አርብ ነሐሴ 13 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) “የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢንሳ) ነው የመጣነው” ብለው በማስፈራራት 260 ሺሕ ብር የተቀበሉት የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ሠራተኞች በእስራት መቀጣታቸው ተገለጸ።
1ኛ ተከሳሽ ዋና ሳጅን ፈቃዱ ዘውዴ (በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በአስተዳደር ዘርፍ ሥር ሾፌር)፣ 2ኛ ተከሳሽ ረ/ኢ/ር ይስሃቅ ዳካ (በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በአስተዳደር ዘርፍ ሥር ሾፌር) 3ኛ ተከሳሽ ረ/ኢ/ር ደሴ ደጆ (በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በአስተዳደር ዘርፍ በተሸከርካሪ ጥገና ዳይሬክቶሬት የገበያ ጥናት ጉዳይ አስፈፃሚ ማስተባበሪያ ሃላፊ) ሆነው በሚሰሩበት ጊዜ ከ4ኛ ተከሳሽ ዳዊት ዳዲ በዳኔ ጋር በመመሳጠር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተገን በማድረግ እና ስልጣናቸውን አላግባብ በመጠቀማቸው ነው እስራቱ የተወሰነባቸው፡፡
የዐቃቤ ህግ ክስ እንደሚያሳየው፤ ተከሳሾች ተጠርጣሪን የመያዝ እና የማቆየት ሰልጣን ሳይኖራቸው በልደታ ክ/ከተማ ወረዳ 9 ልዩ ቦታው ዲአፍሪካ ሆቴል አካባቢ ወደሚገኘው የግል ተበዳይ አሉላ አለነ የመኪና መለዋወጫ ዕቃዎች ሱቅ 2ኛ ተከሳሽ ለሥራ በተሰጠው መኪና በመሄድ 2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች መኪና ውስጥ ሆነው ሲጠብቁ 1ኛ ተከሳሽ በር ላይ ቆሞ ሽፋን ሲሰጥ፣ 4ኛ ተከሳሽ ሱቁ ውስጥ በመግባት የግል ተበዳይን ”ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) ነው የመጣነው፤ ለወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ለጥያቄ ስለምንፈልግህ ዉጣ“ በማለት የግል ተበዳይን ከሱቁ ያስወጡታል።
በማስከተልም፤ ለገሃር አካባቢ ከወሰዱት በኋላ “አንድ ሚሊዬን ብር አምጣ ካለሆነ ለኦሮሚያ ፖሊስ አሳለፈን እንሰጥሃለን” በለው በማፈራራት 260 ሺሕ ብር ወደ 4ኛ ተከሳሽ ሂሳብ እንዲያስተላልፍ ካደረጉ በሗላ ገንዘቡን በመከፋፈል ለግል ጥቅማቸው በማዋላቸው በዋና እና ልዩ ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈፀሙት ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል የሙስና ወንጀል ዐቃቤ ህግ ክስ መስርቶባቸው ነበር፡፡
ጉዳዩን ሲከታተል የነበረው በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ተከሳሾቹ ጥፋተኛ ናቸው በማለት ነሐሴ 11 ቀን 2014 በዋለው ችሎት አራቱም ተከሳሾች እያንዳንዳቸው በ3 ዓመት ፅኑ እስራት እና በ2000 ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ መወሰኑን የፍትሕ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡
የሙስና ወንጀል ጉዳዮቸ ዐቃቤ ሕግ በውሳኔው ላይ ይግባኝ ለመጠየቅ የውሳኔ ግልባጭ ጠይቆ በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡



