አዲስ አበባ እንደዋና ከተማ ከተመሠረተችበት ጊዜ አንስቶ ገጥሟት የማያውቅ የግዛት አከላለል ውዝግብ ውስጥ መሆኗ እየተነገረ ዓመታት አልፈዋል። በዋና ከተማ ላይ ልዩ ጥቅም በሚል የተጀመረ ነዋሪዎችን እንደ አንደኛና ኹለተኛ ዜጋ የሚያደርግ አስተሳሰብ፣ መፍትሔ ባለማግኘቱ መዘዝ እያመጣ መሆኑን የሚናገሩ በርካቶች ናቸው።
በኢሕአዴግ ዘመን አርሶ አደሮች ለመኖሪያ ግንባታ ሲፈናቀሉ የተከፈላቸው ካሳ መጠን አግባብ አይደለም በሚል የተጀመረ ተቃውሞን ብዙዎች ደግፈውት ነበር። የገበሬው ሕይወት አላግባብ እንዲጎዳ ተደርጓል በሚል የቀረበን ስሞታ የአዲስ አበባ ነዋሪ ጭምር ስለደገፈው፣ በቆጠበው ብር የተሠራ ኮንዶሚኒየም ቤትና ተጨማሪ ካሳ ሲሰጥ ተቃውሞ አላሰማም ነበር።
ነገር ግን፣ በዚህ በአርሶ አደሩ ብሶት ላይ ተመርኩዞ የከተማዋን ግዛት ለማሳነስ የተጀመረ እንቅስቃሴ መኖሩን ከኹለት ዓመት ገደማ በፊት በማስረጃ አስደግፈው የባልደራስ ፓርቲ ፕሬዝዳንት የሆኑት ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እና 360 ሚዲያ በጋራ ይፋ ያደረጉበት ሂደት ነበር።
በወቅቱ እውን ይሆናል ብሎ ያልጠበቀ የአዲስ አበባ ነዋሪ በዳርቻ ያሉ ወረዳዎች የሥራ አስፈፃሚዎች ቦታ ከኦሮሚያ ክልል በተላኩ ሰዎች እንዲያዝ ተደርጓል ሲባል፣ የፀጥታ ኃይሎችም ከክልሉ እንዲመጡ ተደርጓል ሲባል ጥቂቶች ቢቃወሙም፣ ከአከላለል ጋር በተገናኘ ሲባል የነበረው እውን ይሆናል ብሎ ያመነ እምብዛም እንደነበር ሠሞኑን እየተነገረ ይገኛል።
የአዲስ አበባ ወሰን ብዙ ውዝግብ እንደሚያስነሳ ያላጡት የአሁኑ የከተማው አስተዳዳሪዎች፣ አሁን የአከላለል እንቅስቃሴ ተጀመረ ብለው ለመናገር ወቅቱን ለምን መረጡ በሚል ትችት እየበረታባቸው ይገኛል። ለኹለት ዓመት ያህል ውስጥ ለውስጥ ሲሠሩ የቆዩትን በይፋ ተግባራዊ ለማድረግ ለምን አሁን ወሰኑ የሚለው በብዙዎች ዘንድ መነጋገሪያ ሆኗል።
ከሚሰጡ መላምቶች መካከል ስለአዲስ አበባ ሲቆረቆሩ የቆዩት የባልደራስ ፓርቲ ፕሬዝዳንት እስክንድር ነጋ ሥልጣናቸውን መልቀቃቸውና ሌሎች ደጋፊዎቻቸው ታስረው ገለል በመደረጋቸው ነው የሚሉ አሉ። ከሐምሌ አጋማሽ ጀምሮ አመራሮቹ በሥራ ገበታቸው ላይ አለመገኘታቸውን በመገንዘብ ማንም የሚቃወመን የለም በሚል እሳቤ አሁን ይፋ ለማድረግ መመረጡን የሚናገሩ አሉ።
ጊዜው የተመረጠበት ወቅት ማወዛገቡ እንዳለ ሆኖ፣ ይካለላል በተባለው አዲሱ ወሰን መሠረት ብዙ የአዲስ አበባ አካባቢዎች በኦሮሚያ ስር እንዲሆኑ ይደረጋል መባሉ ቅሬታ እየፈጠረ ይገኛል። ድርድርና ውይይት ተብሎ በኹለቱም ወገን ኦሮሚያን የወከሉ ሰዎች ተነጋግረው ነው የሚወስኑት በመባሉ ገና ከወዲሁ ዘላቂነቱን ጥያቄ ውስጥ ከቶታል።
“የተከፈላቸው ካሳ አንሷቸዋል” ተብሎ በሥማቸው የተነገደባቸው ምስኪኖቹ አርሰው አደሮች አሁን ያሉበት ቤትና ቦታ በዋናዋ ከተማ ስር ቢሆን ወይስ በኦሮሚያ ክልል ስር ቢሆን ነው ይበልጥ ተጠቃሚ የሚሆኑት ብሎ ማሰብን ይጠይቃል።
ከዋናዋ ከተማ ነዋሪነት ወደ ክልል ነዋሪነት ያለፍላጎታቸው የሚቀየሩ የየትኛውም ብሔር ተወላጆች ቢሆኑ፣ በኢኮኖሚ ረገድ ጉዳት እንደሚደርስባቸው በማስላት ሂደቱ ጊዜያዊ የፖለቲካ ትኩሳት የሆነ ነው ብለው የሚያጣጥሉት በርካቶች ናቸው።
ቅጽ 4 ቁጥር 197 ነሐሴ 7 2014



