በጭልጋ ወረዳ 45 የአማራ ልዩ ኃይል ሕይወት አለፈ

0
1587
  • ከጎንደር መተማ የሚደረገው የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ሙሉ ለሙሉ ቆሟል።

በማዕከላዊ ጎንደር ጭልጋ ወረዳ ከአይከል ከተማ፣ ጓንግ እና ቡሆና ድረስ ከመስከረም 17/2012 ጀምሮ ለአምስት ቀናት የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ በአካባቢው የነበሩ ታጣቂዎች በከፈቱት ድንገተኛ ተኩስ ሰላም በማስከበር ላይ የሚገኙ 45 የአማራ ክልል የልዩ ኃይል አባላትን መግደላቸውን የአዲስ ማለዳ ምንጮች አረጋገጡ።

ማክሰኞ መስከረም 20/2012 በባህርዳር በሚገኘው ጽሕፈት ቤታቸው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ የተናገሩት የአማራ ክልል የሰላምና ሕዝብ ደኅንነት ቢሮ ኃላፊ አገኘሁ ተሻገር፣ የፀጥታ አካላት ወደ ማደሪያ ካምፓቸው ሲገቡ ከበባ እንደተፈፀመባቸው እና ‹‹ከደረሰባቸው ውርጅብኝ›› ራሳቸውን መከላከላቸውን ይናገራሉ። ‹‹ከታጣቂ ኃይሎች፣ ከፀጥታ አካላት የሞቱና የቆሰሉ አሉ›› ያሉት ኃላፊው ‹‹ሕግ ለማስከበር ተንቀሳቅሰናል፤ ሕግ ማስከበርም አለብን›› ሲሉ እየወሰዱት ያለው እርምጃ ሕጋዊ መሆኑን አስረድተዋል። የሞቱ የጸጥታ አካላት መኖራቸውን ቢያስታውቁም ቁጥራቸውን ከመጥቀስ ግን ተቆጥበዋል።

ችግሩ በተነሳበት እለት የክልሉ ልዩ ኃይል ወደ አይከል ከተማ ሊገባ ሲል በታጠቁ የአካባቢው ገበሬዎች በልዩ ኃይሉ ላይ ተኩስ እንደከፈቱ እና ልዩ ኃይሉም የአጸፋ መልስ የተኩስ ልውውጥ በማድረጉ ግጭቱ ሊቀሰቀስ እንደቻለ አገኘሁ ጠቁመዋል። በግጭቱ እስካሁን ቁጥራቸው ያልታወቀ ገበሬዎችም ሕይወታቸውን ማጣታቸውን ለማረጋገጥ ተችሏል። ሮይተርስ በመስከረም 23/2012 የዜና እወጃው በተቀሰቀሰው ግጭት በአምስት ቀናት ውስጥ የ20 ንፁሃን ዜጎች ሕይወት ማለፉን ዘግቧል።

በግንቦት 2008 የክልሉ መንግሥት በማእከላዊ ጎንደር ዞን በቅማንት የማንነት ጉዳይ ላይ በተደረገው የወሰን ማካለል ሒደት ራሳቸውን የቻሉ ነጻ ቀጠና ሆነው እንዲቀጥሉ በተወሰኑት ጀጀቢት፣ ሽንፋና ልንጫ ሦስት ቀበሌዎች በመንግሥትና በአካባቢው ገበሬዎች መካከል ከፍተኛ ያለመግባባት ምክንያት ሆኖ የሚታወስ ነው። በእነዚህ ሦስት ቀበሌዎች ከቅማንት በተጨማሪ የአማራ ተወላጆች በቀበሌዎች አብረው ይኖራሉ።

አገኘሁ፣ በሰጡት ማብራሪያ በማእከላዊ ጎንደር ጭልጋና አካባቢው የተፈጠረው የሰላም መደፍረስ፣ መንግሥት የማንነትና የአስተዳደር ጥያቄዎችን ለመፍታት እየሠራ ባለበት ወቅት ነው ሲሉ ተናግረዋል። የችግሩ ፈጣሪዎች “ከሌላ ወገን በሚያገኙት ድጋፍ” አካባቢውን የጦርነት ቀጠና የማድረግ ዓላማ እንዳላቸው ገልጸው፣ ነገር ግን የክልሉ መንግሥት የማያዳግም እርምጃ እንደሚወስድ ጨምረው ገልጸዋል።

ሰኞ መስከረም 19/2012 ከቀትር በኋላ በአይከል ከተማ አካባቢ አልፎ አልፎ ይሰማ የነበረው የተኩስ ድምፅ ጋብ ቢልም ወደ ጓንግና ቡሆና አካባቢ ግን እስከ ሐሙስ መስከረም 22/2012 የተኩስ ድምፁ ሊቆም አልቻለም። እንደ አዲስ ማለዳ ምንጮች ከሆነ ጓንግ አካባቢ ወደ 15 መኪና የሚሆኑ የክልሉ ልዩ ኃይሎች ወደ አይከል ከተማ መግባት ሳይችሉ መቅረታቸውን ተናግረዋል።

በአካባቢው አሁንም ድንገተኛ ጥቃት የሚያደርሱ ኃይሎች መኖራቸውንና የክልሉ መንግሥት ጥፋተኞችን ለመያዝ ጥረት እያደረገ እንደሆነም አገኘው አስታውቀዋል። “የጥፋት ኃይሉ ዋና ዓላማው የመተማ – ጎንደር መንገድን ዘግቶ ባለሀብቶች ምርታቸውን በወቅቱ እንዳይሰበስቡ እና ለገበያ እንዳያደርሱ በማድረግ በኢኮኖሚ ማዳከም ነው፣ በዚህ ደግሞ አንደራደርም፤ በአጭር ጊዜ መንገዱ ክፍት ይሆናል” ብለዋል አገኘሁ።

በልዩ ኃይሉና በመከላከያ ሰራዊቱ መካከል የቅንጅት ክፍተት እንደነበር ያነሱት አገኘሁ፣ በጋራ በመገምገምና የጋራ ኮሚቴ በማቋቋም ከወትሮው የተሻለ ቅንጅት እንደተፈጠረም ገልጸዋል። የጸጥታ ኃይሉም ጥፋት እንዳይደርሰ በትዕግስት እየተጠባበቀ እንደሆነም ነው የተናገሩት። ግጭቱ እንዳይበርድ የሚፈልጉ አካላትና የመገናኛ ብዙኀን መኖራቸውን፣ ግጭቱም በሌሎች አካላት ድጋፍ ያለው መሆኑ መረጋገጡንም ተናግረዋል።
አዲስ ማለዳ የአማራ ክልል የሰላምና ሕዝብ ደኅንነት ቢሮ ኃላፊን፣ የጭልጋ ወረዳ አስተዳደርና ሌሎች ባለሞያዎችን በስልክ ብታገኝም ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኞች ባለመሆናቸው አስተያየታቸውን ማካተት አልቻለችም።

በተመሳሳይም የመከላከያ ሰራዊት አባላት በዚሁ ወረዳ ለሚገኝ የልዩ ኃይል አባላት ቀለብ አድርሰው ሲመጡ ተኩስ እንደተከፈተባቸውም ታውቋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 48 መስከረም 24 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here