ማረሚያ ቤቶች የማምረቻ ኢንዱስትሪዎችን እንዲያቋቁሙ የሚፈቅድ ሕግ ተረቀቀ

0
587

ባሳለፍነው ሳምንት መስከረም 29/2012 ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የፌደራል ማሪሚያ ቤት ረቂቅ አዋጅ የማረሚያ ቤት አስተዳደርን ወደ ኮሚሽን እንዲያድግ እና ተጨማሪ ዘጠኝ ሥልጣኖች እንዲኖሩት ያቀረበ ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከል ታራሚዎችን በሥራ ላይ ለማሰማራት የሚያስችሉ የማምረቻ ኢንዱስትሪዎችን እንዲያቋቁም ሥልጣን የሚሰጥ ነው።

በተጨማሪም የማሰልጠኛ ተቋማት እንዲኖሩት፣ ለፖሊሶች የጋራ መኖሪያ ካምፖችን እንዲገነባ እና የውስጥ ገቢዎቹን ለመንግሥት ገቢ ማድረጉ ቀርቶ ከበጀት ውጪ ላሉ ሥራዎች እንዲያውል የሚሉት የተወሰኑት ናቸው።

በክልሎች እነዚህን በታራሚዎች እውቀት እና ጉልበት የመነጩ የወስጥ ገቢዎች በመደጎሚያነት በመጠቀም የተሻለ አገልግሎት እየተሰጠ ሲሆን ይህንን ተሞክሮ በመውሰድ የታራሚዎችን የግል፣ የጋራ እና አካባቢያዊ ንፅህና ለመጠበቅ የገንዘብ አቅም የሌላቸው ታራሚዎች ሲፈቱ ወደ ቤተሰቦቻቸው የሚመለሱበትን የትራንስፖርት እና ምግብ ወጪ ለመሸፈን እንዲሁም መሰል ሌሎች ወጪዎችን ከውስጥ ገቢ ላይ ማረሚያ ኮሚሽኑ እንዲሸፍን ሥልጣን ይሰጣል።
በተጨማሪም ታራሚዎች በሚፈቱበት ጊዜ ከማህበረሰቡ ጋር በቀላሉ እንዲቀላቀሉ እና ከወንጀል እንዲርቁ ለማድረግ ባለሞተር ተሽከርካሪን ለመንዳት የሚያስችል ሥልጠና እንዲያገኙ የማድረግ ኃላፊነትንም ለኮሚሽኑ የሚሰጥ ነው።

ረቂቁ በተጨማሪም ከዚህ ቀደም በፖሊስ ጣቢዎች ስር ሲተዳደሩ የቆዩትን ማረፊያ ቤቶችንም በማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ስር ሆነው እንዲተዳደሩ የሚያደርግ ሲሆን አንድ ማረሚያ ቤት ማረሚያ እንዲባል ለሕዝብ በግልጽ የሚታወቅ መሆን እንዳለበት ረቂቁ ደንግጓል።

ለዚህም እንደ ምክንያት በኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት በማረሚያ ቤቶች ውስጥ የሚፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ለማስቀረት እና ማረሚያ ቤቶችን ለሕዝብ ግልፅ እንዲሆኑ ለማድረግ ይረዳል በሚል እንደሆነ ለተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የማብራሪያ ኖት ያስረዳል። ባለፉት ጊዜያት በሕዝብ በማይታወቁ እስር ቤቶች ሲሰቃዩ የነበሩ ዜጎች ጉዳይ ለሕዝብ ይፋ መሆኑን ተከትሎም በሕግ ማዕቀፍ በሚደገፍ መልኩ የማረሚያ ቤቶችን ለሕዝብ ግልፅ ማድረግም አስፈላጊ መሆኑ መካተቱን ረቂቁ ያስረዳል።

‹‹የማረሚያ ጠባቂ›› የሚለው ሥያሜ ‹‹የማረሚያ ፖሊስ›› በሚል የተቀየረ ሲሆን የማረሚያ ፖሊሶች ሥራ እንቅስቃሴን እና ጉልበት የሚጠይቅ በመሆኑ የጡረታ መውጫ እድሜ ዝቅ እንዲል በማድረግ ከኮንስታብል እስከ ዋና ሳጅን ማዕረግ 50 ዓመት፣ ከረዳት ኢንስፔክተር እስከ ኢንስፔክትር 52 እና ከዋና ኢንስፔክትር እስከ ኮሚሽነር 55 የዕድሜ ክልል እንዲሆን ያደርጋል።

ልዩ አያያዝን በተመለከተም በተለይ የሴት እስረኞች የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች መንግሥት እንደሚያቀርብ እና ከእናቶቻቸው ጋር የሚገኙ 18 ወር ያልሞላቸው ህፃናት መንግሥት ለእንክብካቤአቸው የሚሆን በጀት እንደሚመድብም በረቂቁ ላይ ተቀምጧል። በተጨማሪም በፍርድ ቤት እውቅና ያገኘ የአቅም ችግር ካለ መዋእለ ህፃናት እና አስፈላጊ የሆኑ ማቆያዎችን መንግሥት እንደሚያሟላ ይደነግጋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 49 ጥቅምት 1 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here