ከአንድ መቶ ሺሕ በላይ ዜጎች መንግሥትን በመቃወም የረሃብ አድማ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ

0
376
  • ያለአግባብ የታሰሩ ዜጎች ሙሉ በሙሉ እንዲፈቱ ጠይቀዋል።

ሰባ የሚሆኑ ተፎካካሪ ፓርቲዎች መስከረም 21/2012 በሰጡት የጋራ መግለጫ በፖለቲካ ፓርቲ አባላቶች፣ በጋዜጠኞች እና በመብት ተሟጋቾች ላይ እስራት እና አፈና ተጠናክሮ መቀጠሉን ተከትሎ ጥቅምት 5 እና 6 ለኹለት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ የረሀብ አድማ ለማድረግ ከ100 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ አባላቶቻቸው ጥሪ አቀረቡ። ከ450 በላይ የሚሆኑት የፓርቲዎቹ አመራሮች ሙሉ ለሙሉ የረሃብ አድማው ተሳታፊ ይሆናሉ።

ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው፣ ‹‹በአሁኑ ጊዜ እኔ ያልኩት ብቻ ልክ ነው፣ እኔ የሰጠሁትን ብቻ ተቀብሉ፣ እኔ በወሰንኩላችሁና በፈቀድኩላችሁ ልክ ብቻ ኑሩ የሚል አዝማሚያ እየጨመረ መጥቷል›› ሲሉ ገልጸዋል።

የለውጥ ሒደቱ ከተጀመረ ገና አንድ ዓመት ተኩል በወጉ ሳይሞላ በመላው ሀገሪቱ ለማለት በሚያስችል ደረጃ በሆነ ባልሆነው ምክንያትና በሰበብ አስባቡ በዜጎች ላይ የሚደርሰው እንግልት፣ ስቃይ፣ እስራት፣ አፈና፣ ማዋከብ፣ ማስፈራሪያና ዛቻ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ በላኩት መግለጫ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት በመላው ሀገሪቱ በተከሰተው የኑሮ ውድነት ምክንያት ድሀው የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁርስ በልቶ ምሳውን ወይም ምሳውን በልቶ እራቱን መብላት በማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል ያሉት አመራሮቹ፣ ሕዝቡ በዚህ ሁኔታ በኑሮ ስቃይ ውስጥ በወደቀበት ጊዜ፣ መንግሥት የሕዝብን ችግር ለመፍታት ማድረግ የሚችለውን ነገር አለማድረጉም ሕዝቡ ከለውጡ ተጠቃሚ ሳይሆን ተጎጂ እየሆነ መምጣቱን በግልፅ የሚያሳይ ነው ብለዋል።
በሀገሪቱ የዛሬ አንድ ዓመት ተኩል ገደማ የመጣው የሥልጣን ለውጥ ቢሆን በአንድ ቡድን ወይም በተወሰኑ ቡድኖች መስዋዕትነት የመጣና ለሕዝብ በስጦታ የተሰጠ አለመሆኑን በመግለጫቸው ጠቅሰዋል። መላው ሕዝብ የደም፣ የአካልና የሕይወት መስዋዕትነት ከፍሎ ያመጣው ቢሆንም፣ አሁን እየታየ ያለው ሁኔታ ዛሬም የተጀመረውን ለውጥ ወደፊት እንዲሔድ ከማድረግ ይልቅ እንደ ባለፉት በርካታ የሀገራችን የለውጥ ሂደቶች ሁሉ ተደናቅፎ እንዲቀርና ለውጡ በጥቂት አምባገነኖችና ብልጣብልጦች ተጠልፎ የአምባገነኖች መጠቀሚያ ሆኖ እንዲቀር የሚያደርግ አዝማሚያ ነው ብለዋል።

‹‹በአሁኑ ወቅት ችግሩ በመላው ሀገሪቱ የቀጠለ ቢሆንም በተለይም በአማራ፣ በትግራይ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች በንፁሀን ዜጎች ላይ በተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች አባላትና ደጋፊዎችን ጨምሮ በዜጎች ላይ የሚደርሰው ጉዳት እንዲቆምና ያለአግባብ የታሰሩ ዜጎች በሙሉ እንዲፈቱ›› ሲሉ ጠይቀዋል።

በሕግና በሕገ-መንግሥት ሽፋን አፈና የመፈፀም ሂደት መጀመሩን አውስተው፣ የዜጎችን የመደራጀት፣ የመምረጥና የመመረጥ መብትና ነፃነትን የገፈፈ፣ አሳሪና አፋኝ የሆነ እና ለጥቂቶች መብት ጥቅም እና የበላይነት ታስቦ የተዘጋጀ የሴራ አዋጅ ፀድቋል፤ የምርጫ አዋጁ እኛን የማይወክል ነው ሲሉ ተችተዋል።

የምርጫ አዋጁ ከመፅደቁ በፊት ለመንግሥትና ለሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላት በሙሉ የአዋጁን ችግር እና በአዋጁ ላይ ያላቸውን ተቃውሞና ስጋት በተደጋጋሚ ማቅረባቸውንና በተደጋጋሚ መግለጫም መስጠታቸውን የሚናገሩት የፓርቲዎቹ አመራሮቹ፣ መግለጫ መስጠት ብቻ ሳይሆን በተማፅኖም ጭምር ጠይቀናል፤ ነገር ግን የሚሰማን አካል ማግኘት አልቻልንም ሲሉ አስታውቀዋል።

የመግለጫው አካል የሆኑት የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራር አካላት፣ አባላትና ደጋፊዎች በጋራ በመሆን ከሚያካሒዱት የረሀብ አድማ ባሻገር ከጥቅምት 7/2012 ጀምሮ በመላው ሀገሪቱ የሚከናወን በምርጫና በፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ ላይ የተቃውሞ ፊርማ የማሰባሰብ እንቅስቃሴ እንደሚኖርም ይፋ አድርገዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 48 መስከረም 24 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here