አንድን ክስተት መግቢያችን እናድርግ፤ በአንድ የኩላሊት እጥበት ማዕከል ውስጥ ነው። ለኩላሊት እጥበት በማዕከሉ ከተገኙ ሕሙማን መካከል አንድ ሰው ተከታዩን አደረገ። ቢጂአይ ኢትዮጵያ ታከምበት ብሎ ካኖረለት አንድ መቶ ሺሕ ብር ላይ ቀንሶ ለአንድ የኩላሊት እጥበት ታካሚ የዐሥር እጥበት ሒሳብ ከፈለ። በነገሩ ያልተደነቀ አልነበረም። የተለመደም ስላልሆነ ነው፤ የኩላሊት ህሙማን ለእጥበት የሚያወጡት ቀላል የማይባል ወጪ በመሆኑ እርስ በእርስ መደጋገፍ የሚታሰብ አይደለምና።
ይህ ያደረገው ሥመ ጥሩ ሙዚቀኛ ኤልያስ መልካ ነው።
ከአንድ ዓመት በላይ የኩላሊት እጥበት ሲያደርግ በቆየበት የኩላሊት እጥበት ማዕከል ጤናውን ሲከታተሉ የቆዩ የሕክምና ባለሙያዎች በኤልያስ ህልፈት የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን ገልጸዋል። ከእነርሱ መካከል የሆነችው ሲስተር የውብዳር አበራ (ሥሟ የተቀየረ)፣ የኤልያስን መልካምነትና ለሰው አሳቢ መሆን ለአዲስ ማለዳ ገልጻለች።
“በጣም ትሁት ሲሆን ከሁላችንም ጋር ቅርበት ነበረው፤ ፕሮግራም ሲኖርም ይጋብዘን ነበር። ለምሳሌ አውታር የሙዚቃ መገበያያ ሲመረቅ ጠርቶ ጋብዞናል” ብላለች። ይሁንና ግን ለራሱ በዛ ልክ የሚጨነቅ እንዳልነበረም ትናገራለች። “ለራሱ ሳይሆን ለሌላው የኖረ ሰው ነው። ለራሱ አይጠነቀቅም፤ አታድርግ የተባለውን ያደርጋል፤ ለሌሎች የሚጨነቀውን ያህል ለራሱ አያስብም” ስትል ገልጻለች።
ኤልያስ መልካ በሙዚቃው ዘርፍ ያቀናበረውና አሻራውን ያሳረፈበት አልበም፣ ለእውቅና እና ክብር ያበቃቸው አንጋፋ ድምጻውያን፣ ለሙዚቃ ዘርፍ ያበረከታቸው አስተዋጽዖዎች ተደጋግመው ሲነሱ ነበር። ከዛም በላይ ደግሞ ተቆጥረው የማያልቁ መልካም ሥራዎችን በብዙዎች ሕይወት ውስጥ አኑሯል። ዘመኑን ሙሉ የሚበቃውን እንዳረሰ ገበሬ ኤልያስ በለጋ ዕድሜው አብዝቶ የሠራቸው ሥራዎች ቀሪ ዘመኑን ሁሉ እየመነዘረ ሊጠቀምባቸው የሚችሉ ይሆኑ ነበር፤ ዘርፉም በዛ ልክ የማይከፍል ከመሆኑ ውጪ እርሱም በጊዜ አሸለበ እንጂ።
እንደ ኤልያስ መልካ ያሉ ጥቂት ሰዎች፤ ለሽልማት ራሱ ሽልማት ናቸው ወይም ዋንጫና ወርቅ ቢያዘጋጁና ቢሸልሟቸው እንኳን ከሽልማቱ በልጠው ያስጨንቃሉ። ለአክባሪው ለራሱ ክብር ሆነው ግራ ያጋባሉ። በሰው ቋንቋ በሰው ሚዛን “እናመሰግናለን” ብቻ እስኪተርፍ ቃል ያሳጣሉ። ሙዚቀኛው ኤልያስ መልካ ለብዙዎች በቅርበት ለሚያውቁት በርቀትም በሥራው ላገኙት ሁሉ ከዚህ ቃል በላቀ ስሜት የተቀመጠ ሰው ነው ማለት ይቻላል።
