ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረግ ፍልሰትና ፈተናዎቹ

0
2048

ፍልሰት ከጥንት ዘመን ጀምሮ የኖረ የሰው ልጆች ማኅበራዊ ክስተት ስለመሆኑ ይነገራል። ይህም በጊዜያዊነት ወይም በቋሚነት የሰዎች የመኖሪያ ቦታ ለውጥ ወይም ከቦታ ቦታ የሚደረግ እንቅስቃሴ እንደሆነ ነው የሚታሰበው።

የሰዎች ፍልሰት ውስጣዊና ውጫዊ ተብሎ ሊከፈል የሚችል ሲሆን፣ የውስጥ ፍልሰት ዜጎች በአገራቸው ውስጥ ከአንድ ከተማ ወደ ሌላ ከተማ፣ ከገጠር ወደ ሌላ ገጠር፣ ከከተማ ወደ ገጠር እንዲሁም ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረጉ ፍልሰቶችን የሚያጠቃልል ስለመሆኑ ይገለጻል።

ሆኖም ኢትዮጵያ ውስጥ ስለሚደረግ የሰዎች የውስጥ ፍልሰት ሲታይ፣ ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረጉ ፍልሰቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ ስለመምጣታቸው ብዙ አመላካች ጉዳዮች አሉ።

በዚህ ጉዳይ ላይ ስሜ ይቆይ ያሉ ኹለት ባለታሪኮች የሚከተለውን አጋርተውናል። የመጀመሪያዋ ባለታሪካችን የሆኑት ሴት በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ቁጭ ብለው ከሚለምኑ ሰዎች አንዷ ናቸው። አንድ ልጃቸውን ታቅፈው ሌላኛውን አጠገባቸው አስቀምጠዋል። ጊዜው ምሽት በመሆኑ የመኪኖች መብራት ኹለት ሕጻናት ልጆቻቸው ዐይን ላይ ይበራል። በዚህም መንገደኞች የፈቀዱትን ያህል ሳንቲም ከሰጡ በኋላ፣ ‹ምናለበት የልጆቹን ዐይን በዚህ ዕድሜያቸው በሽተኛ ባታደርጊ፣ ከመንገዱ ራቅ ብለሽ ቁጭ ብትይ!› የሚል ቁጣ አዘል ምክራቸውን ለግሰው ያልፋሉ።

ባለታሪኳ እናት አራት ዓመት በፊት ነበር ከገጠር ምንም ወደማያውቁት ከተማ የመጡት። ከመጡም በኋላ በቤት ሠራተኝነትና ከዚያም በመስተንግዶ ከሠሩ በኋላ፣ ሳይታሰብ አንድ ልጅ የወለዱት። ‹‹ምን እንደነካኝ አላውቅም፣ ኹለተኛ ልጅም ወለድኩኝ›› የሚሉት እኚህ እናት፣ ‹‹ከዚያ በኋላ ልጆቼን ለመመገብ ብቸኛው አማራጨ መለመን ነበር›› ሲሉ ይናገራሉ።

እዚያው ገጠር ቢኖሩ ኖሮ ከዚህ የተሻለ ሕይወት ሊኖርዎ አይችልም ነበር ወይ ተብለው ሲጠየቁም፣ ‹‹ለዚህ አስከፊ ሕይወት የዳረገኝ ወደ ከተማ መምጣቴ ነው። የመጣሁትም የጎደለብኝ ነገር ኖሮ አልነበረም፣ ተምሬ ሥራ እንደማገኝ ሰዎች ሲነግሩኝ ትምህርቴን አቋርጨ ነው የመጣሁት። እዚያው ብቀር ኖሮ ትምህርቴን እጨርስ ነበር። ትንሽም ብትሆን ሥራ አላጣም፣ ትዳርም ይኖረኝ ነበር። ከእንግዲህ ግን ያን ማድረግ አልችልም፣ ከእኔ የባሰ የሕይወት ዕጣ ፈንታ ያላቸው ልጆችን ወደዚህች ዓለም አምጥቻለሁ።›› ሲሉ ይገልጻሉ።

የልጃቸው አባት ማን እንደሆነና የት እንዳለ ለመናገር ፈቃደኛ አይደሉም እንጂ፣ አንዳች እገዛ እንደማያደርግላቸው ወደፊትም በእሱ ምንም ተስፋ እንደሌላቸው ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ ጠቀስ አድርገዋል።

አሁን ላይ በኢትዮጵያ፣ ከዓመት በላይ ያስቆጠረው ጦርነትና በመላ የአገሪቱ ክፍል በሚባል ሁኔታ ያሉ ግጭቶች፣ የፍልሰት ዋነኛ ገፊ ምክንያቶች እንደሆኑ ይነገራል።

