አሶሳ ዩኒቨርሲቲ 15 ብር የነበረውን እለታዊ የተማሪዎች ምገባ ወጪ በራሱ ፈቃድ ወደ 34 ብር አሳድጎ ተገኘ

0
1879

አሶሳ ዩኒቨርስቲ ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተቀመጠውን እለታዊ የተማሪዎች ምገባ ዋጋ በሕግ ከተፈቀደለት ውጪ በአንድ ተማሪ ላይ በቀን 19 ብር ጨምሮ ለአንድ ተማሪ በቀን 34 ብር ተመን ሲመግብ እንደነበር በኦዲት መረጋገጡ ተሰምቷል።

ዩኒቨርሲቲው ገንዘብ ሚኒስቴር ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያስቀመጠውን እለታዊ የተማሪ ምገባ ወጪ ተመን ማለትም 15 ብር የነበረውን፣ ወደ 34 ብር ከፍ በማድረግ በፈቃዱ በማኔጅመንት አጽድቆ ከፍተኛ ወጪ ማውጣቱን የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት አረጋግጫለሁ ብሏል።

መሥሪያ ቤቱ ይህን ያለው የመንግሥት ወጪ፣ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የ2012/13 በጀት ዓመት የፋይናንስ ሕጋዊነት ኦዲት ሪፖርት ላይ ያደረገው ክዋኔ ኦዲት ላይ ሰኞ ሰኔ 20/2014 ባደረገው ውይይት ላይ ነው።

ዩኒቨርሲቲው ገንዘብ ሚኒስቴር ያስቀመጠውን ሕግ ጥሶ 15 ብር የነበረውን የተማሪዎች ምገባ እለታዊ ወጪ በራሱ ፈቃድ 34 ብር አደርጎ በኦዲት ተገኝቷል የተባለው ከመስከረም 21/2012 እስከ መጋቢት 23/2012 ነው።

አሶሳ ዩኒቨርሲቲ በራሱ ፈቃድ ዋጋ ማስተካከያ ያደረገ ብቸኛ ዩኒቨርሲቲ መሆኑንም የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ዋና ኦዲተር መሰረት ዳምጤ ለቋሚ ኮሚቴው አስረድተዋል።

ከፍተኛ የሕግ ጥሰት ፈጽሟል የተባለው የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ከማል አብዱራሂም (ዶ/ር) የሕግ ጥሰቱ ለምን እንደተፈጸመ ከቋሚ ኮሚቴው ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ በቀን 15 ብር ተማሪ መመገብ በመቸገራቸው የዋጋ ማስተካከያውን እንዳደረጉ አብራርተዋል።

“በምንም ዓይነት ተአምር በቀን 15 ብር ተማሪ መመገብ አይቻልም” ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ የዋጋ ማስተካከያ እንዲደረግ ለመንግሥት ጥያቄ ማቅረባቸውን ጠቁመዋል።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እለታዊ የተማሪዎች ምገባ ወጪ ተመን በቀን 15 ብር መሆኑ ኹሉንም ዩኒቨርሲቲዎች ችግር ውስጥ የከተተ መሆኑን ዋና ኦዲተር መሰረት ዳምጤ ለቋሚ ኮሚቴው ገልጸዋል። የተማሪዎች ምገባ እለታዊ ወጪ ተመን ወቅቱን ያልዋጀ መሆኑን የጠቆሙት ዋና ኦዲተሯ፣ መንግሥት የዋጋ ማስተካከያ ማድረግ እንዳለበት ጠቁመዋል።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እለታዊ የተማሪዎች ምገባ ወጪ ተመን ከወቅቱ የዋጋ ንረት ጋር የማይጣጣም በመሆኑ የኹሉም ዩኒቨርሲቲዎች ፈተና ሆኗል ተብሏል። ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በበኩላቸው ማስተካከያ እንዲደረግላቸው መንግሥትን እየጠየቁ መሆኑ ተሰምቷል።
እስከ አሁን ባለው የኹሉም ዪንቨርሲቲዎች እለታዊ የተማሪዎች መመገቢያ ወጪ 15 ብር መሆኑ ይታወቃል።

የፌደራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት፣ የፌዴራል ተቋማት ዓመታዊ የበጀት አጠቃቀምን አስመልክቶ በየዓመቱ በሚያወጣው የኦዲት ግኝት ሪፖርት መሠረት፣ ብዙ ዩኒቨርሲቲዎች ከፍተኛ የሆነ የበጀት አያያዝ ጉድለት እንዳለባቸው ተመላክቷል።


ቅጽ 4 ቁጥር 191 ሰኔ 25 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here