የዜማና ግጥም ደራሲና የሙዚቃ አቀናባሪው አማኑኤል ይልማ ስለኤልያስ ለአዲስ ማለዳ ሲናገር፤ ትውውቃቸው በያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት እንደሚጀምር ያስታውሳል። ምንም እንኳ ኤልያስ በትምህርት ቤት ቆይታው አራተኛ ዓመት ተማሪ ሳለ ‹መዲና ባንድ›ን ተቀላቅሎ የሠራ ቢሆንም ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ ‹‹ዜማ ላታስ››ን እንደመሠረቱና አብረው ይሠሩም እንደነበር አማኑኤል ያወሳል።
ዜማ ላስታስ በ1990ዎቹ መጀመሪያ ዓለማየሁ እሸቴ፣ ጋሽ ባህታ፣ ላፎንቴን፣ ትዕግስት በቀለ፣ ጋሽ አበራ ሞላን የመሳሰሉ ድምጻውያን ጋር የሠሯቸውን ሥራዎች ተቀርጸው ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ከወጡ በኋላ ባንዱ እውቅናን አግኝቷል። በስቱድዮም ኤልያስ ፈር ቀዳጅ ነበር የሚለው አማኑኤል፤ አበጋዝ ክብረወርቅ ሺዎታ በውጪ አገር ሆኖ በሚሠራበት ጊዜ በጊዜው የነበረውን ቴክኖሎጂ በመጠቀም በስቱድዮና ኪቦርድ ይዞ የሠራው የመጀመሪያው የቴዲ አፍሮን “አቦጊዳ” አልበም ነበር ሲል ተናግሯል።
“ኤልያስ ሙዚቃን በጣም አሳድጓል፤ ይህም እንኳን ባለሙያው አድማጭ በሚረዳበት መልኩ የታየ ነው፤ እስከ አሁንም እኛ እየሠራን ያለነው የእርሱን ፈር በመከተል ነው።”
ስለ ኤልያስ ስብዕናም ሲያነሳ፤ በተለይ ከቅጂ መብት ጋር በተያያዘ ሙዚቀኞች መሰብሰብ በነበረባቸው ጊዜ የኤልያስ ድርሻ እጅግ የላቀ እንደሆነ ያነሳል። እንደውም በቤቱ ስብሰባ እንዲደረግ በሩን የከፈተ፤ ቤቱም ለሁሉም ክፍት የነበረ እንደሆነ አስታውሷል። “በሙዚቀኛ ያልተለመደ ደግነት ኤልያስ ነበረው፤ ከዛ ውጪ ማንም ሰው ቢጋጭና በባንድ ውስጥ አለመስማማት ሲኖር፤ እርሱ ሁሌም አስታራቂ ሽማግሌ ነበር” ሲል ይመሰክርለታል።
በሥራው ምክንያት ሦስት ቀን ያለእረፍት ቁጭ ብሎ ያድር እንደነበር፤ ድምጻውያን አረፍ ብለው አድረው ለሥራ ማልደው ሲመጡ ሳይተኛ እንደሚያገኙትና ይህም እረፍት ማጣት ጤናው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳሳደረበትም አማኑኤል በሐዘን ስሜት ይናገራል።
