መነሻ ገጽርዕስ አንቀፅታሪካችሁ ተፍቆ በሌላ መተካት እንዳለም እወቁ!

ታሪካችሁ ተፍቆ በሌላ መተካት እንዳለም እወቁ!

ኢትዮጵያ አገራችን በቅርብ ጊዜ ታሪኳ ዐይታው የማታውቅ ዘግናኝ ግፎችን በገዛ ዜጎቿ እያስተናገደች ትገኛለች። የውጭ ጠላት ሳይመጣባት አንዱ አቅም በሌለው በአንዱ ላይ ተነስቶ ከምድረ ገጽ ዘሩን ለማጥፋት በማሰብ ጨቅላዎችን ሳይቀር አረመኔያዊነት በተሞላበት ጭካኔ እየጨፈጨፈ ይገኛል። ይህ ዓይነት አብሮ የማያኗኑር ተግባርን ማስቆም ያልቻለ፣ አልያም ሥልጣን አለኝ ብሎ በእጅ አዙርም ሆነ በቀጥታ ያስፈፀመ መጠየቅ ብቻ ሳይሆን ከነአስተሳሰቡ መጥፋት እንዳለበት የአዲስ ማለዳ እምነት ነው።

መንግሥት አለ ብሎ አርሶ ማኅበረሰቡንም ሆነ ሰፊውን ኅብረተሰብ እመግባለሁ ብሎ ደፋ ቀና የሚለውን ደሃውን ማኅበረሰብ፣ አቅም የለውም ብሎ ማጥቃት የአረመኔዎች ተልካሻ የፈሪ ተግባር እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል። በዚህ ዘመን ይቅርና በቀደሙ ዘመናት የተደረጉ ወረራዎችም ሆኑ የጅምላ ጭፍጨፋዎችና ማፈናቀሎች አሁንም ድረስ እንዳልተረሱ ልብ ሊባልም ያስፈልጋል።

መሻሻል ያልቻሉ የደኅንነት ስጋቶች አሁን አሁን ወደለየለት የዘር ማጥፋት ወንጀሎች መቀየራቸውን መንግሥት አምኖ ኃላፊነቱን ሊቀበል ግድ ይላል። ንጹሐንን አማራ ናቸው በሚል በየጊዜው የሚጨፈጭፉ ታጣቂዎች ባሉበት አገር፣ ከመንግሥት መዋቅር ውጭ ሆነው ስጋት አሳድረዋል በሚል ሕዝብን ከጥፋት የታደጉ ባለውለታዎች ላይ መዝመት ከጅምላ አጥፊዎች እንደማያስለይም ይታወቅ።

መንግሥት ነኝ ብሎ የሚያምነው ግን፣ ይህን ያህል ግፍ በዘመኑ ሲፈፀም ያየው አካል ለሚፈፀመው በደል ሁሉ ወክዬዋለሁ ብሎ የተቀመጠውን የማኅበረሰብ አካል ጭምር ተጠያቂ እንደሚያደርግ ሊያውቀው ያስፈልጋል። በሕዝብ ሥም “ነፃ እናወጣለን” አልያም “ለውጥ እናመጣለን” በሚል ፉክክር ድሃውንና ምንም ያላደረገውን ማኅበረሰብ ጨፍጭፎ ከምድረ ገፅ ማጥፋት መሞከር ለማንም እንደማይጠቅምም አጥፊዎች ሊረዱት ይገባል።

ሕዝብን የጦስ ዶሮ በማድረግ እኩይ ዓላማን ለማሳካት፣ እንዲሁም የወረራና የመስፋፋት እቅድን ለማከናወን የሚያስብ የትኛውም የመንግሥትም ሆነ የአሸባሪ ቡድን አባል ይብዛም ይነስ ረፍዶም ቢሆን የእጁን ማግኘቱ አይቀርም። በኦሮሞ ሥም የሚደረጉ ማናቸውም የዘር ማጥፋት ወንጀሎች መላውን የብሔሩን ተወላጅ በቀጥታ ባያስጠይቅም፣ ኹሉንም አንገት የሚያስደፋ እንደመሆኑ ተግባሩ ለማንም ቢሆን የማያዛልቅ መሆኑን አዲስ ማለዳ ማስገንዘብ ትፈልጋለች።

በኢትዮጵያ ታሪክ ግፍን በዜጎቻቸው ላይ የሠሩ በርካታ ግለሰቦችም ይሁኑ የማኅበረሰብ አካሎች እንዳሉ ይታወቃል። በታሪክ ግን እንድንማርባቸው ሲባል የሠሩት ክፉ ሥራ እንጂ ማንነታቸው ሲጠቀስ አንሰማም። ጥሩ የሠሩትን ከነሥማቸው ከማንቆለጳጰሳችን ውጭ ግፍን መታወቂያቸው ያደረጉ ከታሪክ ማሕደር ማንነታቸው ይፋቃል። ለምሳሌ፣ አንድ በወንድሙ ላይ ተነስቶ ሥልጣን ነጥቆ ሕዝብንም ሲበድል የቆየ ንጉሥ ታሪኩ እንዳይነገር ሥሙም እንዳይጠቀስ ስለተደረገ፣ እኛም እንደማንነግራችሁ የሥልጣን ዘመኑ ተከፍሎ ላስወገደው ወንድሙና እሱን አስወግዶ ለተካው ንጉሥ ተሰጥቷል።

