የዐቃቤያነ ሕግን የሥራ አፈጻጸም የሚመዝን አዲስ ሥርዓት ተጀመረ

0
1104

የፍትሕ ሚኒስቴር የዐቃቤያነ ሕግን የሥራ አፈጻጸም የሚመዝን አዲስ ሥርዓት አጥንቶ ሥራ መጀመሩን አስታወቀ።

በሠራተኞች መካከል ውድድርን በማበረታታት የተገልጋይን እርካታ ለመጨመር፣ ወጥ እና ዘመናዊ የባለሙያዎች የሥራ አፈጻጸም መመዘኛ ሥርዓት ሊኖር ይገባል ሲል ሚኒስቴሩ ገልጿል።

የምዘና ስርዓቱ ያለበት ክፍተት ቢስተካከል ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚችል ባለሙያን ለመፍጠር እንደሚያስችል ታምኖበት፣ አዲስ የዐቃቤያነ ሕግ አፈጻጸም ምዘና ሥርዓት መመሪያ ቁጥር 32/2014 ወጥቶ በሥራ ላይ መዋሉ ተጠቅሷል።

በመመሪያው የተደነገገው የመመዘኛ ስርዓት ከዚህ ቀደም ከነበረው ጋር ሲነጻጸር አስገዳጅነት ያለውና እያንዳንዱን ተግባራት፣ ክብደት እና ውስብስብነት ከግምት ያስገባ ከመሆኑም በላይ አፈጻጸሞች ከውጤት ባሻገር ቅልጥፍናን፣ ጥራት እና የሥነ-ምግባር ሁኔታን ከግምት ያስገባ መሆኑ ለየት ያደርገዋል ነው የተባለው።

በምዘና ስርዓቱ ዐቃቤያነ ሕግ ብቻ ሳይሆኑ የሥራ ክፍል ኃላፊዎችም ጭምር ይመዘናሉ የተባለ ሲሆን፣ በተለይም በአመራር ክሕሎት የሙያ ብቃት እንዲሁም የሥራ ውጤታማነት ከፍተኛ ነጥብ እንዲይዙ መደረጉ ኃላፊዎች በውድድር ስሜት በእቅድ የያዙትን ተግባር በተሻለ ውጤት ማከናወን እንዲችሉ ያደርጋል ተብሏል።

ሥርዓቱ በምዘናው አነስተኛ ውጤት የሚያስመዘግቡ ባለሙያዎችን አቅም ለማጎልበት ተገቢውን እርምጃ ለመውሰድ እንዲሁም የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡትን ደግሞ ለማመስገን እና ለማበረታታት ሌሎችም ከዚሁ ተሞክሮ በመውሰድ በተቋም ደረጃ ተቀራራቢ የአገልጋይነት ስሜት እንዲፈጠር የራሱ ሚና እንዳለውም ታምኖበታል።

በተቋሙ የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ ስር የሚገኙ የሥራ ክፍሎች ኃላፊዎች በተገኙበት የምዘና ስርዓቱን ይዘት እና አተገባበር፣ በዐቃቤያነ ሕግ አስተዳደር ጉባዔ ጽሕፈት ቤት አማካኝነት ቀርቦ ውይይት ከተካሄደበት በኋላ ስርዓቱ ወደ ተግባር መግባቱ ተመላክቷል።


ቅጽ 4 ቁጥር 195 ሐምሌ 23 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here