጵያ እየከፈለችው እንዳለችው ዓይነት አይደለም። ገዢው ፓርቲና መሪው ምንአልባት ይህ መስዋዕትነት አገርን የሚያሻር አድርገው ይቆሩት እንደሆነ፤ አይደለም። ይህ በሁሉም እጅ ላይ ያለ ደም፣ በታሪክ አንገት የሚያስደፋ አሳዛኝ ዘመን፣ ስርዓትን የሚያሳልፍ እንጂ ኢትዮጵያን የሚያሻግር አይደለም። ሰማዕታቱንና በግፍ እየተገደሉ ያሉ ንጹሐንን ግን ኢትዮጵያ መቼም አትረሳቸውም።
‹መግደል መሸነፍ ነው› የሚለው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ንግግር፣ አሁን ያኔ የነበረውን ትህትና እንኳ ያስቀረ አይመስልም። ‹የኢትዮጵያ እናቶች ይጸልዩልኛል፣ ሕጻናት የአገር ተስፋ ናቸው› ያለ አንደበት፣ ‹የሕዝቤን ሕይወት የምታጠፋ፣ የሕጻናትና እናቶችን ሕይወት የምታጎሳቁሉ ሁሉ ትቀፈደዳላችሁ!› ከማለት ይልቅ ክብሬን ከተጠጋችሁ ወየው ማለት ቀንቶታል። ይህ አለመታመን፣ ይህ ቃልንም ሆነ ሰውን አለማክበር ነው።
እንግዲህ የምናየው እንደዛ ነውና ምንም ማድረግ አይቻልም። ኢትዮጵያ እንደወትሮዋ ቀና ብላ ወደፈጣሪዋ መጮኽ፣ ለጸሎት ተነሱ ማለት፣ ማልቀስና እንባዬን ተመልከት ማለት አሁንም እጣዋ ሆኗል። የተሻለው ቀን መጣ ሲባል ነበር፣ ግን የተሻለው ቀን አሁንም ገና ነው። ምንአልባት ጎዳናዎቿ ተውበው፣ በአረንጓዴ ሜዳ አሸብርቃ፣ በቀይ የደም ምንጣፍ ለተሻለው ቀን አቀባበል ለማድረግ እየተጠባበቀች ይሆናል። ማን ያውቅ ነበር! አሁንስ ማን ያውቃል!
በግፍ ለተገደሉ ንጹሐን ወገኖቻችን የንጹሐን አምላክ ይሁናቸው፣ ለነፍሳቸው ምህረትን ላዘኑ መጽናናትን ያድልልን። ለመንግሥት ልብና ማስተዋሉን ሰጥቶ፣ ድረስልን ሲባል ባይደርስ እንኳ ለሕሊና ጸሎት አንድ ደቂቃ የሚሰጥበትን ማስተዋል ይስጥልን። ከዚህም የከፋው እንዳይወጣ ይሰውረና፣ የትንሣኤውን ቀን ያቅርብልን!
ይህ ግን እውነት ሆኗል። አሁን ኢትዮጵያን እያስተዳደረ ያለ ስርዓትም ሆነ መሪው፣ እንመዝናቸው ዘንድ ቃላቸውን ሰጥተውን ነበር። እነሆም በዛ ቃል መሠረት ተመዘኑ፣ ቀለሉ እንጂ በቃሉ ልክ አልተገኙም።
ቅጽ 4 ቁጥር 190 ሰኔ 18 2014



