የተለያዩ አካባቢዎች ያለው ከታሪፍ በላይ ክፍያ ማኅበረሰቡን እያማረረ ነው

0
717

በኢትዮጵያ በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች ከታሪፍ በላይ በሆነ የዋጋ ጭማሪ መማረራቸውን ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።

ቅሬታ አቅራቢዎቹ በገለጹት መሠረት በኢትዮጵያ በሚገኙ የተለያዩ ክልሎች በመንግሥት በኩል የተደረገው የነዳጅ ድጎማን ምክንያት በማድረግ አሽከርካሪዎች ከተተመነው ታሪፍ ውጪ እያስከፈሉ ነው ተብሏል።

የታሪፍ ጭማሪው ከአዲስ አበባ ጀምሮ ነው ሲሉ የተናገሩትና አዲስ ማለዳ በላምበረት መናኽሪያ አግኝታ ያነጋገረቻቸው ሞገስ ይርዳው የተባሉ ተሳፋሪ፤ ወደ ደብረብርሃን ለመሄድ ታሪፉ 82 ብር መሆኑን ጠቅሰው ሹፌሮች የሚያስከፍሉት ግን 150 ብር እና ከዚያ በላይ ነው ብለዋል።

ከተመን ውጪ የሆነው የታሪፍ ጭማሪ መፍትሄ እየተሰጠው አይደለም ያሉት ሞገስ፤ ከኹለት ወር በፊት ከአዲስ አበባ ወደ ደብረ ብርሃን ለመጓዝ ሲከፈል የነበረው 100 ብርም ከታሪፍ ውጪ እንደነበር አስታውሰዋል። ያም መስተካከል ሲገባው ይባስ ብሎ ወደ 150 ብር ከፍ ብሏል ሲሉ ቅሬታቸውን አንስተዋል።

በሀረር ክልል የሚገኙ ተሳፋሪዎች በበኩላቸው፣ የትራንስፖርት ክፍያው በተተመነው ታሪፍ ልክ እንዲከፈል ማድረጉ ይቅርና በመናኽሪያው ውስጥ እንኳን ቅሬታ የሚቀበል አካል ከቢሮ አይገኝም ብለዋል።

ከሐምሌ ወር ጀምሮ የነዳጅ ድጎማ ቢደረግም፣ የሕዝቡን ችግር ሊቀርፍ እንዳልቻለና የትራንስፖርት ክፍያውም በታሪፉ መሠረት እየተከፈለ አለመሆኑን ነው ተገልጋዮች ያመላከቱት።

በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ራያ ቆቦ ወረዳ ተኩለሽ ከተባለችው ታዳጊ ከተማ ወደ ቆቦ ከተማ የሚጓዙ ተሳፋሪዎች ታሪፉ 30 ብር ለሆነ መንገድ በሹፌሮች አስገዳጅነት 100 ብር እየከፈሉ መሆኑንም ጠቁመዋል።

መንገድ ትራንስፖርት ለጉዞው የተመነው ታሪፍ 30 ብር ቢሆንም፣ ሹፌሮች ግን በራሳቸው ፈቃድ ክፍያውን ወደ 100 ብር ከፍ እንዳደረጉት ነው ተሳፋሪዎቹ የተናገሩት።

ሞላ መለሰ የተባሉት ተሳፋሪ ‹‹ከተኩለሽ ቆቦ ለመሄድ ታሪፉ 30 ብር ለሆነ መንገድ 100 ብር እየከፈልን ነው›› ብለዋል። የሚመለከተውን አካል ኹሉ ጠይቀናል ያሉት ሞላ፤ ‹‹ኃላፊዎቹም ዐይተው እንዳላዩ ነው የሚያልፉቸው። የመንገድ ትራፊክም ከወር አንድ ጊዜ ነው ብቅ የሚለው።›› ሲሉ ተናግረዋል።

የታሪፍ ጭማሪው የተስተዋለው ከአነስተኛና መለስተኛ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ጀምሮ በሌሎች አገር አቋራጭ አውቶብሶችም ጭምር መሆኑን ቅሬታ አቅራቢዎቹ ተናግረዋል።

የሰላም፤ የስካይ፤ የዓባይ እና ሌሎች መሰል አገር አቋራጭ አውቶብሶች የሚያስከፍሉት የብር መጠንም በየወቅቱ እየጨመረ ነው ተብሏል።

ከአዲስ አበባ ወደ ደብረ ማርቆስ የሚጓዙ ተሳፋሪዎች በበኩላቸው፣ ክፍያው በኹለት ወራት ውስጥ ከእጥፍ በላይ መጨመሩን ገልጸዋል። ተሳፋሪዎቹ እንደሚሉት ከሆነ፤ ከማርቆስ ወደ አዲስ አበባ ለመጓዝ ከኹለት ወር በፊት 355 ብር የነበረ ሲሆን፤ በአንድ ወር ቆይታ ውስጥ የ100 ብር ጭማሪ አሳይቷል።

ይህ ጭማሪ መስተካከል ሲገባው አሁንም ይባስ ብሎ ከ455 ወደ 600 ብር ከፍ ማለቱን አንስተዋል። በሌሎች የተለያዩ ሥፍራዎችም የክፍያ ጭማሬ መኖሩን ተሳፋሪዎች ተናግረዋል።

የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ ሚኒስቴር የኮምዩኒኬሽንና የሕዝብ ግንኙነት ሥራ አስፈፃሚ ታጠቅ ነጋሽ፣ መንግሥት ያደረገውን የነዳጅ ድጎማ አስመልክቶ በከፍተኛ ሁኔታ ከታሪፍ በላይ እየተከፈለ መሆኑን መስክረዋል።

ከድጎማው ጋር በተገናኘም ቁጥጥር አስፈላጊ ሆኖ ስለተገኘ ከፌዴራል ፖሊስና ከክልል የጸጥታ ኃይሎች ጋር በመሆን ግብረ ኃይል ተቋቁሞ በቅርቡ ጉዳዩን የመከታተል ሥራ ይጀመራል ሲሉ ታጠቅ ገልጸዋል።

ሥራ አስፈጻሚው በቅርብ ጊዜ ይፋ የሚደረጉ አንዳንድ ችግሩን ለመፍታት የሚረዱ አቅጣጫዎች መኖራቸውን ነው ለአዲስ ማለዳ የገለጹት።


ቅጽ 4 ቁጥር 196 ሐምሌ 30 2014

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here