በአገራችን የመጀመሪያው የግል የሞባይል ገንዘብ ዝውውር አገልግሎት ሥራ ሊጀምር ነው

0
1288

የግል የሞባይል ገንዘብ ዝውውር አገልግሎትን ለመስጠት በ200 ሚሊዮን ብር የተፈቀደ ካፒታል የተቋቋመው ካቻ ዲጂታል ፋይናንሺያል ሰርቪስ አክስዮን ማኅበር አገልግሎቱን ለመስጠት የሚያስችለውን ፍቃድ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በማግኘት ሥራ ለመጀመር ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አስታውቋል።

ይህም ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያገኘው የሞባይል ገንዘብ ዝውውር አገልግሎት ፍቃድ በአገሪቱ የመጀመሪያው የግል የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት ሰጪ ኩባንያ እንዲሆን አስችሎታል።

ኩባንያው ለዘርፉ ዋና ተዋናዮች፣ አጋሮች እና ባለድርሻ አካላት ባሳለፍነው ሐሙስ ሐምሌ 21 ቀን 2014 አገልግሎቱን በይፋ የማስተዋወቅ መርሃ ግብር አከናውኗል።

በመርሃ ግብሩ ላይም የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር)፣ የአገር ዐቀፍና ዓለም ዐቀፍ ገንዘብ አስተላላፊ ተቋማት ኃላፊዎች፣ የኩባንያው መሥራቾች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዉበታል።

በመድረኩም ካቻ ዲጂታል ፋይናንሺያል ሰርቪስ አ.ማ. ዋና ሥራ አስፈፃሚው አብርሀም ጥላሁን፤ የካቻ ሞባይል ገንዘብ ዝውውር አገልግሎት በጥሬ ገንዘብ የሚከናወኑ ግብይቶችን በማስቀረት የዜጎችን ኑሮ ለመሻሻል ጉልህ ሚና እንደሚጫወት አስረድተዋል።

አክለውም ኩባንያው ያልተለመዱ የፋይናንስ አሠራሮችን በመተግበር ከፋይናንስ ሥርዓት ውጪ ያሉ ዜጎችን ለማገልገል መቋቋሙን ገልጸው፤ በዚህም አካታችነት፣ ፈጠራን፣ ተመጣጣኝ ዋጋን እና ዘላቂ እድገትን የሚያራምድ የፋይናንስ አቅርቦትን ለኅብረተሰቡ የማድረስ ርዕይን ይዞ መነሳቱን ተናግረዋል።

የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸው ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ በቴክኖሎጂ የተደገፉ የግብይት ሥርዓቶችን ለማከናወን የሚያስችሉ ሥራዎችን በመደገፍና በማበረታታት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ አያይዘውም ካቻ ዲጂታል ፋይናንሺያል ሰርቪስ የጀመረው የሞባይል ገንዘብ ዝውውር አገልግሎት በአገራችን የኢኮኖሚ ዘርፍ ላይ ተዋናይ ለመሆን ለሚጥሩ ኹሉ ተስፋን የሚፈነጥቅ ነው ብለዋል።

ካቻ ፋይናንሻል ሰርቪስ አ.ማ የግል የሞባይል ገንዘብ ዝውውር አገልግሎትን ለመስጠት በ13 ኢትዮጵያዊያን ባለሀብቶች የተመሠረተ ኩባንያ ሲሆን፤ አገልግሎቱን ለማሳለጥ ይረዳው ዘንድም በመላ የአገሪቱ ክፍሎች ከ30 ሺሕ በላይ ወኪሎችን በማሰማራት በቅርቡ ወደ ሥራ እንደሚገባም ተገልጿል።

ኩባንያው ላለፉት ሦስት ዓመታት በኢትዮጵያዊያን እና የውጪ አገር ባለሙያዎች የካቻ የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት መስጫ ቴክኖሎጂን ሲያበለፅግ መቆየቱንም አስታውቋል።

ካቻ የሞባይል ገንዘብ ዝውውር አገልግሎትን በመጠቀም የሞባይል ሂሳብ መክፈት፣ ገንዘብ ገቢ እና ወጪ ማድረግ፣ አነስተኛ ቁጠባ፣ ዋስትና የማይጠየቅባቸው አነስተኛ ብድሮች፣ አነስተኛ የኢንሹራንስ አገልግሎቶች፤ የቀጥታ ክፍያዎች፤ ዓለም ዐቀፍ ሐዋላ፣ ገንዘብ ማስተላለፍ፣ የሞባይል አየር ሰዓት፣ የኤቲ ኤም ገንዘብ-አልባ ግብይቶችን ማከወንና ሌሎች አዳዲስ አገልግሎቶችን ማግኘት እንደሚቻልም በመርሃ ግብሩ ላይ ተነግሯል።


ቅጽ 4 ቁጥር 195 ሐምሌ 23 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here