ድምጻዊ ሚካኤል በላይነህ በበኩሉም ይህን የአማኑኤልን ሐሳብ ይጋራል። ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበረው አጭር ቆይታ፤ ኤልያስ ብዙ ሰጪ መሆኑን ጠቁሟል። “ኤልያስ በተፈጥሮ መስጠት ባሕሪው ነው” ያለው ሚካኤል፤ ይህን ከራሱ እየቀነሰ መስጠቱ፣ ከእንቅልፍና እረፍቱ እየቀነሰ መሥራቱ ለጤናው መጓደል ምክንያት ነው ባይ ነው። ታድያ ይኼ መሰልቸት የሌለበት የኤልያስ ለጋስነት በኑሮ ብቻ ሳይሆን በሥራውም የተገለጠ እንደሆነ ሚካኤል ይናገራል። ይህም ነው ኤልያስን ከሌሎች የሙዚቃ አቀናባሪዎች የተለየ የሚያደርገው።
“ኤልያስ ከሌሎች ከማውቃቸው አቀናባሪዎች ልዩ የሚያደርገው የፕሮድዩሰር[ነት] ችሎታ አለው” አለ ሚካኤል፤ ይህንንም ሲያብራራ፤ ኤልያስ የተሰጠውን ዜማ ሠርቶና አቀናብሮ መስጠት ብቻ ሳይሆን በሥራው መካከል ላይ ሙዚቃው ከድምጻዊው ጋር ይሔዳል አይሔድም፣ ያምርበታል ወይስ አያምርበትም የሚለውንም አገናዝቦና አመዛዝኖ ይናገራል። ዜማው ላይ ብቻ ሳይሆን ግጥም ላይም አስተያየት ይሰጣል። ግጥምና ዜማው ምን ያህል ተጣጥሟል የሚለውንም የሚያይ ባለሙያ እንደሆነ ይናገራል። ይህ ከልምድ የተገኘ እንዲሁም በተፈጥሮም የሚታደሉት ነው ሲል ይገልጻል።
አዲስ ነገር ጋዜጣ በ2001 የካቲት ወር ዕትሟ ላይ “ምዑዝ ኤልያስ” በሚል ርዕስ የኤልያስ መልካን የሕይወትና የሥራ ጉዞ በዳሰሰችበት ገጽ፤ ኤልያስ በሕይወት ብዙ ፈተናዎች እንደገጠሙትና በዚህም ሁሉ ውስጥ ግን ማንነቱና ጸባዩ ሳይቀየር እንዳለፈ ከትባለች። ይህን ለመረዳት ከዚህ በተጨማሪ በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን “አርሂቡ” በተባለ ሳምንታዊ ዝግጅት ላይ እንግዳ በሆነ ጊዜ የተናገረውን እናንሳ።
መቼም የትኛውም ሰው ምንም ሥራ ሲሠራ አንዱ ዓላማው ገቢ ለማግኘት ነው። ይህም ሲሆን በተቻለ መጠን ከፍ ያለ ገቢ ለማግኘት ጥረት ይደረጋል። ታድያ ኤልያስ ደግሞ በአንጻሩ ነው የሚሠራው። ብዙ የሙዚቃ ባለሙያዎችና አብረውት የሠሩት እንደሚናገሩት የበለጠ ትኩረቱ አቅም አላቸው ብሎ ካመነባቸው አዳዲስ ድምጻውያንና ሙዚቀኞችና ጋር መሥራትን ነበር። ለምን?
