ከ30 ሚሊዮን በላይ አንበጣዎች ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸው ስጋት ፈጥሯል

0
922

መነሻቸውን ከየመን በማድረግ በጅቡቲና በሶማሌ ላንድ አድርገው ወደ ኢትዮጵያ የገቡት ከ30 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የበረሃ አንበጣዎች በአራት ክልሎች በሚገኙ 56 ወረዳዎችና 1085 ቀበሌዎች መስፋፋታቸውን ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

በአፋር፣ አማራ፣ ኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች በሚገኙ ወረዳዎች የተስፋፉት የበረሃ አንበጣዎች፣ በየቀኑ 8700 ሜትሪክ ቶን የሰብል እህሎችን ሊያወድሙ እንደሚችሉም ሚኒስቴሩ ከተባበሩት መንግሥታት የምግብና ግብርና ተቋም እና ከምስራቅ አፍሪካ የበረሃ አንበጣ መከላከል ጋር በጋራ ሐሙስ መስከረም 22/2012 ረፋድ ላይ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

አንበጣዎቹ ወደ ሃገር ውስጥ መግባታቸውን ተከትሎም በግጦሽ መሬቶችና በቁጥቋጦዎች ላይ ጥቃት የደረሰ ቢሆንም በምግብ ሰብሎች ላይ ግን እስካሁን የደረሰ ጥቃት አለመኖሩን በሚኒስቴሩ የእፅዋት ጥበቃ ዳይሬክተር ዘብዴዎስ ሰላቶ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

አንበጣዎቹ በተለይም በምስራቁ የሀገሪቱ ክፍል፣ እንደ ማሽላ፣ ዘንጋዳ፣ በቆሎና ጫት ያሉ ከፍተኛ የአረንጓዴ ምርት ያለባቸው አካባቢዎች ላይ ተስፋፍተዋል ሲሉ ተናግረዋል። ስጋት ውስጥ ከወደቀው 17 ሺሕ 370 ሄክታር መሬት ውስጥ 28ሺሕ 671 ሄክታሩ ከሐምሌ 2011 እስከ መስከረም 2012 ድረስ የበረሃ አንበጣ መንጋ እንደታየባቸውም መግለጫው ያመለክታል።

በአንድ ዓመት ውስጥ ለ30 ያህል ጊዜያት ከተለያዩ የአረብ እና አፍሪቃ ቀንድ ሀገራት ተነስቶ ወደ ኢትዮጵያ ግዛት የገባን ሰብል አጥፊ የአንበጣ መንጋ በአውሮፕላን በታጀበ ርብርብ ማስወገዱን ያስታወሱት ዘብዴዎስ፣ አሁን የተከሰተውን የወጣት አንበጣ መንጋ በተመሳሳይ ለመከላከል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

አሁን የተከሰተው የበረሃ አንበጣ በአገሪቱ ለመራባት ምቹ ሁኔታ ካገኘ እስከ ቀጣይ አምስት ወራት ስጋት ፈጥሮ ሊቆይ እንደሚችል የግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል።

የበረሃ አንበጣው በፍጥነት ለመራባት ዝናባማ የአየር ሁኔታና እርጥብ አሸዋማ አፈር የሚፈልግ እንደመሆኑ ይህ ሁኔታ በሁሉም የአገሪቱ ክፍል የሚገኝ ስላልሆነ በአሁን ወቅት ፀረ-ሰብል ተባዩ በግብርናው ላይ እምብዛም ስጋት አይፈጥርም ብለዋል ዘብዲዮስ።

ይሁን እንጂ የወቅቱ የዝናብ ሁኔታ መሻሻል እያሳየ ስለሆነ በቀጣይ በበረሃ አንበጣው የሚጣሉ እንቁላሎች እርጥበት አግኝተው ሊፈለፈሉ ስለሚችሉ የዘርፉ ባለሞያዎች ከፍተኛ ክትትል እያደረጉ እንደሆነ ገልፀዋል። በአሁን ሰዓትም ባለሞያዎቹ ከህብረተሰብ ጋር በመሆን ለተባዩ መፈልፈያ አመቺ ቦታዎችን በመለየት የመከላከል ሥራ እየሠሩ ነው ብለዋል።

ይህ ፀረ-ሰብል አንበጣ ወደ መንጋ ሲሻገር ማንኛውንም እጽዋቶች የሚያጠፋ ስለሆነ በግጦሽና በእህል ሰብል ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርስ ስለሚችል ጥንቃቄ ያስፈልጋል ሲሉ ዘብዲዎስ ተናግረዋል።

በየመን ከፀጥታ መደፍረስ ጋር ተያይዞ፤ በሶማሌላንድ ደግሞ የተደራጀ የግብርና ዘርፍ አለመኖሩን ተከትሎ አገራቱ በአንበጣው ላይ ጠንካራ የመከላከል ሥራ ባለመሥራታቸው ከውጭ የሚመጣው የአንበጣ መንጋ በቀጣይ ከፍተኛ ስጋት ይፈጥራል ብለዋል።

አርሶ አደሩ የበረሃ አንበጣ ሲያይ ወዲያውኑ ከመጠቆም ባለፈ የአንበጣውን ማደሪያ ስፍራዎችን በመለየት ባለሞያዎች በሚሰጡዋቸው ምክረ ሀሳብ መሰረት ቁጥሩን መቀነስ እንዳለባቸው ተነግሯል። የበረሃ አንበጣ በሚያደርሰው የጉዳት መጠን በዓለም ካሉ ተባዮች ሁሉ በአደገኛነቱ የሚጠቀስ ነው።
በዚህም ሳቢያ አንበጣውን የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራ የዓለም አገራት በተናጠል ሳይሆን እርስ በእርስ መረጃዎችን በመለዋወጥ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመሆን በትብብር እንደሚሠሩ ይነገራል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here