እሱ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም በቅርብ የምናውቃቸው ክፉ የሠሩ ነገሥታት ጭምር የሠሩት በጎ ተግባር ካለ እነሱ ለነጠቁት ወይም ላስወገዳቸው አካል ተላልፎ ሥማቸው ከታሪክ ማሕደር የሚፋቅበት አሰራር ዛሬም ቢሆን ተግባራዊ የማይደረግበት ምክንያት የለም። ታሪክ የአሸናፊዎች ነው ቢባልም፣ ተበዳይ እንጂ በዳይ ስለሚረሳው የሆነው መጻፉ እንደማይቀር ልትጠራጠሩ አይገባም።

“አረንጓዴ አሻራ” እየተባለ ለትውልድ የሚተላለፍ ሥም ለመትከል የሚሯሯጡ የዘመናችን ገዢዎች ከቀደመው ታሪካችን ተምረው፣ በተቃውሞ ወቅት በችግኛቸው የተጀመረው የመንቀል ዘመቻ በሥማቸውና በራሳቸው እንደሚቀጥል ሊረዱት ግድ ይላል። “የራበው ሕዝብ መሪውን ይበላል” እየተባለ ከሚነገረው የዘመናችን አባባል ይልቅ፣ “ጅብ ከሚበላህ በልተኸው ተቀደስ” የሚለው አባባል ግፍን ለተላመደ ትውልድ ስለሚሆን ለራሱ ሲል መንግሥት ሊያስብበት ይገባል።

ጭፍጨፋውን የፈፀመው ቡድን የሠራውን ያውቃልና እኔ ሠራሁ ስለማይል፣ ደኅንነታችንን እንዲያስጠብቅልን የምንገብርለት መንግሽት ሁኔታውን ለማድበስበስና ተረስቶ እንዲቀር በተለመደው መሸፋፈኛ መንገዱ የሚቀጥልበት ከሆነ፣ ቀጥታ ቃታ ስበውና ካራ መዘው ከሚገድሉት በላይ እንደሚያስጠይቀው አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።

በቅርቡ በደርግ ዘመን ተፈፀመ ለሚባለው የትኛውም ወንጀል ወታደሩ ሳይሆን አዛዦች እንደተጠየቁ ዓለም ዐቀፍ ሕግን ባንረዳ እንኳን፣ ከቅርቡ ታሪካችን መገንዘብ ይኖርብናል። የሕዝብ ልብ ቆስሎ፣ በወገኑ ጭፍጨፋ አንጀቱ አርሮ ሲብሰለሰል የተመለከተ መንግሥት ለመካስ ባይቻለው እንኳን፣ አንጀቱን የሚያርስለት እርምጃ ለዓመታት መውሰድ አለመቻሉ አሳዛኝ ነው።

ሕዝብን ከጥቃት ሊታደግ ይገባው የነበረ መንግሥት አቅም ሳይሆን ብቃቱ ቢያንሰው እንኳን እንዴት እንደሕዝቡ አዘኔታ አይሰማውም! ባንዲራ ዝቅ አድርጎ መዋል ማንንም የማይጎዳ እንደመሆኑ ሊያውጅ በተገባውም ነበር። እንኳን ሊያስተዛዝን የሕሊና ፀሎት እንዳይደረግ የከለከለ መንግሥት፣ “አብዮታዊ እርምጃ ለተወሰደበት እንዳታለቅሱ” ብሎ ከለከለ ከሚባለው ደርግ የሚለየው አንዳችም ነገር እንደማይኖር ሊታወቅ ይገባል።

ጎረቤቱ ሲሞት ሬዲዮ እንኳን ለመክፈት የማይፈቅድ ማኅበረሰብን እገዛለሁ የሚል መንግሥት፣ የአንድ ቀበሌ ነዋሪ ፍሊት እንደተረጨባቸው ነፍሳት ሲረፈረፉ እያየ ሐዘን ለመቀመጥ አለመፈለጉ ከገዳዮቹ ሊያስለየው አይችልም። ማስተዛዘንና ቦታው ሄዶ መጎብኘት እንኳን ባይችል፣ ሕዝብ ለቅሶ ተቀምጦ አንድ መሪ ነኝ የሚል ሰው ከነሹማምንቱ ሲምነሸነሽ እንዴት እዩኝ ብሎ የሚያሳፍር ተግባሩን በምስል ይለቃል።

ከዚህ ቀደም በነበሩ ተመሳሳይ ጭፍጨፋዎች ማሳ በመጎብኘቱ ሲወቀስ የነበረ አካል ላይ የቀረበ መደበኛ ክስም ሆነ ትችት ባለመኖሩ የልብ ልብ ተሰምቶት አሁንም ደግሞታል። ድንገተኛ ጉዳይ ሲመጣ የተያዘ እቅድ ታጥፎ እንደሚተካ ቢታወቅም፣ ይህን ለማድረግ አለመሞከሩ ለጉዳዩ መንግሥት የሰጠውን አናሳ ትኩረት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ እንደሆነ አዲስ ማለዳ ትረዳለች።


ቅጽ 4 ቁጥር 190 ሰኔ 18 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች