• ኤርፖርቱ ሐምሌ 2016 ይጠናቀቃል
ከአዳዲስ ኤርፖርቶች መካከል አንዱ የሆነው የደብረ ማርቆስ ኤርፖርት፣ የግንባታ ሂደቱ በቁፋሮ እንዲሁም ቦታ ጠረጋ ላይ መሆኑን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለአዲስ ማለዳ ገለጸ።
ግንባታውን ለመጀመር የታቀደው በፈረንጆች መስከረም 15/2021 ቢሆንም፣ የግንባታ ቦታው በአርሶ አደር ሰብል በመሸፈኑ ምክንያት ሥራው በታሰበው ጊዜ አልተጀመረም ያለው ተቋሙ፣ ይህም በመሆኑ ሥራው የተጀመረው በፈረንጆች ጥር 16/2022 ነው ሲል ገልጿል።
ስለሆነም፣ የግንባታ ሂደቱን አስመልክቶ አሁን ላይ የዲዛይን ሥራው በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ በመግለጽ፣ የቦታ ጠረጋ እና የቁፍሮ ሥራ እየተከናወነ ሲሆን፣ የተመረጠ አፈር እና የተፈጨ ድንጋይ (ጠጠር) ለማምረት በሂደት ላይ ነው ብሏል።
በዚህም የግንባታ ውሉን ያሸነፈው ሥራ ተቋራጭ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን፣ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር የግንባታ ውል በመፈፀም ቦታውን ተረክቦ ግንባታውን በማከናወን ሂደት ላይ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አሳውቋል።
ጠቅላላ የኤርፖርቱ የይዞታ ስፋት 150 ነጥብ 32 ሄክታር ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ለ126 ነጥብ 42 ሄክታር ክፍያ መፈጸሙን እና ቀሪው 23 ነጥብ 9 ሄክታር የካሳ ክፍያ ግምት ደግሞ በመሠራት ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል።
በተጨማሪም ወደ ኤርፖርቱ የሚወስደው መዳረሻ መንገድ የይዞታ ስፋት እና የተነሺ አርሶ አደሮች የካሳ ክፍያ ግምት በመሠራት ላይ እንደሚገኝ ነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ያሳወቀው።
ይህም የኤርፖርቱ ይዞታ ከአርሶ አደር ንብረት ነጻ ባለመደረጉ ሥራውን ያጓተተ ሲሆን፣ ቀሪ የካሳ ክፍያ ያልተከፈለ የኤርፖርት ይዞታ እና የመዳረሻ መንገድ መኖሩ ሥራውን ለመሥራት እንቅፋት ሆኗል ነው ያለው።
ግንባታው ከሚቀጥለው ዓመት በኋላ በ913 ቀናት ውስጥ፤ በፈረንጆች ሐምሌ 17/2024 ይጠናቀቃል ተብሏል።
ለፕሮጀክቱ የተያዘለት በጀት የአርሶ አደሮችን የካሳ ክፍያ ሳይጨምር 6 መቶ ሚሊዮን ብር ነው። ሆኖም አሁን ካለው የዋጋ ግሽበት አንጻር የበጀት ማስተካከያ ይደረጋል ወይስ በተያዘው በጀት ሥራው ይጠናቀቃል የሚለውን፣ የዋጋ ማስተካከያ የኮንትራት ውሉ በሚፈቅደው መሠረት የሚታይ ይሆናል ሲል ተቋሙ አመላክቷል።
የአየር ማረፊያውን ደረጃ አስመልክቶም፣ አሁን ባለው ሁኔታ አገር ዐቀፍ የበረራ አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን፣ ወደፊት የሚኖረውን የትራፊክ ፍሰት (የመንገደኛ ብዛት) ታሳቢ አድርጎ በሚከናወነው የማስፋፊያ ሥራ እስከ ዓለም ሠቀፍ በረራዎችን ሊያስተናግድ በሚችል መልኩ የግንባታው ቦታው ተመርጧል ነው የተባለው።
እንዲሁም ግንባታው ሲጠናቀቅ በሚኖረውን የመንገደኛ ብዛት ታሳቢ ተደርጎ፣ የበረራ አገልግሎት መስጠት የሚጀምር ሲሆን፣ እንደ አስፈላጊነቱ የመንገደኞች ቁጥር ሲጨምር የበረራው ቁጥርም የሚጨምር መሆኑን ተቋሙ አስገንዝቧል።
የአየር ማረፊያው በሚገነባበት ጊዜ እና ግንባታው ካለቀ በኋላ ለአካባቢው ማኅበረሰብ የሥራ እድል ከመፍጠር ባሻገር፣ የሕዝቡን የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ጥያቄ ምላሽ ይሰጣልም ተብሏል።
እንዲሁም በአካባቢው ከፍተኛ የግብርና ምርት እና እንስሳት ሀብት በመኖሩ ባለሀብቶች/ኢንቨስተሮችን ለመሳብ ከፍ ያለ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ነው የተገለጸው።
መንግሥት የትራንስፖርት ዘርፉን ለማስፋፋት የያዘውን ዕቅድ ታሳቢ በማድረግ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ፣ በኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎች የአየር ትራንስፖርት አገልግሎቱን ለማስፋፋትና አምስት አዳዲስ ኤርፖርቶችን በሚዛን አማን፣ ነገሌ ቦረና፣ ያቤሎ፣ ደብረ ማርቆስ እና ጎሬ መቱ በማስገንባት ሂደት ላይ እንደሚገኝ አሳውቋል።
ቅጽ 4 ቁጥር 194 ሐምሌ 16 2014