“እነርሱ [ዝነኞቹ] የፈለጉበት ቦታ መድረስ ይችላሉ። ሁሉም የሙዚቃ አቀናባሪ ለእነርሱ ለመሥራት ዝግጁ ነው፤ ስለሚታወቁም አማራጭ አላቸው፤ ገንዘብም ስላላቸው ከፍለው ማሠራት ይችላሉ። እኔ መሥራት የምፈልገው አዳዲስ ልጆች ላይ ነው፤ ወጥተው እንዲታዩም እፈልጋለሁ” ይላል። አዳዲስ ሙዚቀኞች ጆሮ የሚሰጣቸው በሌለበት፣ የሚከፍሉት ብዙ ገንዘብና በገበያው በአንድ ጊዜ ሰብረው የሚገቡበት የቀደመ የእውቅና መንገድ ባይኖራቸውም፤ ከገቢው ይልቅ ሙዚቃን ያስቀደመው ኤልያስ፤ ለእነዚህ ልጆች ቅድሚያውን ይሰጥ ነበር።
ታድያ ቀድመው በሙዚቃው ዘርፍ የቆዩና ከእርሱ ጋር ለመሥራት የሚፈልጉትን ደግሞ “ታገሱ” ይላቸዋል። ትዕግስታቸውም ለእርሱ ካላቸው ፍቅር የተነሳ እንደሆነ ስለሚያስብና ጊዜ እንደሚወስድባቸውም ስለሚያውቅ፤ የበለጠ የእነዚህን ሙዚቀኞች ሥራ ከአዳዲሶቹ አያስቀድምም። ይህ የኤልያስ የሙያ ሥነ ምግባሩ፣ ጊዜ ወስዶ፣ ተጨንቆና ብዙ አስቦ የጠራ ሥራ የማበርከት ፍላጎቱ ዛሬ በጆሯችን ደርሰው ለምናጣጥማቸው አይረሴና ዘመን አይሽሬ ሙዚቃዎች ምክንያት ሆኗል፤ ላይረሳም ተከትቧል።
ልክ የዛሬ ሳምንት የኤልያስ መልካ ህልፈት እንደተሰማ መገናኛ ብዙኀን፣ ማኅበራዊ ገጾችም ሥሙን ከወትሮው በተለየ ደጋግመው አነሱ። ቀድሞ የእርሱን ሥራዎች ሲያዳምጡ የቆዩ ጆሮዎች አሁን የእርሱን ታሪክ ማድመጥ ጀመሩ። “ሙዚቃ ጉድሽ ፈላ!” ተባለ።
የሙዚቃ ተመራማሪው ሰርጸ ፍሬስብሐት ልክ የዛሬ ሳምንት ቅዳሜ፣ መስከረም 24/2012 የቀብር ሥነ ስርዓቱና ሽኝት መርሃ ግብሩን በተመለከተ ምን እንደሚኖር ለመንገር በፋና ቴሌቭዥን በቀረበ ጊዜ ሲናገር፤ ኤልያስ ጊዜ እንደሌለው አውቆ ሥራውን በፍጥነትና በብዛት እንደሠራ ሰው ነው ሲል ገለጸው።
ሰኞ፣ መስከረም 26/2012 በብሔራዊ ቴአትር አዳራሽ በተካሔደው የሽኝት መርሃ ግብር ላይ፤ የኤልያስ የቅርብ ጓደኞቹ የሚባሉት ጆኒ ራጋ እና ኃይሌ ሩትስ ለቃሉ የሚታመንና በተናገረው የሚጸና ሰው እንደሆነ መስክረውለታል። ኤልያስ ቃሉን የሚጠብቅ፣ በራሱ ችግር ውስጥ ሆኖም የሰውን ችግር የሚያዳምጥና በአምላኩ ቃል የሚኖር ነው ሲሉም ገልጸውታል።
ኤልያስ ለዝና ግድ እንደሌለውም ብዙዎች መስክረውለታል። መገናኛ ብዙኀን ይህን ሰው ደጋግመው ሽፋን ሳይሰጡት መቅረታቸውም አንዱ ምክንያት ይኸው ሳይሆን አይቀርም። ድምጻዊ ጆኒ ራጋ ሲናገር “ለዝና ግድ የለውም እንጂ በመላው ዓለም ሊታወቅ ይችል ነበር፤ ጥልቅ ሙዚቀኛ ነው ብዬ አምናለሁ። ከሆሆታውም ርቆ ሊሆን ይችላል፤ ግን ዋናው ቦታ ላይ ነበር።” ብሏል።