አንድ እድሜያቸው በ50ዎቹ መካከል የሚገመት አባወራ ወደ አዲስ አበባ ከመጡ ከሦስት ወር በላይ አልሆነኝም ይላሉ። ከዚህ በፊት አዲስ አበባን ለሕክምና በመጣኹ ጊዜ ለኹለት ቀን እንጂ አላውቃትም የሚሉት አባወራው፣ ሆኖም ችግርና መጎሳቆል ሲመጣ፣ በቀዬ የመኖር ተስፋ ሲጨልም እንዲህ ፈጽሞ ወደማያውቁት ከተማ ያስመጣል ባይ ናቸው። አሁንም የመጡት በግጭት ምክንያት ንብረታቸው በመውደሙ በተለይም የሚያርሱባቸውን በሬዎቻቸው በታጣቂዎች ስለታረዱባቸው ጎዳና ላይ ለምነው የበሬ መግዣ ይዞ ለመመለስ ነው።

እናም 10 ሺሕ ብር ካገኘሁ እመለሳለሁ የሚል ዕቅድ ይዘው ቢመጡም፣ ካሰቡት አንጻር በአጭር ጊዜ ውስጥ 60 ሺሕ ብር አገኘሁ ይላሉ። ‹‹ከዚህ በኋላም ወደ ገጠር የመመለስ ዕቅዴን አንስቻለሁ የምመለስ ቢሆን እንኳን መቼ እንደሆነ አላውቀውም። አዲስ አበቤም ልጅ ያውጣ! የተባረከ ሕዝብ ነው›› በማለት ተናግረዋል።

በወፍ በረር እንደሚሰሙትና እርሳቸውም እንደሚገምቱት ከሆነ በርካታ የሰፈራቸው ወጣቶችና ጎልማሶች ወደተለያዩ ከተሞች ፈልሰዋል። ይህም ያሳዝነኛል፣ አንድም ቀን እንዲህ ዓይነት ሕይወት ይገጥመናል ብን አስበን አናውቅም ነበር ይላሉ።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገሪቱ እየተባባሰ በመጣው የሰላም እጦት ከተፈናቀሉ በርካታ የማኅበረሰብ ክፍሎች አብዛኞቹ ወደ ከተማ እንደፈለሱ ነው የሚነገረው። ለአብነትም በደብረ ብርሃን ከተማ ከሚገኙ ከ21 ሺሕ በላይ ተፈናቃዮች ወስጥ በርካታ የሚባሉ ሰዎች ወደ ቀያቸው የመመለስ ፍላጎት ፈጽሞ እንደሌላቸው መገለጹ ይታወሳል። ከእነዚህ ውስጥ ሥራ የፈጠሩ፣ ተቀጥረው የሚሠሩ እንዲሁም ለልመናና ዝሙት አዳሪነት የተጋለጡ ስለመኖራቸው ይጠቀሳል።

በተለይ ግን በየከተሞች መሥራት የሚችሉ ወጣቶችና ጎልማሶች ልመና ተበራክቷል ሲሉ የሚገልጹ ብዙዎች ናቸው። ሰዎች በቋሚነት ከሚኖሩበት ገጠር ወይም ትንሽ ከተማ ወደ ትላልቅ ከተሞች ሲፈልሱ የሚታዩት የተሻለ ሕይወት በመፈለግ ሲሆን፣ ብዙዎች በቋሚነት ሳይመለሱ እንደወጡ ሊቀሩ ይችላሉ ነው የሚባለው። የተወሰኑት ደግሞ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ወደ ቀደመ ቀያቸው የሚመለሱበት ሁኔታ ይኖራል።

ሰዎች አንዳንዴ ከመኖሪያቸው ያለፈቃዳቸው የሚፈልሱ ሲሆን፣ ይህም በተፈጥሮ አደጋዎች፣ በጦርነትና ግጭቶች ይሁን እንጂ፣ በጥቅሉ በአንድ አካባቢ ያለው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ለሰዎች ፍልሰት እንደ ዋና ምክንያት የሚቆጠር ስለመሆኑ ነው የሚገለጸው።

ወጣቶችና ሕጻናትን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ በተለይም ከገጠር ወደ ከተማ እንዲፈልሱ ከሚያደርጓቸው ምክንያቶች ውስጥ የቤተሰብ ገቢ ማነስ፣ ወላጅን በሞት ማጣት፣ የትዳር መፍረስ፣ እንደ ጠለፋ፣ ያለዕድሜ ጋብቻና የሴት ልጅ ግርዛት ያሉ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች እንዲሁም የተሳሳተ የከተማ ሕይወት መረጃ ተጠቅሰው ይገኛሉ።

ከዚህም ባለፈ ደግሞ ፍልሰት ውስብስብ ክስተት ከመሆኑ የተነሳ መነሻ ምክንያቶቹን በግልጽ ለማስቀመጥ አስቸጋሪ እንደሆነ የሚገልጹ በርካቶች ናቸው።

ፍልሰት በዓለም ላይ የተለመደ ክስተት ቢሆንም፣ ባላደጉ አገራት ግን ከኹሉም ይበልጥ ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረገው ፍልሰት መጠኑም ይሁን ፍጥነቱ የበዛ እንደሆነ ጥናቶች ይጠቁማሉ።

በቅርቡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶች፣ ሕጻናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ በአዲስ አበባ በጎዳና ከሚኖሩ ልጆች 93 በመቶ የሚሆኑት ከክልል ከተሞች እንደሚመጡ በጥናት ማረጋገጡን አስታውቆ ነበር። ይህም በአዲስ አበባ ከተማ በጎዳና ላይ ከሚኖሩ ልጆች የአዲስ አበባ ተወላጅ የሆኑት ሰባት በመቶ ብቻ ናቸው ነው ያለው።

በተጓዳኝ ሕጻናቱ ወደ ከተማ ከመጡ በኋላ የሚገጥማቸው ሕይወት አስቸጋሪ እንደሆነ በተደጋጋሚ ይነገራል። ለወሲብ ጥቃት፣ ለጉልበት ብዝበዛ እንዲሁም ለጎዳናና ለሱስ ሕይወት ሊጋለጡ እንደሚችሉም የሚነገር ጉዳይ ነው። ቢሮው እንደገለጸውም፣ ለሕጻናቱ የሰዎች የክብደት መለኪያ ሚዛን ሰጥቶ ለራሱ ትርፍ ለማግኘት የሚያሠራ አካል አለ።

በአንድ ወቅት ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ጎዳና ላይ ሚዛን የሚሠሩ ታዳጊዎችን ማንሳት ተጀምሮ የነበረ ቢሆንም፣ ለልጆች ሚዛን በመስጠት የሚያሠሩ ግለሰቦች በመኖራቸው ተይዘው ክስ ተጀምሮ ሊመሰክር የሚችል አካል ባለመገኘቱ ግለሰቦች መለቀቃቸውንና በዚህ የተነሳ ልጆችን ከጎዳና የማንሳቱ ሥራ እንደተቋረጠ ነው ቢሮው ያመላከተው።

ምን ማድረግ ይቻላል?
በርካቶች በተሳሳተ መረጃ ከተማ ከገቡ ጥሩ ነገር እንደሚያጋጥማቸው ተነግሯቸው የሚፈልሱ ሲሆን፣ ሌሎች ደግሞ በሥራ አጥነት፣ በመፈናቀል፣ በቤተሰብ አልባነት ሊመጡ እንደሚችሉ ይገመታል። ሆኖም ብዙዎች ባሉበት ቦታ የተሻለ ኑሮ መኖር እየቻሉ ከተማ ገብተው ለወንጀል፣ ለጉልበት ብዝበዛ ወይም ለጎዳና ሕይወት የሚጋለጡ ናቸው።

ለአብነትም (በጥናት የተረጋገጠ ባይሆንም) በከተሞች ያሉ ዝሙት አዳሪዎች በአብዛኛው ከገጠር የሚመጡ ሴቶችና ልጃገረዶች ስለመሆናቸው ሲነገር ይሰማል። እንዲሁም በዋና ዋና ከተሞች ጎዳና ላይ ሲለምኑ የሚታዩ ሰዎች፣ እንዲሁም የጎዳና ተዳዳሪ ሕጻናትም በብዛት ከገጠር የፈለሱ ስለመሆናቸው ነው የሚነሳው።

ይህን ለመከላከልም ማድረግ የሚቻለው ዜጎች በቀያቸው ሠርተው መኖር እንዲችሉ ሰላም መፍጠር፣ ለወጣቶች የሥራ እድል ማመቻቸት፣ እንዲሁም ከፍልሰት ጋር ስለሚመጡ ቀውሶች ግንዛቤ መፍጠር እንደሚገባ ይመከራል።

ፈልሰው የሚመጡ ሕጻናትንም በተቋም በማቆየት እና የሥነ ልቦና ድጋፍ በማድረግ ቤተሰቦቻቸውን አፈላልጎ የተረጋጋ ሁኔታ በተፈጠረበት አካባቢ መልሶ የማቀላቀል ሥራ መሥራት እንደሚገባም ይታመናል። ከገጠር የሚገፉና ወደ ከተማ የሚስቡ ምክንያቶችን ከመጥቀስ በቀር የሚደረጉ ፍልሰቶችን የሚገልጽ አሐዝ ማግኘት አዳጋች ነው።

አሁን ካለው አገራዊ ቀውስ አንጻር የዜጎች ከቦታ ቦታ ፍልሰት እያሻቀበ መሆኑ የሚነገር ቢሆንም፣ ፍልሰቱን ከባለፉት ጊዜያት ጋር በማነፃፀር፣ እንዲሁም የሚያስከትለውን ማኅበራዊ ቀውስ አስመልክቶ በየጊዜው ግንዛቤ መፍጠር፣ ፍልሰቱን ለመግታት የሚረዱ የመፍትሄ ሐሳቦችን በማቅረብ የሚመለከተው አካል መሥራት እንዳለበት ብዙዎች ያምናሉ።

ሆኖም በዋናነት ለዚሁ ዓላማ የተቋቋመው ሕጻናት፣ ሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጉዳዩ በቀጥታ እኔን ነው የሚመለከተው ቢልም፣ መረጃ ለመስጠት ባለመቻሉ ምክንያት አዲስ ማለዳ ሳምንቱን ሙሉ ደጅ ጠንታ ምላሽ ሳታገኝ ቀርታለች።


ቅጽ 4 ቁጥር 191 ሰኔ 25 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here