”በሶማሌ እና አፋር ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች የሚገኙ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በአስከፊ ችግር ውስጥ ይገኛሉ።”:- የሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት

0
1031

ሐሙስ ነሐሴ 12 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በሶማሌ እና አፋር ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች በሚገኙ አካባቢዎች በተፈጠረው ግጭት የተፈናቀሉ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በአስከፊ ችግር ውስጥ እንደሚገኙ የሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት አስታወቀ።

የሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በሶማሌ እና አፋር ክልል አወሳኝ አካባቢዎች በሚኖሩ የክልሉ ነዋሪዎች ላይ የደረሰውን መፈናቀል አስመልክቶ በዛሬው ዕለት መግለጫ አውጥቷል።

በመግለጫውም፤ ከመኖሪያ ቀዬአቸው የተፈናቀሉት ዜጎች በአሁኑ ወቅት በሲቲ ዞን ኤረር ወረዳ አስቡሊ እና በድዌይ በሚባል አካባቢ የተሰባሰቡ ቢሆንም፤ በክረምቱ ከባድ ዝናብ ምክንያት መንገዶች በመቆራረጣቸውና ወደ አካባቢው ተሽከርካሪ ሊገባ ባለመቻሉ ምንም አይነት የእለት ደራሽ እርዳታ ለማቅረብ አልተቻለም ብሏል።

በአሁኑ ወቅት ተፈናቃዮቹ በከፍተኛ ችግር ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፤ የክልሉ መንግስት ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመቀናጀት አፋጣኝ እርዳታ ለማቅረብ ከፍተኛ ጥረትና ርብርብ እያደረገ እንደሚገኝም አስታውቋል።

ለዚህም፤ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፋ ሙሀመድ እና ም/ርዕሰ መስተደድር ኢብራሂም ኡስማን የተካተቱበት የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ልኡካን ቡድን ተፈናቃዮች በሚገኙበት በሲቲ ዞን በመገኘት ሰብአዊ ድጋፍ ለማድረስ በማስተባበር ላይ እንደሚገኙም ተገልጿል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here