ሐሙስ ነሐሴ 12 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የኢፌዲሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 6ኛ የፓርላማ ዘመን፣ 1ኛ ዓመት፣ በ1ኛ አስቸኳይ ጉባኤው በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ይኖሩ የነበሩ የ6 ዞኖችና የ5 ልዩ ወረዳ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በአንድ ክልል የእንደራጅ አቤቱታን ተቀብሎ ከመረመረ በሗላ ሕዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
ምክር ቤቱ በዚህ አስቸኳይ ጉባኤው የ6 ዞኖችና የ5 ልዩ ወረዳዎች በአንድ ክልል መጠቃለል ያስፈልገናል ብለው ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት፤ በየደረጃው በዞንና ልዩ ወረዳ በየብሔረሰብ ምክር ቤቶች ውይይት ተደርጎበትና ጸድቆ መምጣቱ ተገልጿል።

እነዚህ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ያቀረቡትን ጥያቄ አስመልክቶ የማንነት፣ የአስተዳደር ወሰን እና የሰላም ግንባታ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ በቀረበው ጥያቄ ላይ ሲመክርና ሲመረምር ቆይቶ ለምክር ቤቱ የውሳኔ ሐሳብ ማቅረቡ ተነግሯል፡፡
ምክር ቤቱ፤ የወላይታ፣ የጋሞ፣ የጎፋ፣ የደቡብ ኦሞ፣ የጌዴኦ፣ የኮንሶ ዞኖች፣ እንዲሁም የደራሼ፣ የአማሮ፣ የቡርጂ፣ የአሌ እና የባስኬቶ ልዩ ወረዳ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በጋራ ”የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል” የመመስረት ጥያቄ ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 47/3 እና ከምክር ቤቱ ደንብ ቁጥር 4/2014 አንቀጽ 19/2 አንጻር ውሳኔ ለመስጠት እንዲያስችል የሕዝብን ይሁንታ ማረጋገጥ ስለሚያስፈልግ ከማንኛውም ተጽእኖ ነጻ በሆነ መልኩ ገለልተኛ በሆነው ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ አማካኝነት በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ ሕዝበ ውሳኔ እንዲደራጅ መወሰኑ ተገልጿል።

የሕዝብ ውሳኔው ውጤትም ሪፖርት ለምክር ቤቱ እንዲቀርብ፣ እንዲሁም የሕዝብ ውሳኔው ሂደት ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና የሕዝብን ሰፊ ተሳትፎ ባረጋገጠ መልኩ እንዲጠናቀቅ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችና የጸጥታ አካላት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ምክር ቤቱ በአብላጫ ድምጽ መወሰኑን ገልጸዋል።
በሌላ በኩል፤ የሀድያ፣ ሀላባ፣ ከምባታና ጠምባሮ፣ ስልጤ፣ ጉራጌ ዞኖችና የም ልዩ ወረዳ በነባሩ የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አንድ ላይ የሚቀጥሉ ይሆናል ተብሏል።



