መንግሥት በታጣቂዎች የሚደርሱ ጥቃቶችን የማስቆም ኃላፊነቱን እየተወጣ አለመሆኑን ኢሰመጉ ገለጸ

0
1189

መንግሥት በታጣቂዎች የሚደርሱ ጥቃቶችን የማስቆም ኃላፊነቱን በበቂ ሁኔታ እየተወጣ አይደለም ሲል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) መንግሥትን ወቀሰ።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ መንግሥት ኃላፊነቱን በበቂ ሁኔታ እየተወጣ አይደለም ሲል የወቀሰው፣ ከሰሞኑ በአማራ ክልል ሰሜን ሽዋ ዞን በታጣቂዎች የተፈጸመውን ጥቃት አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ነው።

ከዓለም ዐቀፍ፣ አኅጉር ዐቀፍ እና አገር ዐቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ሕጎች ላይ እንደተደነገገው፣ መንግሥት የሰዎችን ሰብዓዊ መብቶች ማክበር፣ ማስከበር እና የማሟላት ኃላፊነት አለበት ያለው ኢሰመጉ፣ ይህ ሳይሆን ሲቀር እና በመንግሥት ቸልተኝነት የዜጎች ሰብዓዊ መብቶች ሳይከበሩ ሲቀሩ ዋነኛ ተጠያቂ ሊሆን የሚገባው መንግሥት መሆኑን ገልጿል።

ኢሰመጉ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ከኤፍራታና ግድም ወረዳና አዋሳኝ ከሆነው የጅሌ ጥሙጋ ወረዳ በኩል በመጡ ታጣቂዎች ሐምሌ 4/2014 በተፈጸመ ጥቃት በርካታ የጸጥታ አካላትና የቀበሌው አርሶ አደሮች ላይ ግድያ እና የአካል ጉዳት መፈጸሙን በጉዳዩ ላይ ባወጣው መግለጫ ይፋ አድርጓል። በኤፍራታና ግድም ወረዳ ስር የሚገኙ ኹለት ቀበሌዎች ውስጥ ያሉ መኖሪያ ቤቶች መቃጠላቸውንና በአካባቢው የሚኖሩ ነዋሪዎች አካባቢያቸውን ለቀው መፈናቀላቸውን ኢሰመጉ ከአካባቢው ካሰባሰባቸው መረጃዎች መረዳቱንም በመግለጫው አመላክቷል።

እንደ ኢሰመጉ መረጃ፣ ጥቃቱ የጀመረው ሐምሌ 3/2014 ምሽት እንደሆነ እና እስከ ሐምሌ 5/2014 ድረስ በአካባቢው ተኩስ እንደነበረ አስታውቋል። ጥቃቱን ተከትሎ በኤፍራታና ግድም ወረዳ መጤ ቀበሌና ዘንቦ ቀበሌ ከደሴ ወደ አዲስ አበባ የሚወስደው መንገድ ተዘግቶ እንደነበር ኢሰመጉ ከአካባቢው ሰዎች ተረድቻለሁ ብሏል።

ኢሰመጉ ባቀረበው ጥሪ፣ በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታና ግድም ወረዳ አጣዬ ከተማ ላይ በተደጋጋሚ በታጣቂ ቡድኖች የሚፈጸሙ ከፍተኛ የሆኑ ጥቃቶችን በአስቸኳይ ዘላቂ መፍትሔና ጥበቃን በማበጀት ችግሩን እንዲፈታ ጠይቋል።

እንዲሁም መንግሥት ጥቃት አድራሾችን ለፍርድ እንዲያቀርብ፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የማኅበረሰብ አንቂዎች፣ ጋዜጠኞች፣ ሲቪል ማኅበራት እና ሰብዓዊነት የሚሰማው አካል በሙሉ በተደጋጋሚ እየደረሱ ላሉ አሰቃቂ ጥቃቶች የፌዴራል መንግሥት እንዲሁም የሚመለከታቸው የክልል መንግሥታት ትኩረት ሰጥተው በመሥራት የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶች የማስከበር ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ በመወትወት የበኩላቸውን እንዲወጡ ኢሰመጉ ጥሪ አቅርቧል።

ኢሰመጉ በጉዳዩ ላይ ባወጣው መግለጫ፣ በአካባቢው በተከሰተው ጥቃት ላይ ተጨማሪ የምርመራ ሥራን እንደሚያከናወን እና የምርመራ ውጤቱን ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቋል። በአጣዬ አካባቢ በታጣቂ ኃይሎች የሚከሰተው ጥቃት በየጊዜው እየተደጋጋመ ቢሆንም፣ ጥቃቱን የሚያስቆም አካል እስካሁን አልተገኘም።

ከሰሞኑ ታጣቂ ኃይሎች ባደረሱት ጥቃት የአማራ ክልል መንግሥት የጸጥታ ኃይሎችና የአካባቢው ንጹሐን ዜጎች ላይ የሞት፣ የአካል ጉዳትና የንብረት ውድመት ማጋጠሙን የኤፍራታና ግድም ወረዳ አስታውቋል። በጥቃቱ በብዛት የሞቱትና የተጎዱት አማራ ክልል ልዩ ኃይል አባላት መሆናቸው የተሰማ ሲሆን፣ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ የክልሉ መንግሥትም ይሁን የዞኑ አስተዳደር በጉዳዩ ላይ ያለው ነገር የለም።


ቅጽ 4 ቁጥር 193 ሀምሌ 9 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here