በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ከ200 በላይ የሚሆኑ የቢል ቦርድ ማስታወቂያዎች ሕገ ወጥና ከስታንዳርድ በታች መሆናቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን ለአዲስ ማለዳ ገለጸ።
ከተማዋ ውስጥ በሚገኙ ከ400 በላይ ቢል ቦርድ ማስታወቂያዎች ላይ በተደረገ ቅኝት መሠረት ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ማስታወቂያዎች ደረጃቸውን ያልጠበቁና ሕጋዊ ያልሆኑ መሆናቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነትና የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር አረጋዊ ማሩ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ከቢል ቦርድ ውጭ ያሉ ሌሎች በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ማስታወቂያዎችም ሕገ ወጥ ከመሆናቸውም በላይ ከስታንዳርድ በታች መሆናቸውን ነው አዲስ ማለዳ ከባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ያገኘችው መረጃ የሚያመላክተው።
ከ400 በላይ በሚደርሱት ቢል ቦርዶች ላይ በተደረገው ዳሰሳ፣ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ማስታወቂያዎች ደረጃቸውን ያልጠበቁ መሆናቸው የተረጋገጠ ሲሆን፤ ሌሎቹ ማስታወቂያዎችም አብዛኛዎቹ ሕጋዊ ያልሆኑና ከስታንዳርድ በታች ናቸው ሲሉ አረጋዊ ገልጸዋል።
በተለያዩ ቦታዎች ማለትም በመብራት ፖል የሚንጠለጠሉ፤ በግለሰብ አጥር ላይ ያለባለቤቱ ፈቃድ በሕገ ወጥ ሁኔታ የሚሰቀሉ፤ በሕንፃዎች ላይ የሚለጠፉ፤ የኢትዮጵያን ባህልና እሴት መሠረት አድርገው ያልተጻፉና ያልተቀረጹ እንዲሁም በመንገድ ዳር ያለቦታቸው የተቀመጡ ማስታወቂያዎች የከተማዋን ውበት ማደብዘዛቸው ተገልጿል።
የከተማዋን ውበት ያጠለሹ ማስታወቂያዎችንም አረጋዊ በኹለት ዋና ዋና መደቦች ከፋፍለው ማብራሪያ ሰጥተዋል። ዳይሬክተሩ በመጀመሪያ ደረጃ የከተማን ውበት ያደበዘዙት በአብዛኛው በአደባባዮች እና ዋና ዋና መንገዶች የተቀመጡ እንዲሁም በሕገ ወጥ መንገድ በግለሰብ አጥር የተሰቀሉ ማስታወቂያዎች ናቸው ብለዋል።
እንዲሁም ወቅታቸውን ጠብቀው መነሳት ሲገባቸው ባለመነሳታቸው የበሰበሱና ያረጁ ማስታወቂያዎችም ለከተማዋ ፕሮቶኮል ጥላሸት በመሆን በኹለተኛ ደረጃ የሚጠቀሱ መሆናቸውን ለአዲስ ማለዳ አብራርተዋል።
በመሆኑም ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ከዚህ በኋላ በሕገ ወጥ መንገድ የሚለጠፉ እና የሚንጠለጠሉ፣ ከስታንዳርድ በታች የሆኑ ማስታወቂያዎችን የለጠፈ ድርጅት ወይም ግለሰብ ላይ እርምጃ እንደሚወስድ ነው የተገለጸው።
እርምጃም ለመውሰድ በቅድሚያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እየተካሄደ ይገኛል ያሉት የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ፤ በቀጣዮቹ ኹለት ሳምንታት ውስጥ እርምጃ መውሰድ እንደሚጀመር ጠቁመዋል።
ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የውጭ ማስታወቂያ ፈቃድ አሰጣጥ ሥርዓትን ለመቆጣጠር የሚያስችል ስታንዳርድ ይፋ ማድረጉንና የውጭ ማስታወቂያ ደንብ ማዘጋጀቱን ጠቁሟል።
በማስታወቂያ አዋጅ ቁጥር 759/2004 በተደነገገው ቅጣት መሠረትም ያለ ፈቃድ በመኪናዎች ላይ ማስታወቂያ ሲሠራ የተገኘ ሹፌር አንድ ሺሕ 600 ብር፤ ባለሥልጣኑ ያወጣቸውን ሕገ ደንቦች የተላለፈ ማንኛውም ሰው ኹለት ሺሕ ብር፤ በአደባባይ ላይ መልካም ሥነ ምግባርን የሚነካ ድርጊት አስቦ የተከለከሉ ማስታወቂያዎችን ያሰራጨ እና እንዲሰራጭ ያደረገ አካል አራት ሺሕ ብር እንደሚቀጣም ተመላክቷል።
በከተማዋ ያሉ የውጭ ማስታወቂያዎች በተማከለ የሕግ ማዕቀፍና አሠራር ሥርዓት ባለመመራታቸው ከኅብረተሰቡ እምነትና ባህል ያፈነገጡ የውጭ ማስታወቂያዎች እየተበራከቱ እንደሚገኙም አረጋዊ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
በመሆኑም፤ የከተማዋን ውበትና ጽዳትን የማይጠብቁና የሚያበላሹ የውጭ ማስታወቂያዎችን ለመቆጣጠር ሁሉም የከተማዋ ነዋሪዎች እና የማስታወቂያ ድርጅቶች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።
ቅጽ 4 ቁጥር 191 ሰኔ 25 2014



