በደቡብ ክልል ኮንሶና አማሮ ልዩ ወረዳ በተከሰተው ድርቅ በተለይ ሕጻናትና አቅመ ደካሞች በረሃብ እየሞቱ መሆኑን ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
በአማሮ ልዩ ወረዳ ከ2012 ጀምሮ ለሦስት ዓመት የዘለቀ ድርቅ የተከሰተ ሲሆን፣ በዚህ ዓመት ደግሞ በኮንሶና በሌሎች ቦታዎችም እየተስፋፋ ነው ተብሏል።
በኮንሶ ዞን በተከሰተው ድርቅ ባለፉት አራት ወራት ከ13 በላይ ሕጻናት መሞታቸውና ከ190 ሺሕ በላይ ሰዎች እርዳታ እንደሚጠብቁ ተገልጿል።
በአማሮ ልዩ ወረዳ ኬረዳ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር ጴጥሮስ ቤንጆ፣ በወረዳው ቆላማ ቀበሌዎች ድርቁ እጅግ የበረታ መሆኑን አንስተው፣ ‹‹እኔ ባለሁበት አካባቢ ከ10 በላይ ሰዎች ሲሞቱ ዐይቻለሁ። ምን ሆነው ነው የሞቱት ሲባል በረሃብ ነው፣ በእጦት ነው ይባላል።›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ስለሆነም፣ በድርቁ አስከፊነት የተነሳ ምንም የሌላቸው ድሆች በየዕለቱ እየሞቱ ነው ሲሉ ገልጸው፣ በብዙዎች ቤት የበሰለ ምግብ የለም ሲሉም አክለዋል።
ድርቁ ባስከተለው ሰፊ ረሃብ በተለይ ሕጻናት፣ ነፍሰ ጡሮችና አቅመ ደካማ አሮጊቶች እንዲሁም አዛውንቶች ክፉኛ መጎዳታቸውን ያነሱት አርሶ አደሩ፣ የቤት እንስሳትም ቢሆኑ በመኖ እና በውሃ እጦት እያለቁ ነው በማለት ተናግረዋል።
አርሶ አደሩ አክለውም፣ በሰው ነፍስ ላይ መከራ ነው እየወረደ ያለው ካሉ በኋላ፣ በዚህ ወቅት በአማሮ ወረዳ አዋሳኝ በሆኑት በኮንሶ እንዲሁም ቡርጂ ወረዳ ድርቁ እየተስፋፋ እንደሚገኝ በመጥቀስ፣ ወደ አርባ ምንጭ አካባቢ ስንሄድም ድርቅ መኖሩ ይታወቃል ነው ያሉት።
በፊት በየኹለት እና አምስት ወሩ እርዳታ ይቀርብ እንደነበር በማንሳትም፣ አሁን ላይ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ጦርነት አለ እየተባለ እርዳታ ከቀረበልን ሰባት ወር ሆኖናል ብለዋል። በቅርቡ ስንዴ የቀረበ ቢሆንም ለአንድ ቀበሌ ብቻ እንጂ ድርቁ ላጠቃቸው ኹሉም ቀበሌዎች ሊቀርብ አልቻለም ሲሉ ገልጸዋል።
በአካባቢው ከመጋቢት ወር ወዲህ እስካሁን ዝናብ አለመዝነቡን በመጥቀስ፣ አሁንም የዝናብ ምልክት አለመኖሩን ነዋሪዎች አክለዋል።
የአካባቢው ነዋሪዎች ከድርቅ በተጨማሪ በግጭትም ጉዳት እየደረሰባቸው መሆኑን በመግለጽ፣ በአማሮ ልዩ ወረዳ ቆላማ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች ወደ ደጋው ክፍል ቀያቸውን ጥለው እየሄዱ እንደሆነ ጠቁመዋል።
መንግሥት እርዳታ እንዲያቀርብላቸውና አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግላቸው የጠየቁት ነዋሪዎቹ፣ እስከ አሁንም የወረዳው መንግሥት ለዞን፣ ዞኑም ለክልል እያለ እስከ ፌዴራል ድረስ ችግራችን የቀረበ ቢሆንም የተገኘ ዕልባት የለም ብለዋል።
አዲስ ማለዳ ከአማሮ ልዩ ወረዳ አደጋ ስጋት አመራር ጽሕፈት ቤት እንዲሁም ከኮንሶ ዞን የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ቢሮ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ብትሞክርም ሳይሳካ ቀርቷል።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም ባለፈው ሚያዚያ ወር እንዳስታወቀው፣ በደቡብ እና ደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያ በተከሰተው ድርቅ በጠቅላላው 7 ነጥብ 2 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች ተርበዋል። እንደ ድርጅቱ ገለጻ፣ ድርቁ በተከሰተባቸው የአገሪቱ አካባቢዎች ከአንድ ሚሊዮን በላይ የቀንድ ከብት ያለቀ ሲሆን፣ በ40 ዓመታት ውስጥ ከታየው ኹሉ የከፋ የተባለው ድርቅ ሰብል አውድሟል፣ የውኃ ምንጮችንም አድርቋል።
ቅጽ 4 ቁጥር 194 ሐምሌ 16 2014



