በሐሰተኛ መታወቂያ የሚሰጡ የንግድ ፈቃዶች ትልቅ ፈተና ሆነዋል ተባለ

0
1879

በመዲናዋ ሐሰተኛ መታወቂያ ተጠቅመው በሚወጡ ንግድ ፈቃዶች አማካኝነት ጥቅም ላይ የሚውሉ የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያዎች መበራከታቸውና በዚህም በሐሰተኛ ደረሰኝ የሚፈጸሙ ግብይቶች መጨመራቸው ትልቅ ፈተና እየሆነ መምጣቱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የገቢዎች ቢሮ ለአዲስ ማለዳ ገለጸ።

እንደ ቢሮው ገለጻ፣ በአሁኑ ወቅት በተደረገ የማጣራት ሥራ በአራት ሰዎች ሐሰተኛ የግዥ መመዝገቢያ መሣሪያዎች ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ ያልተጣራ ገንዘብ መገኘቱን እና ገና ያልተደረሰባቸው በጣም በርካታ ማሽኖች መኖራቸው ታውቋል።

ከ600 ሚሊዮን ብሩ ውስጥ የተወሰነው መጠን ተወራርዶ የተዘረፈ ሲሆን፣ ጉዳዩ በፖሊስ ተይዞ ቀሪው የገንዘብ መጠን የተወራረደ መሆን አለመሆኑ ገና እየተጣራ እንደሆነም ነው የተነገረው።

በሐሰተኛ መታወቂያ በሚወጣ ሐሰተኛ ንግድ ፈቃድ በሚገዙ የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያዎች፣ ሐሰተኛ ደረሰኞችን በማተም ከመንግሥት ካዘና ገንዘብ እየተዘረፈ ይገኛል። ይህም እየተስፋፋ የሚገኝ ተግባር በተካኑ ሌቦች እንደሚፈጸምና ከባድ ፈተና እየሆነ ስለመምጣቱም ተመላክቷል።

በአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ የታክስ መረጃና የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ገዛኸኝ ልደቱ፣ በሐሰተኛ ንግድ ፈቃድ የተገዙ የሽያጭ መሣሪያዎች ግብይት ሲከናወን የሚሰጡት ደረሰኝ ብቻ ነው። የተሸጠ ዕቃ ወይም የተሰጠ አገልግሎት ግን አይኖርም ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ማሽኖች ትክክለኛ ቢሆኑም አድራሻ ግን የላቸውም። የተፈጸመውን የግብይት መረጃም ለሚመለከተው ሕጋዊ የመንግሥት አካል ሪፖርት አያደርጉም ነው ያሉት።

ግዥ ከተከናወነ በኋላም የንግድ ፈቃድ አድራሻቸውን ይዘን ስንሄድ አናገኛቸውም ሲሉ ገልጸዋል። በምሳሌም ሲያስረዱ፣ ‹‹ለአንድ ግለሰብ አገልግለት ለሰጡበት 20 ብር ያስከፍሉና የ100 ብር ደረሰኝ ይቆርጡለታል። ግለሰቡም የ100 ብር ዕቃ ገዝቻለሁ ወይም አገልግሎት አግኝቻለሁ ብሎ ከመንግሥትም ሆነ ከግለሰብ ተቋማት ያወራርዳል። ይሁን እንጂ ሰውየው የ100 ብር ዕቃ አልገዛም። ይልቅስ 80 ብር አትርፏል ማለት ነው። ይህ ዘዴ በሚሊዮን በሚቆጠር የገንዘብ መጠን ሲፈጸም ከመንግሥት ካዘና የሚደርሰው ዝርፊያ የከፋ ነው።›› ብለዋል።

ሐሰተኛ ማሽኖች በመላ አገሪቱ በስፋት መኖራቸውን ጠቅሰውም፣ ይህን ወንጀል ለመቀነስና ለመከላከል በአዲስ አበባና በክልል ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እንዲሁም ከሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

በተያዙ ሐሰተኛ ማሽኖት ተወራርደው የተዘረፉ ገንዘቦችን፣ ወንጀል የሠሩትን አካላት ተጠያቂ በማድረግ እንዲመለሱ አድርገናል። አድራሻ የሌላቸው ማሽኖችንም እየለየን ከአገልግሎት ውጭ እያደረግን ነውም ሲሉ ተደምጠዋል።

በሌላም በኩል፣ በግብይት ወቅት ደረሰኝ እያላቸው የማይሰጡ ነጋዴዎች መኖራቸውን ጠቁመው፤ ሆኖም ግን ከቀደሙ ዓመታት ጋር ሲነጻጸር ይህ ወንጀል እየቀነሰ ነው ብለዋል።

በዚህም በተለይ ደግሞ ደረሰኝ እጅ በእጅ በሚጠቀሙት ላይ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን ያነሱት ዳይሬክተሩ፣ የቁጥጥር ሥራችን ውጤታማ መሆኑን የሚያሳየን የምናገኘው የተጨማሪ እሴት ግብር (ቫት) መጨመሩ ነው ሲሉ ተናግረዋል። መርካቶ ላይ ብዙ ጊዜ ደረሰኝ አይቆረጥም ስለሚባልም ‹‹block management›› የሚባል አሰራር ተዘርግቶ የሠራተኛ ቁጥር በመጨመር እየተሠራ መሆኑን ነው የጠቆሙት።

በማሽን አቅርቦት ችግር ማሽን መግዛት የሚጠበቅባቸውን ግብር ከፋዮች አዲስ ሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ ከማስገዛት አንጻር 2 ሺሕ 25 ግብር ከፋዮችን ለማስገዛት ታቅዶ 634 ብቻ ማስገዛት መቻሉን፣ የገቢዎች ሚኒስቴር የ2014 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ያሳያል።


ቅጽ 4 ቁጥር 190 ሰኔ 18 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here