ቋሚ ኮሚቴው የወልቃይት ጠገዴና የራያ የማንነት ጥያቄዎች መልስ እንዲያገኙ እየሠራሁ ነው አለ

0
1046

የማንነት አስተዳደር ወሰን እና የሰላም ግንባታ ቋሚ ኮሚቴ የወልቃይት ጠገዴና የራያ የማንነት ጥያቄዎች መልስ እንዲያገኙ እየሠራሁ ነው ሲል አስታወቀ።

ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ቀርበው ሲጠየቁ የነበሩ የማንነት ይታወቅልን እና ማንነታችን ይከበርልን፣ የመካለል ጥያቄ፣ ራስን በራስ የማስተዳደር እና የመዋቅር ጥያቄዎች መረጃን የማጥራት ሥራ ማከናወኑን አመላክቷል።

ባለፈው አንድ ዓመት መረጃን የማጥራት ሥራ መሥራቱን የገለጸው ቋሚ ኮሚቴው፣ ከዘጠኝ ክልሎች 30 አቤቱታዎች እንደቀረቡለትም ነው ያስገነዘበው።

ከእነዚህ ውስጥ የራያ ጉዳይ እንደሚገኝበትና ለመፍትሄው ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር በመተጋገዝ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ጠቁሟል። ከቀረቡት ውስጥ ስድስቱ የማንነት ይታወቅልኝ ሲሆኑ የመካለል እና መዋቅር ጥያቄዎች ደግሞ 24 መሆናቸውን ጠቅሷል።

የወልቃይት ጠገዴን ጉዳይ መፍታት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ አጀንዳ አድርጎ በመወያየት አቅጣጫዎችን የማመላከት ሥራዎች እየሠራ መሆኑን በመጥቀስም፥ ቀሪ ሥራዎችን በማጠናቀቅ የውሳኔ ሐሳብ መሉ በሙሉ እንደተጠናቀቀ ለምክር ቤቱ እንደሚቀርብም ነው የገለጸው።

አቤቱታዎችን ለማጣራት እና ለመመርመር ይረዳ ዘንድ ቀድም ብሎ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ተለይተው ለአስተዳደር ወሰን እና ማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን የተላኩ 27 ልዩ ልዩ ጉዳዮች ኮሚሽኑ የደረሰበትን የጥናት ደረጃ ለመገምገም የጋራ ምክክር መደረጉንም አመላክቷል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተለዩት 5 የማንነት፣ 18 የመካለል፣ ሦስት የወሰን ይቁምልን ውዝግብ እና አንድ የውክልና በድምሩ 27 ለኮሚሽኑ የተላኩ ጉዳዮችን መነሻ በማድረግ የጥናት ውጤት ላይ ተመስርቶ ኮሚሽኑ ምክረ ሐሳቦችን ማቅረብ ቢኖርበትም የሥራ ጊዜውን ማጠናቀቁን ተከትሎ የጥናቱ ውጤት ለምክር ቤቱ ማስረከቡም ተመላክቷል።


ቅጽ 4 ቁጥር 193 ሀምሌ 9 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here