ኃይሌ ሩትስም በሽኝት መርሃ ግብሩ ላይ በመድረክ ሲናገር፤ “ኤልያስ ለብዙዎች ታላቅ የሙዚቃ ባለሙያ ሲሆን ለእኛ ለወንድሞቹ የሰውነት ስብዕናውና መልካምነቱ በተለምዶ እንደሚነበቡ የሕይወት ታሪኮች ሳይሆን የእውነት የኖረው ነው። ያስተማረንን እና የተናገረውንም በሕይወት ኖሮ አሳይቶናል” ሲል ገልጾታል።
ታድያ ከሕመሙ ጊዜ ጀምሮ በተለይም ከኹለት ዓመት ወዲህ በጤናው መታወክ ምክንያት በጋራ ያሳለፉትን ከባድ ጊዜም ኃይሌ ሩትስ ሳይጠቅስ አላለፈም። በእነዚህ ከባድ ጊዜያትም ጓደኞቹ አብረውት እንደነበሩና እንዳልተለዩት ጠቅሶ፤ “እርሱ ለሰዎች በጨነቃቸው ሰዓት ይደርስ ነበር። እኛም ለእርሱ ያንን አድርገናል። መስዋዕትነትም ከፍለናል፤ በዚህም አይቆጨንም” ሲል አክሏል።
በሽኝት ስርዓቱ ወቅት በብሔራዊ ቴአትር ከተገኙ የጥበብ ሰዎች መካከል ገጣሚ ኤፍሬም ስዩም ከጋዜጠኞች ለቀረበለት ጥያቄ መልስ ሲሰጥ፤ ሞተ የሚባለው አዲስ ነገር መሥራት ያቆመ ሰው ነው አለ። እናም በየጊዜው ለአድማጩ አዳዲስ የሙዚቃ ሥራዎችን ሲያቀርብ የኖረው ኤልያስ ተፈጥሯዊ በሆነው ሞት ሲወሰድ “ያረገ እና ያረፈ ሰው ነው” ሲልም ገልጾታል።
አዲስ አበባ ከተማ አብነት በሚባለው ሰፈር ተወልዶ ያደገው ኤልያስ፤ ከ11ኛ ወደ 12ኛ ክፍል ሲዘዋወር ጀምሮ ነበር ሙዚቃን በትምህርት የተዋወቀው። ከዛም በያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ገብቶ መማሩን ቀጠለና የአራተኛ ዓመት ተማሪ ሳለ ለመጀመሪያ ጊዜ መዲና የተባለ የሙዚቃ ባንድ ተቀላቀለ። ከዚህ አሃዱ ብሎ የጀመረው የሙዚቃ ሥራው አንድም ቀን እረፍት ሳይሰጠው እርሱም ልረፍ ልተው ሳይል ቆይቶ የሁሉም ሰው ልጅ ዕጣ የሆነውን ሞት ቀምሷል።
በሙዚቃው 19 ዓመታትን ብቻ የሠራ ቢሆንም ከ40 ዓመት በላይ የቆየ ያህል ሥሙ በብዙዎች እዝነ ልቦና ታትሞ ቀርቷል። በድምጻውያን በኩል ካበረከታቸው አርባ በላይ አልበሞችና እጅግ በርካታ ነጠላ ሙዚቃዎች ውጪ በፀረ ኤድስ ዘመቻ የተዜሙትን “ማለባበስ ይቅር”፣ “መላመላ”፣ “ኑር ባታምንም”ን ጨምሮ “አሽከርክር ረጋ ብለህ”፣ ከአፍሪካ ኅብረት ጋር በተያያዘ “አዲስ አስተሳሰብ” የኤልያስ አቅም የታየባቸው፣ አሻራውም ያረፈባቸው ኅብረ ዝማሬዎች ናቸው።
ከላይ እንደተባለው እንደ ኤልያስ ያሉ ባለሙያዎችን፣ ሥራቸውን በታማኝነትና በብቃት ያከናወኑ፣ ስብዕናቸውም የላቀ ሰዎችን በማመስገን አክባሪ የበለጠ ያተርፋል። አዲስ ማለዳም መልካም ሥራው በምድር አይረሴ አድርጎት ይቆያልና፤ ለነፍሱም እረፍትን የሚያሰጥ እንዲሆንለት፤ ነፍሱን በገነት ያኑርልን ትላለች። ለቤተሰቦቹ፣ ለቅርብ ወዳጆቹና ለኢትዮጵያ ሙዚቃ አድማጮች ሁሉ መጽናናትንም ትመኛለች።
ቅጽ 1 ቁጥር 49 ጥቅምት 1 2012



