በ2 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር የተፈረመና በ734 ሚሊዮን ብር በሥራ ላይ በዋለ ካፒታል የተቋቁመው ፀሐይ ባንክ ሐምሌ 16 ቀን 2014 በይፋ ሥራ መጀመሩን አስታውቋል።
‹ለሁሉ› የሚል መሪ ቃል ያለው ባንኩ፤ ዝቅተኛ የአክሲዮን ግዢውን ከብር 100 ሺሕ በመጀመር፣ በ373 ባለአክሲዮኖች ባንክን ለመመሥረት የሚያስችለውን ካፒታል በማሰባሰብና የመሥራች ጉባኤውን የካቲት 11 ቀን 2013 በሸራተን አዲስ ሆቴል በማካሄድ፤ የባንክ ኢንዱስትሪውን መቀላቀሉን የባንኩ ዋና ሥራ አስኪያጅ ያሬድ መስፍን ተናግረዋል።
የባንኩ ዓላማ የባንክ ኢንዱስትሪውን መቀላቀል ብቻ ሳይሆን፤ በፋይናንስ ዘርፉ በቂ ትኩረት ያላገኙትን የጥቃቅንና አነስተኛ፣ የግብርናውን ዘርፍ፣ የአምራች ኢንዱስትሪውን እንዲሁም አዋጭ ለሆኑ የፈጠራ ሥራዎችና ሥራ ፈጣሪዎች ተደራሽ መሆን ነው ያሉት ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ በዚህም ‹ለሁሉም የሆነ ባንክ› እንዲሆን የአገልጋይነትን እሴትን ተላብሶ ጉዞውን መጀመሩን ገልጸዋል።
ፀሐይ ባንክ የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራቱን በማዘመን፤ ዘመኑን የዋጀ “ቴሚኖስ ትራንዛክት አር 21” የለቀቀውን የኮር ባንኪንግ ሲስተምን በመላበስ፤ ደንበኛውን የባንክ አልግሎት እና ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎትን እንዲሁም የቢፒሲ ካምፓኒ ምርት የሆነውን ስማርት ቪስታ በመጠቀም አጠቃላይ የዲጂታል ባንክ አገልግሎት ይዞ መቅረቡንም ያሬድ ተናግረዋል።
ወደ ገበያው የገባው ፀሐይ ባንክ ኹሉን ዐቀፍ የባንክ አገልግሎት የሚሰጥ ባንክ ሲሆን፤ የኅብረተሰቡን የዕለት ከዕለት ሕይወት ለለወጥ ተግቶ የሚሰራ ባንክ ይሆናል ያሉት ደግሞ፤ የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ ታዬ ዲበኩሉ ናቸው። በተለይም የተሻሻሉ አሰራሮችን ይዞ በማቅረብ በኅብረተሰቡ የኑሮ መሻሻልና እድገት ላይ የበኩሉን ሚና ለመጫወት በትጋት እንደሚሠራም ተናግረዋል።
በባንኩ በምረቃ ሥነ ሥርዓት ዕለት 30 ቅርንጫፎች የባንክ አገልግሎት መስጠት የጀመሩ ሲሆን፤ በቅርብ ቀንም ባንኩ የቅርንጫፎቹን ቁጥር ከ50 በላይ የሚያሳድግ ይሆናል ተብሏል። እንዲሁም በአንድ ዓመት ውስጥ 100 ቅርንጫፎችን በኹሉም የአገራችን አካባቢዎች ለመክፈት የሚያስችለውን ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተነግሯል።
ቅጽ 4 ቁጥር 194 ሐምሌ 16 2014


